አንደኛ ሳሙኤል 31:1-13

  • ሳኦልና ሦስት ወንዶች ልጆቹ ሞቱ (1-13)

31  ፍልስጤማውያን ከእስራኤል ጋር እየተዋጉ ነበር።+ የእስራኤልም ሰዎች ከፍልስጤማውያን ፊት ሸሹ፤ ብዙዎቹም በጊልቦአ+ ተራራ ላይ ተገደሉ።  ፍልስጤማውያንም ሳኦልንና ወንዶች ልጆቹን እግር በእግር ተከታተሏቸው፤ ፍልስጤማውያንም የሳኦልን ልጆች ዮናታንን፣+ አቢናዳብንና ሜልኪሳን መትተው ገደሏቸው።+  ውጊያው በሳኦል ላይ በረታ፤ ቀስተኞቹም አገኙት፤ እነሱም ክፉኛ አቆሰሉት።+  ከዚያም ሳኦል ጋሻ ጃግሬውን “እነዚህ ያልተገረዙ+ ሰዎች መጥተው እንዳይወጉኝና በጭካኔ እንዳያሠቃዩኝ* ሰይፍህን መዘህ ውጋኝ” አለው። ጋሻ ጃግሬው ግን እጅግ ፈርቶ ስለነበር ፈቃደኛ አልሆነም። በመሆኑም ሳኦል ሰይፉን ወስዶ በላዩ ላይ ወድቆ ሞተ።+  ጋሻ ጃግሬውም ሳኦል መሞቱን ሲያይ+ እሱም በራሱ ሰይፍ ላይ ወድቆ ከእሱ ጋር ሞተ።  ስለዚህ ሳኦል፣ ሦስቱ ወንዶች ልጆቹ፣ ጋሻ ጃግሬውና የእሱ ሰዎች በሙሉ በዚያ ቀን አብረው ሞቱ።+  በሸለቆውና* በዮርዳኖስ አካባቢ የነበሩት እስራኤላውያን፣ የእስራኤል ሠራዊት መሸሹን እንዲሁም ሳኦልና ልጆቹ መሞታቸውን ባዩ ጊዜ ከተሞቹን ጥለው ሸሹ፤+ ከዚያም ፍልስጤማውያን መጥተው ከተሞቹን ያዙ።  በማግስቱ ፍልስጤማውያን የሞቱትን ሰዎች ልብስና ትጥቅ ለመግፈፍ ሲመጡ ሳኦልንና ሦስቱን ወንዶች ልጆቹን በጊልቦአ+ ተራራ ላይ ወድቀው አገኟቸው።  ስለሆነም የሳኦልን ራስ ከቆረጡና የጦር ትጥቁን ከገፈፉ በኋላ ወሬው በጣዖቶቻቸው+ ቤቶችና* በሕዝቡ ሁሉ መካከል እንዲሰራጭ+ ለማድረግ በመላው የፍልስጤም ምድር መልእክት ላኩ። 10  ከዚያም የጦር ትጥቁን በአስታሮት ምስሎች ቤት አስቀመጡት፣ አስከሬኑን ደግሞ በቤትሻን+ ግንብ ላይ ቸነከሩት። 11  የኢያቢስጊልያድ+ ነዋሪዎችም ፍልስጤማውያን በሳኦል ላይ ያደረጉትን ሲሰሙ 12  ተዋጊዎቹ ሁሉ ተነስተው ሌሊቱን ሙሉ ሲጓዙ አደሩ፤ ከዚያም የሳኦልንና የልጆቹን አስከሬን ከቤትሻን ግንብ ላይ አወረዱ። ወደ ኢያቢስ ተመልሰውም በዚያ አቃጠሏቸው። 13  ከዚያም አፅማቸውን+ ወስደው በኢያቢስ+ በሚገኝ የታማሪስክ ዛፍ ሥር ቀበሩት፤ ለሰባት ቀንም ጾሙ።

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “እንዳይጫወቱብኝ።”
ወይም “በረባዳማው ሜዳና።”
ወይም “ቤተ መቅደሶችና።”