ለቆሮንቶስ ሰዎች የተጻፈ የመጀመሪያው ደብዳቤ 13:1-13

  • ፍቅር፣ ከሁሉ የላቀው መንገድ (1-13)

13  በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ በኃይል እንደሚጮኽ ደወል* ወይም ሲምባል* ሆኛለሁ።  የመተንበይ ስጦታ ቢኖረኝ፣ ቅዱስ ሚስጥርን ሁሉና እውቀትን ሁሉ ባውቅ+ እንዲሁም ተራራን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ማንቀሳቀስ የሚያስችል እምነት ቢኖረኝ፣ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ።*+  ሌሎችን ለመመገብ ያለኝን ሁሉ ብሰጥ+ እንዲሁም እኩራራ ዘንድ ሰውነቴን አሳልፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ+ ምንም የማገኘው ጥቅም የለም።  ፍቅር+ ታጋሽና+ ደግ+ ነው። ፍቅር አይቀናም።+ ጉራ አይነዛም፣ አይታበይም፣+  ጨዋነት የጎደለው ምግባር አያሳይም፣*+ የራሱን ፍላጎት አያስቀድምም፣+ በቀላሉ አይበሳጭም።+ ፍቅር የበደል መዝገብ የለውም።+  ፍቅር በዓመፅ አይደሰትም፤+ ከዚህ ይልቅ ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል።  ሁሉን ችሎ ያልፋል፣+ ሁሉን ያምናል፣+ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፣+ ሁሉን ነገር በጽናት ይቋቋማል።+  ፍቅር ለዘላለም ይኖራል።* ሆኖም የመተንበይ፣ በልሳን የመናገርም* ሆነ የእውቀት ስጦታ ይቀራል።  እውቀታችን ከፊል ነውና፤+ ትንቢት የምንናገረውም በከፊል ነው፤ 10  የተሟላው ሲመጣ ግን ከፊል የሆነው ይቀራል። 11  ልጅ በነበርኩበት ጊዜ እንደ ልጅ እናገር፣ እንደ ልጅ አስብ እንዲሁም እንደ ልጅ አመዛዝን ነበር፤ አሁን ሙሉ ሰው ከሆንኩ በኋላ ግን የልጅነትን ጠባይ ትቻለሁ። 12  አሁን በብረት መስተዋት ብዥ ያለ* ምስል ይታየናል፤ በዚያን ጊዜ ግን ፊት ለፊት የማየት ያህል በግልጽ ይታየናል። አሁን ስለ አምላክ የማውቀው በከፊል ነው፤ በዚያን ጊዜ ግን እሱ እኔን በትክክል የሚያውቀኝን ያህል የተሟላ* እውቀት ይኖረኛል። 13  ይሁን እንጂ እምነት፣ ተስፋ፣ ፍቅር፣ እነዚህ ሦስቱ ይቀጥላሉ፤ ከእነዚህ መካከል የሚበልጠው ግን ፍቅር ነው።+

የግርጌ ማስታወሻ

ቃል በቃል “ነሐስ።”
እዚህ ላይ የገባው ግሪክኛ ቃል፣ እርስ በርሱ ሲጋጭ ኃይለኛ ድምፅ የሚያወጣን ክብ ቅርጽ ያለው ከብረት የተሠራ የሙዚቃ መሣሪያ ያመለክታል።
ወይም “ዋጋ ቢስ ነኝ።”
ወይም “ሥርዓት የለሽ አይደለም።”
ወይም “መቼም ቢሆን አይጠፋም።”
ሌሎች ቋንቋዎችን የመናገር ተአምራዊ ስጦታን ያመለክታል።
ወይም “ለመለየት የሚያስቸግር።”
ወይም “ትክክለኛ።”