ለቆሮንቶስ ሰዎች የተጻፈ የመጀመሪያው ደብዳቤ 6:1-20

  • ወንድሞች ፍርድ ቤት ተካሰሱ (1-8)

  • የአምላክን መንግሥት የማይወርሱ ሰዎች (9-11)

  • በሰውነታችሁ አምላክን አክብሩ (12-20)

    • “ከፆታ ብልግና ሽሹ!” (18)

6  ከእናንተ መካከል አንዱ ከሌላው ጋር የሚከራከርበት ጉዳይ ቢኖረው፣+ ጉዳዩን በቅዱሳን ፊት በማቅረብ ፋንታ በዓመፀኛ ሰዎች ፊት ለማቅረብ ፍርድ ቤት ለመሄድ እንዴት ይደፍራል?  ወይስ ቅዱሳን በዓለም ላይ እንደሚፈርዱ አታውቁም?+ ታዲያ እናንተ በዓለም ላይ የምትፈርዱ ከሆነ በጣም ተራ የሆኑ ጉዳዮችን ለመዳኘት አትበቁም?  በመላእክት ላይ እንኳ እንደምንፈርድ አታውቁም?+ ታዲያ በአሁኑ ሕይወት በሚያጋጥሙ ጉዳዮች ላይ ለምን አትፈርዱም?  ደግሞስ በአሁኑ ሕይወት የሚያጋጥሙ ዳኝነት የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ካሉ+ ጉባኤው የሚንቃቸው ሰዎች እንዲዳኙት ታደርጋላችሁ?  ይህን የምለው ኀፍረት እንዲሰማችሁ ብዬ ነው። ወንድሞቹን መዳኘት የሚችል አንድ እንኳ ጥበበኛ ሰው በመካከላችሁ የለም?  አንድ ወንድም ሌላውን ወንድም ፍርድ ቤት ይወስዳል፤ ያውም የማያምኑ ሰዎች ፊት!  እንግዲህ እርስ በርስ ተካስሳችሁ ፍርድ ቤት መሄዳችሁ ለእናንተ ትልቅ ሽንፈት ነው። ከዚህ ይልቅ እናንተ ራሳችሁ ብትበደሉ አይሻልም?+ ደግሞስ እናንተ ራሳችሁ ብትታለሉ አይሻልም?  እናንተ ግን ትበድላላችሁ እንዲሁም ታታልላላችሁ፤ ያውም የገዛ ወንድሞቻችሁን!  ወይስ ዓመፀኞች የአምላክን መንግሥት እንደማይወርሱ አታውቁም?+ አትታለሉ፤ ሴሰኞችም*+ ሆኑ ጣዖት አምላኪዎች+ ወይም አመንዝሮች+ ወይም ቀላጮች*+ ወይም ግብረ ሰዶማውያን*+ 10  ወይም ሌቦች ወይም ስግብግቦች+ ወይም ሰካራሞች+ ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ቀማኞች የአምላክን መንግሥት አይወርሱም።+ 11  አንዳንዶቻችሁም እንደዚህ ነበራችሁ። ሆኖም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስምና በአምላካችን መንፈስ ታጥባችሁ ነጽታችኋል፣+ ተቀድሳችኋል+ እንዲሁም ጻድቃን ተብላችኋል።+ 12  ሁሉም ነገር ተፈቅዶልኛል፤ ሆኖም ሁሉም ነገር ይጠቅማል ማለት አይደለም።+ ሁሉም ነገር ተፈቅዶልኛል፤ ሆኖም ለምንም ነገር ተገዢ መሆን አልሻም። 13  ምግብ ለሆድ፣ ሆድም ለምግብ ነው፤ አምላክ ግን ሁለቱንም ያጠፋቸዋል።+ አካል ለጌታ ነው እንጂ ለፆታ ብልግና* አይደለም፤+ ጌታ ደግሞ ለአካል ነው። 14  ይሁን እንጂ አምላክ በኃይሉ+ አማካኝነት ጌታን እንዳስነሳው+ እኛንም ከሞት ያስነሳናል።+ 15  ሰውነታችሁ የክርስቶስ አካል ክፍል እንደሆነ አታውቁም?+ ታዲያ የክርስቶስ አካል ክፍል የሆነውን ወስጄ ከዝሙት አዳሪ ጋር ላጣምረው? በፍጹም! 16  ከዝሙት አዳሪ ጋር የሚጣመር ሁሉ ከእሷ ጋር አንድ አካል እንደሚሆን አታውቁም? አምላክ “ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ” ብሏልና።+ 17  ሆኖም ከጌታ ጋር የተቆራኘ ሁሉ በመንፈስ ከእሱ ጋር አንድ ነው።+ 18  ከፆታ ብልግና* ሽሹ!+ አንድ ሰው የሚፈጽመው ሌላ ኃጢአት ሁሉ ከአካሉ ውጭ ነው፤ የፆታ ብልግና የሚፈጽም ሁሉ ግን በራሱ አካል ላይ ኃጢአት እየሠራ ነው።+ 19  የእናንተ አካል ከአምላክ ለተቀበላችሁት፣ በውስጣችሁ ላለው መንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ+ እንደሆነ አታውቁም?+ በተጨማሪም እናንተ የራሳችሁ አይደላችሁም፤+ 20  በዋጋ ተገዝታችኋልና።+ ስለዚህ በሰውነታችሁ+ አምላክን አክብሩ።+

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ከወንዶች ጋር የፆታ ግንኙነት የሚፈጽሙ ወንዶች።” ቃል በቃል “ከወንዶች ጋር የሚተኙ ወንዶች።”
ግብረ ሰዶማውያን ሆነው የሴት ዓይነት ሚና ያላቸውን ወንዶች ያመለክታል።
የቃላት መፍቻው ላይ “የፆታ ብልግና” የሚለውን ተመልከት።
ግሪክኛ፣ ፖርኒያ። የቃላት መፍቻው ላይ “የፆታ ብልግና” የሚለውን ተመልከት።
ግሪክኛ፣ ፖርኒያ። የቃላት መፍቻው ላይ “የፆታ ብልግና” የሚለውን ተመልከት።