ለቆሮንቶስ ሰዎች የተጻፈ የመጀመሪያው ደብዳቤ 8:1-13

  • ‘ለጣዖቶች የቀረበ ምግብ’ (1-13)

    • ‘እኛ አንድ አምላክ አለን’ (5, 6)

8  ለጣዖቶች የቀረበን ምግብ በተመለከተ፣+ ሁላችንም እውቀት እንዳለን እናውቃለን።+ እውቀት ያስታብያል፤ ፍቅር ግን ያንጻል።+  አንድ ሰው ስለ አንድ ነገር አውቃለሁ ብሎ የሚያስብ ከሆነ ስለዚያ ነገር ማወቅ የሚገባውን ያህል ገና አያውቅም።  ሆኖም አንድ ሰው አምላክን የሚወድ ከሆነ በእሱ ዘንድ የታወቀ ነው።  ለጣዖቶች የቀረበ ምግብ መብላትን በተመለከተ፣ በዓለም ላይ ጣዖት ከንቱ እንደሆነና+ ከአንዱ በቀር አምላክ እንደሌለ እናውቃለን።+  ብዙ “አማልክት” እና ብዙ “ጌቶች” እንደመኖራቸው መጠን በሰማይም ሆነ በምድር አማልክት ተብለው የሚጠሩ+ ቢኖሩም እንኳ  እኛ ግን ሁሉም ነገር ከእሱ የሆነ እኛም ለእሱ የሆን+ አንድ አምላክ+ አብ+ አለን፤ እንዲሁም ሁሉም ነገር በእሱ በኩል የሆነና እኛም በእሱ በኩል የሆን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለ።+  ይሁንና ይህ እውቀት ያላቸው ሁሉም ሰዎች አይደሉም።+ አንዳንዶች ግን ቀደም ሲል ጣዖት ያመልኩ ስለነበር የሚበሉት ምግብ ለጣዖት የተሠዋ እንደሆነ አድርገው ያስባሉ፤+ ሕሊናቸው ደካማ ስለሆነም ይረክሳል።+  ይሁን እንጂ ምግብ ከአምላክ ጋር አያቀራርበንም፤+ ባንበላ የሚጎድልብን ነገር የለም፤ ብንበላም የምናተርፈው ነገር የለም።+  ነገር ግን የመምረጥ መብታችሁ፣ ደካማ የሆኑትን በሆነ መንገድ እንዳያሰናክላቸው ተጠንቀቁ።+ 10  አንተ እውቀት ያለህ በጣዖት ቤተ መቅደስ ውስጥ ስትበላ አንድ ሰው ቢያይህ ደካማ የሆነው ይህ ሰው ሕሊናው ለጣዖት የቀረበውን ምግብ እንዲበላ አያደፋፍረውም? 11  እንግዲህ ክርስቶስ የሞተለት ይህ ደካማ የሆነው ወንድምህ በአንተ እውቀት ሳቢያ ጠፋ* ማለት ነው።+ 12  በዚህ መንገድ ወንድሞቻችሁን ስትበድሉና ደካማ የሆነውን ሕሊናቸውን ስታቆስሉ+ በክርስቶስ ላይ ኃጢአት እየሠራችሁ ነው። 13  ስለዚህ ምግብ ወንድሜን የሚያሰናክለው ከሆነ ወንድሜን ላለማሰናከል ስል ከእንግዲህ ፈጽሞ ሥጋ አልበላም።+

የግርጌ ማስታወሻ

እምነቱ ወይም የዘላለም ሕይወት ተስፋው መጥፋቱን ያመለክታል።