ለቆሮንቶስ ሰዎች የተጻፈ የመጀመሪያው ደብዳቤ 9:1-27

  • ጳውሎስ፣ በአርዓያነት የሚታይ ሐዋርያ (1-27)

    • “እህል እያበራየ ያለውን በሬ አፉን አትሰር” (9)

    • “ባልሰብክ ወዮልኝ!” (16)

    • “ለሁሉም ዓይነት ሰዎች ሁሉንም ነገር ሆንኩ” (19-23)

    • ለሕይወት በሚደረገው ሩጫ ራስን መግዛት (24-27)

9  እኔ ነፃ ሰው አይደለሁም? ሐዋርያስ አይደለሁም? ደግሞስ ጌታችንን ኢየሱስን አላየሁትም?+ እናንተ በጌታ የሥራዬ ውጤት አይደላችሁም?  ለሌሎች ሐዋርያ ባልሆን እንኳ ለእናንተ ሐዋርያ እንደሆንኩ የተረጋገጠ ነው! እናንተ የጌታ ሐዋርያ መሆኔን የሚያረጋግጥ ማኅተም ናችሁና።  ለሚመረምሩኝ የማቀርበው የመከላከያ መልስ ይህ ነው፦  እኛ የመብላትና የመጠጣት መብት* የለንም እንዴ?  እንደ ሌሎቹ ሐዋርያትና እንደ ጌታ ወንድሞች+ እንዲሁም እንደ ኬፋ*+ አማኝ የሆነች ሚስት ይዘን የመዞር መብት የለንም?+  ወይስ ሰብዓዊ ሥራ የመተው መብት የሌለን እኔና በርናባስ+ ብቻ ነን?  ለመሆኑ በራሱ ወጪ ወታደር ሆኖ የሚያገለግል ማን ነው? ወይን ተክሎ ፍሬውን የማይበላ ማን ነው?+ ወይስ መንጋ እየጠበቀ ከመንጋው ወተት የተወሰነ ድርሻ የማያገኝ ማን ነው?  ይህን የምለው ከሰብዓዊ አመለካከት አንጻር ነው? ሕጉስ ቢሆን እንዲህ አይልም?  በሙሴ ሕግ “እህል እያበራየ ያለውን በሬ አፉን አትሰር” ተብሎ ተጽፏልና።+ አምላክ ይህን የተናገረው ስለ በሬዎች ተጨንቆ ነው? 10  እንዲህ ያለው ስለ እኛ በማሰብ አይደለም? እንዲህ ተብሎ የተጻፈው በእርግጥ ስለ እኛ ነው፤ ምክንያቱም አራሹም ሆነ የሚያበራየው ሰው ሥራቸውን የሚያከናውኑት ከምርቱ ድርሻ እንደሚኖራቸው ተስፋ በማድረግ ነው። 11  እኛ በእናንተ መካከል መንፈሳዊ ነገሮች ከዘራን ከእናንተ ሥጋዊ ነገሮች ብናጭድ ትልቅ ነገር መሆኑ ነው?+ 12  ሌሎች የእናንተን ድጋፍ የማግኘት መብት ካላቸው እኛ ከእነሱ የበለጠ መብት የለንም? ይሁንና እኛ በዚህ መብት* አልተጠቀምንም፤+ ከዚህ ይልቅ ስለ ክርስቶስ የሚሰበከውን ምሥራች የሚያደናቅፍ ምንም ነገር ላለመፍጠር ሁሉን ችለን እንኖራለን።+ 13  ቅዱስ አገልግሎት የሚያከናውኑት ሰዎች ከቤተ መቅደስ የሚያገኙትን ምግብ እንደሚመገቡ እንዲሁም ዘወትር በመሠዊያው የሚያገለግሉ ከመሠዊያው የራሳቸውን ድርሻ እንደሚያገኙ አታውቁም?+ 14  በተመሳሳይም ምሥራቹን የሚያውጁ ሰዎች በምሥራቹ አማካኝነት በሚያገኙት ነገር እንዲኖሩ ጌታ አዟል።+ 15  ይሁን እንጂ እኔ ከእነዚህ ዝግጅቶች በአንዱም አልተጠቀምኩም።+ እርግጥ ይህን የጻፍኩት እንዲህ ሊደረግልኝ ይገባል ለማለት አይደለም፤ ማንም ሰው የምኮራበትን ነገር ከሚያሳጣኝ ብሞት ይሻለኛልና!+ 16  አሁን ምሥራቹን እየሰበክሁ ብሆንም ለመኩራራት ምክንያት አይሆነኝም፤ እንዲህ የማድረግ ግዴታ ተጥሎብኛልና። እንዲያውም ምሥራቹን ባልሰብክ ወዮልኝ!+ 17  ይህን በፈቃደኝነት ካከናወንኩ ሽልማት አለኝ፤ ይሁንና ሳልወድ ባደርገውም እንኳ የመጋቢነት አደራ ተጥሎብኛል።+ 18  ታዲያ ሽልማቴ ምንድን ነው? ከምሥራቹ ጋር በተያያዘ ሥልጣኔን* አላግባብ እንዳልጠቀምበት ምሥራቹን በምሰብክበት ጊዜ ምሥራቹን ያለክፍያ ማቅረብ ነው። 19  እኔ ከሰው ሁሉ ነፃ ነኝ፤ ሆኖም በተቻለ መጠን ብዙዎችን እማርክ ዘንድ ራሴን ለሁሉ ባሪያ አደረግኩ። 20  አይሁዳውያንን እማርክ ዘንድ ለአይሁዳውያን እንደ አይሁዳዊ ሆንኩ፤+ እኔ ራሴ በሕግ ሥር ባልሆንም እንኳ በሕግ ሥር ያሉትን እማርክ ዘንድ በሕግ ሥር ላሉት በሕግ ሥር እንዳለሁ ሆንኩ።+ 21  በአምላክ ፊት ከሕግ ነፃ ያልሆንኩና በክርስቶስ ፊት በሕግ ሥር ያለሁ ብሆንም እንኳ ሕግ የሌላቸውን እማርክ ዘንድ ሕግ ለሌላቸው ሕግ እንደሌለው ሰው ሆንኩ።+ 22  ደካሞችን እማርክ ዘንድ ለደካሞች ደካማ ሆንኩ።+ በተቻለ መጠን የተወሰኑ ሰዎችን አድን ዘንድ ለሁሉም ዓይነት ሰዎች ሁሉንም ነገር ሆንኩ። 23  ምሥራቹን ለሌሎች አካፍል ዘንድ ለምሥራቹ ስል ሁሉን ነገር አደርጋለሁ።+ 24  በሩጫ ውድድር ሁሉም እንደሚሮጡ፣ ሽልማቱን የሚያገኘው ግን አንዱ ብቻ እንደሆነ አታውቁም? እናንተም ሽልማቱን እንድታገኙ በዚሁ ሁኔታ ሩጡ።+ 25  በውድድር የሚሳተፍ ማንኛውም ሰው* በሁሉም ነገር ራሱን ይገዛል። እነሱ ይህን የሚያደርጉት የሚጠፋውን አክሊል+ ለማግኘት ሲሆን እኛ ግን የማይጠፋውን አክሊል ለማግኘት ነው።+ 26  ስለዚህ እኔ ያለግብ አልሮጥም፤+ ቡጢ የምሰነዝረውም አየር ለመምታት አይደለም፤ 27  ከዚህ ይልቅ ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ እኔ ራሴ በሆነ መንገድ ተቀባይነት እንዳላጣ* ሰውነቴን እየጎሰምኩ*+ እንደ ባሪያ እንዲገዛልኝ አደርገዋለሁ።

የግርጌ ማስታወሻ

ቃል በቃል “ሥልጣን።”
ጴጥሮስ ተብሎም ይጠራል።
ቃል በቃል “ሥልጣን።”
ወይም “መብቴን።”
ወይም “አትሌት።”
ወይም “ብቃቱን እንዳላጓድል።”
ወይም “እየቀጣሁ፤ አጥብቄ እየገሠጽኩ።”