ለተሰሎንቄ ሰዎች የተጻፈ የመጀመሪያው ደብዳቤ 5:1-28

  • የይሖዋ ቀን የሚመጣበት መንገድ (1-5)

    • “ሰላምና ደህንነት ሆነ!” (3)

  • ነቅተን እንኑር፤ የማመዛዘን ችሎታችንን እንጠብቅ (6-11)

  • ማሳሰቢያ (12-24)

  • የስንብት ቃላት (25-28)

5  እንግዲህ ወንድሞች፣ ጊዜያትንና ወቅቶችን በተመለከተ ምንም ነገር እንዲጻፍላችሁ አያስፈልግም።  የይሖዋ* ቀን+ የሚመጣው ሌባ በሌሊት በሚመጣበት መንገድ+ መሆኑን እናንተ ራሳችሁ በሚገባ ታውቃላችሁና።  “ሰላምና ደህንነት ሆነ!” ሲሉ ምጥ እርጉዝ ሴትን እንደሚይዛት ያልታሰበ ጥፋት ድንገት ይመጣባቸዋል፤+ ደግሞም በምንም ዓይነት አያመልጡም።  እናንተ ግን ወንድሞች፣ በጨለማ ውስጥ ስላልሆናችሁ ሌሊቱ ድንገት እንደሚነጋበት ሌባ፣ ያ ቀን ድንገት አይደርስባችሁም፤  እናንተ ሁላችሁ የብርሃን ልጆችና የቀን ልጆች ናችሁና።+ እኛ የሌሊት ወይም የጨለማ ልጆች አይደለንም።+  ስለዚህ ነቅተን እንኑር+ እንዲሁም የማስተዋል ስሜታችንን እንጠብቅ+ እንጂ እንደ ሌሎቹ አናንቀላፋ።+  የሚያንቀላፉ ሰዎች፣ የሚያንቀላፉት በሌሊት ነው፤ የሚሰክሩም ቢሆኑ የሚሰክሩት በሌሊት ነው።+  የቀን ልጆች የሆንነው እኛ ግን የማስተዋል ስሜታችንን እንጠብቅ፤ ደግሞም የእምነትንና የፍቅርን ጥሩር እንልበስ፤ የመዳንንም ተስፋ እንደ ራስ ቁር እንድፋ፤+  ምክንያቱም አምላክ የመረጠን በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኩል መዳን እንድናገኝ+ ነው እንጂ ለቁጣ አይደለም። 10  እሱ በሕይወት ብንኖርም ሆነ ብናንቀላፋ* አብረነው እንድንኖር+ ለእኛ ሞቶልናል።+ 11  ስለዚህ አሁን እያደረጋችሁት እንዳለው እርስ በርስ ተበረታቱ* እንዲሁም እርስ በርስ ተናነጹ።+ 12  እንግዲህ ወንድሞች፣ በመካከላችሁ በትጋት እየሠሩና በጌታ ሥራ አመራር እየሰጧችሁ ያሉትን እንዲሁም ምክር እየለገሷችሁ ያሉትን እንድታከብሯቸው እንለምናችኋለን፤ 13  በተጨማሪም በሚያከናውኑት ሥራ የተነሳ በፍቅር ለየት ያለ አሳቢነት እንድታሳዩአቸው እንለምናችኋለን።+ እርስ በርሳችሁ ሰላማዊ ግንኙነት ይኑራችሁ።+ 14  በሌላ በኩል ደግሞ ወንድሞች፣ ይህን እናሳስባችኋለን፦ በሥርዓት የማይሄዱትን አስጠንቅቋቸው፤*+ የተጨነቁትን* አጽናኗቸው፤ ደካሞችን ደግፏቸው፤ ሁሉንም በትዕግሥት ያዙ።+ 15  ማንም ሰው በማንም ላይ በክፉ ፋንታ ክፉ እንዳይመልስ ተጠንቀቁ፤+ ከዚህ ይልቅ እርስ በርሳችሁም ሆነ ለሌሎች ሰዎች ሁሉ ምንጊዜም መልካም የሆነውን ነገር ለማድረግ ተጣጣሩ።+ 16  ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ።+ 17  ዘወትር ጸልዩ።+ 18  ለሁሉም ነገር አመስግኑ።+ አምላክ በክርስቶስ ኢየሱስ ለእናንተ ያለው ፈቃድ ይህ ነው። 19  የመንፈስን እሳት አታጥፉ።+ 20  ትንቢቶችን አትናቁ።+ 21  ሁሉንም ነገር መርምሩ፤+ መልካም የሆነውን አጥብቃችሁ ያዙ። 22  ከማንኛውም ዓይነት ክፋት ራቁ።+ 23  የሰላም አምላክ ራሱ ሙሉ በሙሉ ይቀድሳችሁ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገኝበት ጊዜ መንፈሳችሁ፣ ነፍሳችሁና* አካላችሁ በማንኛውም ረገድ ጤናማ ይሁን፤ ደግሞም ነቀፋ አይገኝበት።+ 24  የጠራችሁ ታማኝ ነው፤ ይህን በእርግጥ ያደርገዋል። 25  ወንድሞች፣ ስለ እኛ መጸለያችሁን አታቋርጡ።+ 26  ወንድሞችን ሁሉ በተቀደሰ አሳሳም ሰላም በሏቸው። 27  ይህ ደብዳቤ ለወንድሞች ሁሉ እንዲነበብ በጌታ አደራ እላችኋለሁ።+ 28  የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።

የግርጌ ማስታወሻ

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “በሞት ብናንቀላፋ።”
ወይም “ተጽናኑ።”
ወይም “ምከሯቸው።”
ወይም “ተስፋ የቆረጡትን።” ቃል በቃል “ትንሽ ነፍስ ያላቸውን።”
ወይም “ሕይወታችሁና።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።