አንደኛ ነገሥት 10:1-29

  • የሳባ ንግሥት ሰለሞንን ልትጠይቀው መጣች (1-13)

  • ሰለሞን የነበረው ብዙ ሀብት (14-29)

10  የሳባ ንግሥት ስለ ሰለሞን ዝና እንዲሁም ከይሖዋ ስም ጋር ስላለው ግንኙነት ሰማች፤+ በመሆኑም አስቸጋሪ በሆኑ ጥያቄዎች* ልትፈትነው መጣች።+  እሷም እጅግ ታላቅ አጀብ አስከትላ+ እንዲሁም የበለሳን ዘይት፣+ በጣም ብዙ ወርቅና የከበሩ ድንጋዮች በግመል አስጭና ኢየሩሳሌም ደረሰች። ወደ ሰለሞንም ገብታ በልቧ ያለውን ሁሉ ነገረችው።  ሰለሞንም ጥያቄዎቿን ሁሉ መለሰላት። ንጉሡ ሊያብራራላት ያልቻለው* ምንም ነገር አልነበረም።  የሳባ ንግሥት የሰለሞንን ጥበብ+ ሁሉና የሠራውን ቤት ስትመለከት፣+  በገበታው ላይ የሚቀርበውን ምግብ፣+ የአገልጋዮቹን አቀማመጥ፣ አስተናጋጆቹ በማዕድ ላይ የሚያስተናግዱበትን መንገድና አለባበሳቸውን፣ መጠጥ አሳላፊዎቹን እንዲሁም በይሖዋ ቤት ዘወትር የሚያቀርባቸውን የሚቃጠሉ መሥዋዕቶች ስታይ በመገረም ፈዛ ቀረች።*  በመሆኑም ንጉሡን እንዲህ አለችው፦ “ስላከናወንካቸው ነገሮችና* ስለ ጥበብህ በአገሬ ሳለሁ የሰማሁት ነገር እውነት ነው።  ይሁንና እኔ ራሴ መጥቼ በገዛ ዓይኔ እስከማይ ድረስ የተነገረኝን ነገር አላመንኩም ነበር። እንደዚያም ሆኖ ግማሹ እንኳ አልተነገረኝም! በጥበብም ሆነ በብልጽግና ከሰማሁት ሁሉ እጅግ የላቅክ ነህ።  አብረውህ ያሉ ሰዎች ደስተኞች ናቸው፤ ዘወትር በፊትህ ቆመው ጥበብህን የሚሰሙት አገልጋዮችህም እጅግ ደስተኞች ናቸው!+  አንተን በእስራኤል ዙፋን ላይ በማስቀመጥ በአንተ ደስ የተሰኘው አምላክህ ይሖዋ ይወደስ።+ ይሖዋ ለእስራኤል ካለው ዘላለማዊ ፍቅር የተነሳ ፍትሕንና ጽድቅን እንድታሰፍን ንጉሥ አድርጎ ሾሞሃል።” 10  ከዚያም ለንጉሡ 120 ታላንት* ወርቅ እንዲሁም እጅግ ብዙ የበለሳን ዘይትና+ የከበሩ ድንጋዮች ሰጠችው።+ የሳባ ንግሥት ለንጉሥ ሰለሞን የሰጠችውን የሚያህል መጠን ያለው የበለሳን ዘይት ከዚያ በኋላ መጥቶ አያውቅም። 11  ከኦፊር ወርቅ ጭነው የመጡት የኪራም መርከቦች ከኦፊር+ እጅግ ብዙ የሰንደል ዛፍ ሳንቃዎችንና+ የከበሩ ድንጋዮችንም+ አምጥተው ነበር። 12  ንጉሡም ከሰንደል ዛፍ ሳንቃዎቹ ለይሖዋ ቤትና ለንጉሡ ቤት* ድጋፎችን እንዲሁም ለዘማሪዎቹ የሚሆኑ በገናዎችንና ሌሎች ባለ አውታር መሣሪያዎችን ሠራ።+ ይህን ያህል ብዛት ያለው የሰንደል ዛፍ ሳንቃ እስከ ዛሬ ድረስ መጥቶም ሆነ ታይቶ አያውቅም። 13  ንጉሥ ሰለሞንም ለሳባ ንግሥት በልግስና ተነሳስቶ* ከሰጣት ሌላ የፈለገችውንና የጠየቀችውን ነገር ሁሉ ሰጣት። ከዚያም ተነስታ አገልጋዮቿን በማስከተል ወደ አገሯ ተመለሰች።+ 14  ሰለሞን በየዓመቱ 666 ታላንት ወርቅ ይመጣለት ነበር፤+ 15  ይህም ከነጋዴዎች፣ ከሸቃጮች ከሚገኘው ትርፍ፣ ከዓረብ ነገሥታት ሁሉና ከአገረ ገዢዎች የሚሰበሰበውን ሳይጨምር ነው። 16  ንጉሥ ሰለሞን ከቅይጥ ወርቅ 200 ትላልቅ ጋሻዎችን ሠራ፤+ (እያንዳንዱ ጋሻ በ600 ሰቅል* ወርቅ ተለብጦ ነበር)፤+ 17  እንዲሁም ከቅይጥ ወርቅ 300 ትናንሽ ጋሻዎችን* ሠራ፤ (እያንዳንዱ ትንሽ ጋሻ በሦስት ምናን* ወርቅ ተለብጦ ነበር)። ከዚያም ንጉሡ የሊባኖስ ደን+ በተባለው ቤት አስቀመጣቸው። 18  በተጨማሪም ንጉሡ ከዝሆን ጥርስ ትልቅ ዙፋን ሠርቶ+ በተጣራ ወርቅ ለበጠው።+ 19  ወደ ዙፋኑ የሚያስወጡ ስድስት ደረጃዎች ነበሩ፤ ዙፋኑም ከኋላው በኩል ክብ ከለላ ነበረው፤ መቀመጫውም በጎንና በጎኑ የእጅ መደገፊያዎች ያሉት ሲሆን ከእጅ መደገፊያዎቹም አጠገብ ሁለት አንበሶች+ ቆመው ነበር። 20  በስድስቱ ደረጃዎች ዳርና ዳር አንድ አንድ አንበሳ፣ በአጠቃላይ 12 አንበሶች ቆመው ነበር። እንዲህ ያለ ዙፋን የሠራ አንድም ሌላ መንግሥት አልነበረም። 21  የንጉሥ ሰለሞን የመጠጫ ዕቃዎች በሙሉ ከወርቅ የተሠሩ ነበሩ፤ የሊባኖስ ደን በተባለው ቤት+ የነበሩት ዕቃዎችም በሙሉ ከንጹሕ ወርቅ የተሠሩ ነበሩ። ከብር የተሠራ ምንም ነገር አልነበረም፤ በሰለሞን ዘመን ብር እንደ ተራ ነገር ይቆጠር ነበር።+ 22  ንጉሡ ከኪራም መርከቦች ጋር አብረው በባሕር ላይ የሚጓዙ የተርሴስ+ መርከቦች ነበሩት። እነዚህ የተርሴስ መርከቦች በሦስት ዓመት አንድ ጊዜ ወርቅ፣ ብር፣ የዝሆን ጥርስ፣+ ጦጣና ጣዎስ* ጭነው ይመጡ ነበር። 23  በመሆኑም ንጉሥ ሰለሞን በብልጽግናና+ በጥበብ+ ምድር ላይ ካሉ ሌሎች ነገሥታት ሁሉ ይበልጥ ነበር። 24  የምድር ሕዝቦችም ሁሉ አምላክ በሰለሞን ልብ ውስጥ ያኖረውን ጥበብ+ ይሰሙ ዘንድ ከእሱ ጋር ለመገናኘት ይጓጉ ነበር።* 25  ወደ እሱ የሚመጡትም ሰዎች በየዓመቱ የብር ዕቃዎች፣ የወርቅ ዕቃዎች፣ ልብሶች፣ የጦር ትጥቆች፣ የበለሳን ዘይት፣ ፈረሶችና በቅሎዎች ስጦታ አድርገው ያመጡ ነበር። 26  ሰለሞንም ሠረገሎችንና ፈረሶችን* መሰብሰቡን ቀጠለ፤ እሱም 1,400 ሠረገሎችና 12,000 ፈረሶች*+ ነበሩት፤ እነሱንም በሠረገላ ከተሞችና በኢየሩሳሌም በንጉሡ አቅራቢያ አኖራቸው።+ 27  ንጉሡ በኢየሩሳሌም ያለውን ብር ከብዛቱ የተነሳ በየቦታው እንደሚገኝ ድንጋይ አደረገው፤ አርዘ ሊባኖሱንም ከብዛቱ የተነሳ በሸፌላ እንደሚገኘው የሾላ ዛፍ አደረገው።+ 28  የሰለሞን ፈረሶች ከግብፅ ያስመጣቸው ነበሩ፤ የንጉሡ ነጋዴዎችም የፈረሶቹን መንጋ አንዴ በተተመነው ዋጋ ይገዙ ነበር።*+ 29  ከግብፅ የሚመጣው እያንዳንዱ ሠረገላ 600 የብር ሰቅል ያወጣ ነበር፤ አንድ ፈረስ ደግሞ 150 ሰቅል ያወጣል፤ እነሱ ደግሞ በተራቸው ለሂታውያን+ ነገሥታትና ለሶርያ ነገሥታት ሁሉ ሠረገሎችንና ፈረሶችን ይሸጡ ነበር።

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “በእንቆቅልሾች።”
ቃል በቃል “ከንጉሡ የተሰወረ።”
ቃል በቃል “በውስጧ መንፈስ አልቀረም።”
ወይም “ስለ ቃሎችህና።”
አንድ ታላንት 34.2 ኪሎ ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “ቤተ መንግሥት።”
ቃል በቃል “በንጉሥ ሰለሞን እጅ መሠረት።”
አንድ ሰቅል 11.4 ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
አብዛኛውን ጊዜ ቀስተኞች የሚይዙት ትንሽ ጋሻ።
በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ አንድ ምናን 570 ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ዥጉርጉር ቀለም ያለው ትልቅ የወፍ ዝርያ። እንግሊዝኛ፣ ፒኮክ።
ቃል በቃል “የእሱን ፊት ይሹ ነበር።”
ወይም “ፈረሰኞችን።”
ወይም “ፈረሰኞች።”
“ከግብፅና ከቀዌ ያስመጣቸው ነበሩ፤ የንጉሡ ነጋዴዎች ከቀዌ አንዴ በተተመነው ዋጋ ይገዟቸው ነበር” ማለትም ሊሆን ይችላል። ቀዌ ኪልቅያን ልታመለክት ትችላለች።