አንደኛ ነገሥት 15:1-34

  • አብያም በይሁዳ ነገሠ (1-8)

  • አሳ በይሁዳ ላይ መግዛት ጀመረ (9-24)

  • ናዳብ የእስራኤል ንጉሥ ሆነ (25-32)

  • ባኦስ የእስራኤል ንጉሥ ሆነ (33, 34)

15  የናባጥ ልጅ ንጉሥ ኢዮርብዓም+ በነገሠ በ18ኛው ዓመት አብያም በይሁዳ ላይ ነገሠ።+  እሱም በኢየሩሳሌም ለሦስት ዓመት ገዛ። የእናቱ ስም ማአካ+ ሲሆን እሷም የአቢሴሎም የልጅ ልጅ ነበረች።  እሱም አባቱ ከእሱ በፊት በሠራው ኃጢአት ሁሉ መመላለሱን ቀጠለ፤ ልቡ እንደቀድሞ አባቱ እንደ ዳዊት ልብ በአምላኩ በይሖዋ ዘንድ ሙሉ* አልነበረም።  ሆኖም በዳዊት+ የተነሳ አምላኩ ይሖዋ ከእሱ በኋላ ልጁን በማስነሳትና ኢየሩሳሌም ጸንታ እንድትኖር በማድረግ በኢየሩሳሌም መብራት ሰጠው።+  ምክንያቱም ዳዊት በይሖዋ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር አድርጓል፤ እንዲሁም ከሂታዊው ከኦርዮ ጋር በተያያዘ ከፈጸመው ነገር በስተቀር በሕይወት ዘመኑ ሁሉ እሱ ከሰጠው ከየትኛውም ትእዛዝ ፈቀቅ አላለም።+  በሕይወት ዘመኑ ሁሉ በሮብዓምና በኢዮርብዓም መካከል ጦርነት ነበር።+  የቀረው የአብያም ታሪክ፣ ያደረጋቸው ነገሮች በሙሉ በይሁዳ ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው ይገኙ የለም?+ በአብያምና በኢዮርብዓም መካከልም ጦርነት ነበር።+  በመጨረሻም አብያም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊት ከተማም ቀበሩት፤ በእሱም ምትክ+ ልጁ አሳ+ ነገሠ።  የእስራኤል ንጉሥ ኢዮርብዓም በነገሠ በ20ኛው ዓመት አሳ በይሁዳ ላይ መግዛት ጀመረ። 10  እሱም በኢየሩሳሌም ለ41 ዓመት ገዛ። የአያቱም ስም ማአካ+ ሲሆን እሷም የአቢሴሎም የልጅ ልጅ ነበረች። 11  አሳ እንደ አባቱ እንደ ዳዊት በይሖዋ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር አደረገ።+ 12  እሱም የቤተ መቅደስ ቀላጮችን* ከምድሪቱ አባረረ፤+ እንዲሁም አባቶቹ የሠሯቸውን አስጸያፊ ጣዖቶች* በሙሉ አስወገደ።+ 13  ሌላው ቀርቶ አያቱ ማአካ+ ለማምለኪያ ግንዱ* አምልኮ ጸያፍ ጣዖት ሠርታ ስለነበር ከእመቤትነቷ* ሻራት። አሳ፣ አያቱ የሠራችውን ጸያፍ ጣዖት ቆርጦ+ በቄድሮን ሸለቆ+ አቃጠለው። 14  ከፍ ያሉት የማምለኪያ ቦታዎች ግን አልተወገዱም ነበር።+ ያም ሆኖ አሳ በሕይወት ዘመኑ* ሁሉ ልቡ በይሖዋ ዘንድ ሙሉ* ነበር። 15  እሱና አባቱ የቀደሷቸውን ነገሮች ይኸውም ብሩን፣ ወርቁንና ልዩ ልዩ ዕቃዎችን ወደ ይሖዋ ቤት አስገባ።+ 16  በአሳና የእስራኤል ንጉሥ በሆነው በባኦስ+ መካከል የማያቋርጥ ጦርነት ነበር። 17  በመሆኑም የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ በይሁዳ ላይ ዘመተ፤ እሱም ማንም ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ አሳ እንዳይገባና እንዳይወጣ* ለማድረግ ራማን+ መገንባት* ጀመረ።+ 18  በዚህ ጊዜ አሳ በይሖዋ ቤት ግምጃ ቤትና በንጉሡ ቤት* ግምጃ ቤት የቀረውን ብርና ወርቅ ሁሉ አውጥቶ ለአገልጋዮቹ ሰጣቸው። ከዚያም ንጉሥ አሳ እነዚህን አገልጋዮቹን በደማስቆ ወደሚገኘው የሶርያ ንጉሥ+ ማለትም የሄዝዮን ልጅ፣ የታብሪሞን ልጅ ወደሆነው ወደ ቤንሃዳድ እንዲህ ሲል ላካቸው፦ 19  “በእኔና በአንተ እንዲሁም በአባቴና በአባትህ መካከል ውል* አለ። እኔ የብርና የወርቅ ስጦታ ልኬልሃለሁ። ስለዚህ ና፣ የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ ከእኔ እንዲርቅ ከእሱ ጋር የገባኸውን ውል* አፍርስ።” 20  ቤንሃዳድ የንጉሥ አሳን ሐሳብ ተቀብሎ የጦር ሠራዊቱን አለቆች በእስራኤል ከተሞች ላይ አዘመተ፤ እነሱም ኢዮንን፣+ ዳንን፣+ አቤልቤትማዓካን እንዲሁም ኪኔሬትን ሁሉና መላውን የንፍታሌም ምድር መቱ። 21  ባኦስም ይህን ሲሰማ ወዲያውኑ ራማን መገንባቱን* አቁሞ በቲርጻ+ መኖሩን ቀጠለ። 22  ከዚያም ንጉሥ አሳ ማንንም ሳያስቀር የይሁዳን ሰዎች ሁሉ ሰበሰበ፤ እነሱም ባኦስ እየገነባባቸው የነበሩትን የራማን ድንጋዮችና ሳንቃዎች አጋዙ፤ ንጉሥ አሳም በድንጋዮቹና በሳንቃዎቹ በቢንያም የምትገኘውን ጌባንና+ ምጽጳን+ ገነባ።* 23  የቀረው የአሳ ታሪክ ሁሉ፣ ኃያልነቱ ሁሉ፣ ያደረጋቸው ነገሮች በሙሉና የገነባቸው* ከተሞች በይሁዳ ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው ይገኙ የለም? ሆኖም አሳ ባረጀ ጊዜ በእግር ሕመም ይሠቃይ ነበር።+ 24  በመጨረሻም አሳ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በአባቱ በዳዊት ከተማም ከእነሱ ጋር ተቀበረ፤ በእሱም ምትክ ልጁ ኢዮሳፍጥ+ ነገሠ። 25  የይሁዳ ንጉሥ አሳ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት የኢዮርብዓም ልጅ ናዳብ+ የእስራኤል ንጉሥ ሆነ፤ እሱም በእስራኤል ላይ ለሁለት ዓመት ገዛ። 26  በይሖዋም ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር ማድረጉን ገፋበት፤ የአባቱንም መንገድ ተከተለ፤+ እንዲሁም አባቱ እስራኤላውያን እንዲፈጽሙ ባደረገው ኃጢአት ተመላለሰ።+ 27  ከይሳኮር ቤት የሆነው የአኪያህ ልጅ ባኦስ በእሱ ላይ አሴረ፤ ናዳብና እስራኤል ሁሉ የፍልስጤማውያን ከተማ የሆነችውን ጊበቶንን+ ከበው ሳሉ ባኦስ ጊበቶን ላይ ናዳብን ገደለው። 28  በመሆኑም ባኦስ የይሁዳ ንጉሥ አሳ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት ናዳብን ገድሎ በምትኩ ነገሠ። 29  እሱም እንደነገሠ ወዲያውኑ የኢዮርብዓምን ቤት ሁሉ ፈጀ። ከኢዮርብዓም ቤት እስትንፋስ ያለውን አንድም ሰው አላስቀረም፤ ይሖዋ በአገልጋዩ በሴሎናዊው በአኪያህ በኩል በተናገረው መሠረት ሁሉንም ደመሰሳቸው።+ 30  ይህም የሆነው ኢዮርብዓም በፈጸመው ኃጢአትና እስራኤላውያን እንዲፈጽሙ ባደረገው ኃጢአት የእስራኤልን አምላክ ይሖዋን ክፉኛ ስላስቆጣው ነው። 31  የቀረው የናዳብ ታሪክና ያደረጋቸው ነገሮች በሙሉ በእስራኤል ነገሥታት ዘመን ስለተፈጸሙት ነገሮች በሚተርከው የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈው ይገኙ የለም? 32  በአሳና የእስራኤል ንጉሥ በሆነው በባኦስ መካከል የማያቋርጥ ጦርነት ነበር።+ 33  የይሁዳ ንጉሥ አሳ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት የአኪያህ ልጅ ባኦስ በቲርጻ ሆኖ በመላው እስራኤል ላይ ለ24 ዓመት ገዛ።+ 34  ሆኖም በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር ማድረጉን ገፋበት፤+ የኢዮርብዓምን መንገድ ተከተለ፤ እንዲሁም ኢዮርብዓም እስራኤላውያን እንዲፈጽሙ ባደረገው ኃጢአት ተመላለሰ።+

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ለአምላኩ ለይሖዋ ሙሉ በሙሉ ያደረ።”
እዚህ ላይ የገባው የዕብራይስጥ ቃል “ፋንድያ” ከሚለው ቃል ጋር ዝምድና ሊኖረው የሚችል ሲሆን ንቀትን ለማመልከት ተሠርቶበታል።
ግብረ ሰዶማውያን ሆነው የሴት ዓይነት ሚና ያላቸውን ወንዶች ያመለክታል።
ወይም “እንደ ንጉሡ እናት ተቆጥራ ከተሰጣት ቦታ።”
ቃል በቃል “በቀናቱ።”
ወይም “ሙሉ በሙሉ ለይሖዋ ያደረ።”
ወይም “ከይሁዳ ንጉሥ ከአሳ ግዛት ማንም እንዳይወጣ ወይም ማንም ወደዚያ እንዳይገባ።”
ወይም “ማጠናከር፤ መልሶ መገንባት።”
ወይም “ቤተ መንግሥት።”
ወይም “ቃል ኪዳን።”
ወይም “ቃል ኪዳን።”
ወይም “ማጠናከሩን፤ መልሶ መገንባቱን።”
ወይም “አጠናከረ፤ መልሶ ገነባ።”
ወይም “ያጠናከራቸው፤ መልሶ የገነባቸው።”