አንደኛ ነገሥት 17:1-24

  • ኤልያስ ድርቅ እንደሚከሰት ትንቢት ተናገረ (1)

  • ኤልያስን ቁራዎች መገቡት (2-7)

  • ኤልያስ በሰራፕታ ወደምትገኘው መበለት ሄደ (8-16)

  • የመበለቷ ልጅ ሞተ፤ ከዚያም ከሞት ተነሳ (17-24)

17  በዚህ ጊዜ ከጊልያድ+ ነዋሪዎች አንዱ የሆነው ቲሽባዊው ኤልያስ*+ አክዓብን “በማገለግለውና* ሕያው በሆነው በእስራኤል አምላክ በይሖዋ እምላለሁ፣ በእኔ ትእዛዝ ካልሆነ በቀር በእነዚህ ዓመታት ጠል ወይም ዝናብ አይኖርም!” አለው።+  የይሖዋም ቃል እንዲህ ሲል ወደ እሱ መጣ፦  “ከዚህ ተነስተህ ወደ ምሥራቅ አቅጣጫ ሂድ፤ ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ በሚገኘው በከሪት ሸለቆም* ተደበቅ።  ከጅረቱ ትጠጣለህ፤ ቁራዎችም እዚያ ምግብ እንዲያመጡልህ አዛለሁ።”+  እሱም ወዲያውኑ ሄዶ ይሖዋ እንዳዘዘው አደረገ፤ ሄዶም ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ በሚገኘው በከሪት ሸለቆ* ተቀመጠ።  ቁራዎቹም ጠዋትና ማታ ምግብና ሥጋ ያመጡለት ነበር፤ እሱም ከጅረቱ ይጠጣ ነበር።+  ሆኖም በምድሪቱ ላይ ዝናብ ስላልዘነበ ከተወሰኑ ቀናት በኋላ ጅረቱ ደረቀ።+  ከዚያም የይሖዋ ቃል እንዲህ ሲል ወደ እሱ መጣ፦  “ተነስተህ በሲዶና ወደምትገኘው ወደ ሰራፕታ ሂድ፤ እዚያም ተቀመጥ። እኔም በዚያ አንዲት መበለት እንድትመግብህ አዛለሁ።”+ 10  ኤልያስም ተነስቶ ወደ ሰራፕታ ሄደ። ወደ ከተማዋ መግቢያ በደረሰም ጊዜ አንዲት መበለት ጭራሮ ስትለቅም አገኘ። መበለቲቱንም ጠርቶ “እባክሽ የምጠጣው ትንሽ ውኃ በዕቃ ስጪኝ” አላት።+ 11  ልታመጣለት ስትሄድም ጠራትና “እባክሽ ቁራሽ ዳቦም ይዘሽልኝ ነይ” አላት። 12  በዚህ ጊዜ እንዲህ አለችው፦ “ሕያው በሆነው አምላክህ በይሖዋ እምላለሁ፣ በማድጋው ውስጥ ካለው አንድ እፍኝ ዱቄትና በማሰሮው ውስጥ ካለው ጥቂት ዘይት በስተቀር ምንም ዳቦ የለኝም።+ ለእኔና ለልጄ የሆነች ነገር ለማዘጋጀት ጭራሮ እየለቀምኩ ነው። እኛም እሷን ቀምሰን እንሞታለን።” 13  ከዚያም ኤልያስ እንዲህ አላት፦ “አይዞሽ ስጋት አይግባሽ። ወደ ቤት ገብተሽ እንዳልሽው አድርጊ። ብቻ በመጀመሪያ ከዚያችው ካለችሽ ላይ ትንሽ ቂጣ ጋግረሽ አምጪልኝ። ከዚያ በኋላ ለአንቺና ለልጅሽ የሆነ ነገር ማዘጋጀት ትችያለሽ። 14  ምክንያቱም የእስራኤል አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ይሖዋ በምድሪቱ ላይ ዝናብ እስከሚያዘንብበት ዕለት ድረስ ከማድጋው ዱቄት አይጠፋም፤ ከማሰሮውም ዘይት አያልቅም።’”+ 15  ስለሆነም ሄዳ ኤልያስ እንዳላት አደረገች፤ እሷም ሆነች እሱ እንዲሁም ቤተሰቧ ለብዙ ቀናት ሲመገቡ ቆዩ።+ 16  ይሖዋ በኤልያስ አማካኝነት በተናገረው ቃል መሠረት ከማድጋው ዱቄት አልጠፋም፤ ከማሰሮውም ዘይት አላለቀም። 17  ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ የቤቱ ባለቤት፣ ልጇ ታመመ፤ ሕመሙም እጅግ ስለጠናበት እስትንፋሱ ቀጥ አለ።+ 18  በዚህ ጊዜ ሴትየዋ ኤልያስን “የእውነተኛው አምላክ ሰው ሆይ፣ ምን አደረግኩህ?* የመጣኸው በደሌን ልታስታውሰኝና ልጄን ልትገድል ነው?” አለችው።+ 19  እሱ ግን “ልጅሽን ስጪኝ” አላት። ከዚያም ልጁን ከእቅፏ ወስዶ እሱ ወዳረፈበት በሰገነቱ ላይ ወዳለው ክፍል ይዞት ወጣ፤ ልጁንም በራሱ አልጋ ላይ አስተኛው።+ 20  እሱም “አምላኬ ይሖዋ ሆይ፣+ እኔን ያሳረፈችኝ የዚህች መበለት ልጅ እንዲሞት በማድረግ በእሷም ላይ መከራ ታመጣባታለህ?” በማለት ወደ ይሖዋ ጮኸ። 21  ከዚያም ልጁ ላይ ሦስት ጊዜ ከተዘረጋበት በኋላ “አምላኬ ይሖዋ ሆይ፣ እባክህ የዚህ ልጅ ሕይወት ይመለስለት”* ብሎ ወደ ይሖዋ ጮኸ። 22  ይሖዋም የኤልያስን ልመና ሰማ፤+ የልጁም ሕይወት ተመለሰለት፤* እሱም ሕያው ሆነ።+ 23  ከዚያም ኤልያስ ልጁን ይዞት ሰገነት ላይ ካለው ክፍል ወደ ቤት ከወረደ በኋላ ለእናቱ ሰጣት፤ ኤልያስም “ይኸው፣ ልጅሽ ሕያው ሆኗል” አላት።+ 24  በዚህ ጊዜ ሴትየዋ ኤልያስን “አንተ በእርግጥ የአምላክ ሰው+ እንደሆንክ በአንደበትህም ያለው የይሖዋ ቃል እውነት እንደሆነ አሁን አወቅኩ” አለችው።

የግርጌ ማስታወሻ

“አምላኬ ይሖዋ ነው” የሚል ትርጉም አለው።
ቃል በቃል “ፊቱ በምቆመውና።”
ወይም “ደረቅ ወንዝም።”
ወይም “ደረቅ ወንዝ።”
ወይም “እኔ ከአንተ ጋር ምን አለኝ?”
ወይም “ነፍስ ትመለስለት።”
ወይም “ነፍስ ተመለሰችለት።”