አንደኛ ነገሥት 19:1-21

  • ኤልያስ ከኤልዛቤል ሸሸ (1-8)

  • ይሖዋ ለኤልያስ በኮሬብ ተገለጠለት (9-14)

  • ኤልያስ ሃዛኤልን፣ ኢዩንና ኤልሳዕን እንዲቀባቸው ተነገረው (15-18)

  • ኤልሳዕ የኤልያስ ተተኪ እንዲሆን ተሾመ (19-21)

19  ከዚያም አክዓብ+ ኤልያስ ያደረገውን ሁሉና ነቢያቱን በሙሉ እንዴት በሰይፍ እንደገደለ+ ለኤልዛቤል+ ነገራት።  በዚህ ጊዜ ኤልዛቤል “ነገ በዚህ ሰዓት ከእነሱ እንደ አንዱ ሳላደርግህ* ብቀር አማልክት እንዲህ ያድርጉብኝ፤ ከዚህ የባሰም ያምጡብኝ!” ብሎ ለኤልያስ እንዲነግረው መልእክተኛ ላከችበት።  በዚህ ጊዜ ኤልያስ ፈራ፤ በመሆኑም ሕይወቱን* ለማትረፍ ሸሸ።+ በይሁዳ ወደምትገኘው+ ወደ ቤርሳቤህም+ መጣ፤ አገልጋዩንም እዚያ ተወው።  ከዚያም በምድረ በዳው የአንድ ቀን መንገድ ከተጓዘ በኋላ ወደ አንድ የክትክታ ዛፍ ሲደርስ ሥሩ ተቀመጠ፤ እንዲሞትም* መለመን ጀመረ። እንዲህም አለ፦ “አሁንስ በቅቶኛል! ይሖዋ ሆይ፣ እኔ ከአባቶቼ አልበልጥምና ሕይወቴን* ውሰዳት።”+  ከዚያም በክትክታው ዛፍ ሥር ጋደም አለ፤ እንቅልፍም ወሰደው። ሆኖም ድንገት አንድ መልአክ ነካ አደረገውና+ “ተነስና ብላ” አለው።+  እሱም ቀና ብሎ ሲመለከት ራስጌው አጠገብ በጋሉ ድንጋዮች ላይ የተቀመጠ ዳቦ እንዲሁም በውኃ መያዣ ዕቃ ውስጥ ያለ ውኃ አየ። እሱም ከበላና ከጠጣ በኋላ ተመልሶ ተኛ።  በኋላም የይሖዋ መልአክ ለሁለተኛ ጊዜ መጥቶ ነካ አደረገውና “ሩቅ መንገድ ስለምትጓዝ ተነስና ብላ” አለው።  ስለሆነም ተነስቶ በላ፤ ጠጣም፤ ከምግቡም ባገኘው ብርታት እስከ እውነተኛው አምላክ ተራራ እስከ ኮሬብ+ ድረስ ለ40 ቀንና ለ40 ሌሊት ተጓዘ።  እዚያም ሲደርስ ወደ አንድ ዋሻ+ ገብቶ አደረ፤ በዚህ ጊዜ የይሖዋ ቃል ወደ እሱ መጥቶ “ኤልያስ እዚህ ምን ታደርጋለህ?” አለው። 10  እሱም እንዲህ አለ፦ “እኔ ለሠራዊት ጌታ ለይሖዋ እጅግ ቀንቻለሁ፤+ ምክንያቱም የእስራኤል ሰዎች ቃል ኪዳንህን ትተዋል፤+ መሠዊያዎችህንም አፈራርሰዋል፤ ነቢያትህን በሰይፍ ገድለዋል፤+ እንግዲህ የቀረሁት እኔ ብቻ ነኝ። ይኸው አሁን ደግሞ የእኔንም ሕይወት* ለማጥፋት እየፈለጉ ነው።”+ 11  እሱ ግን “ውጣና ተራራው ላይ ይሖዋ ፊት ቁም” አለው። በዚህ ጊዜ ይሖዋ እያለፈ+ ነበር፤ ታላቅና ኃይለኛ ነፋስም በይሖዋ ፊት ተራሮቹን ሰነጣጠቀ፤+ ዓለቶቹንም ፈረካከሰ፤ ይሖዋ ግን በነፋሱ ውስጥ አልነበረም። ከነፋሱ ቀጥሎ ደግሞ የምድር መናወጥ ተከሰተ፤ ይሖዋ ግን በምድር መናወጡ+ ውስጥ አልነበረም። 12  ከምድር መናወጡ በኋላም እሳት+ መጣ፤ ይሖዋ ግን በእሳቱ ውስጥ አልነበረም። ከእሳቱ በኋላ ደግሞ ዝግ ያለና ለስለስ ያለ ድምፅ ተሰማ።+ 13  ኤልያስ ይህን ድምፅ ሲሰማ ወዲያውኑ በለበሰው የነቢይ ልብስ ፊቱን ሸፈነ፤+ ወጥቶም ዋሻው ደጃፍ ላይ ቆመ። ከዚያም አንድ ድምፅ “ኤልያስ እዚህ ምን ታደርጋለህ?” ሲል ጠየቀው። 14  እሱም እንዲህ አለ፦ “እኔ ለሠራዊት ጌታ ለይሖዋ እጅግ ቀንቻለሁ፤ ምክንያቱም የእስራኤል ሰዎች ቃል ኪዳንህን ትተዋል፤+ መሠዊያዎችህንም አፈራርሰዋል፤ ነቢያትህን በሰይፍ ገድለዋል፤ እንግዲህ የቀረሁት እኔ ብቻ ነኝ። ይኸው አሁን ደግሞ የእኔንም ሕይወት* ለማጥፋት እየፈለጉ ነው።”+ 15  ይሖዋም እንዲህ አለው፦ “ወደ ደማስቆ ምድረ በዳ ተመልሰህ ሂድ። እዚያም ስትደርስ ሃዛኤልን+ በሶርያ ላይ ንጉሥ አድርገህ ቀባው። 16  እንዲሁም የኒምሺን የልጅ ልጅ ኢዩን+ በእስራኤል ላይ ንጉሥ አድርገህ ቀባው፤ የአቤልምሆላ ሰው የሆነውን የሻፋጥን ልጅ ኤልሳዕን* ደግሞ በአንተ ምትክ ነቢይ አድርገህ ቀባው።+ 17  ከሃዛኤል ሰይፍ+ ያመለጠውን ኢዩ ይገድለዋል፤+ ከኢዩ ሰይፍ ያመለጠውን ደግሞ ኤልሳዕ ይገድለዋል።+ 18  እኔም ለባአል ያልተንበረከኩና+ እሱን ያልሳሙ+ በእስራኤል ውስጥ የቀሩ 7,000 ሰዎች አሉኝ።”+ 19  ኤልያስም ከዚያ ወጥቶ ሄደ፤ የሻፋጥንም ልጅ ኤልሳዕን ከፊቱ 12 ጥማድ በሬዎች እያረሱ፣ እሱም በ12ኛው ጥማድ በሬ እያረሰ አገኘው። ኤልያስም ወደ እሱ በመሄድ የራሱን የነቢይ ልብስ+ አውልቆ ላዩ ላይ ጣል አደረገበት። 20  በዚህ ጊዜ ኤልሳዕ በሬዎቹን እዚያው በመተው ኤልያስን ተከትሎ እየሮጠ “እባክህ፣ አባቴንና እናቴን ስሜ እንድመጣ ፍቀድልኝ። ከዚያ በኋላ እከተልሃለሁ” አለው። እሱም “ሂድ ተመለስ፤ እኔ መቼ ከለከልኩህ?” አለው። 21  በመሆኑም ተመለሰ፤ ከዚያም አንድ ጥማድ በሬ ወስዶ መሥዋዕት አደረገ፤ በእርሻ መሣሪያዎቹም የበሬዎቹን ሥጋ በመቀቀል ለሕዝቡ ሰጠ፤ እነሱም በሉ። ይህን ካደረገ በኋላም ተነስቶ ኤልያስን ተከተለው፤ እሱንም ያገለግለው ጀመር።+

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ነፍስህን እንደ እነሱ ነፍስ ሳላደርጋት።”
ወይም “ነፍሱን።”
ወይም “ነፍሴን።”
ወይም “ነፍሱ እንድትሞትም።”
ወይም “ነፍስ።”
ወይም “ነፍስ።”
“አምላክ አዳኝ ነው” የሚል ትርጉም አለው።