አንደኛ ነገሥት 2:1-46

  • ዳዊት ለሰለሞን መመሪያ ሰጠው (1-9)

  • ዳዊት ሞተ፤ ሰለሞን ነገሠ (10-12)

  • አዶንያስ የጠነሰሰው ሴራ ሕይወቱን አሳጣው (13-25)

  • አብያታር ተባረረ፤ ኢዮዓብ ተገደለ (26-35)

  • ሺምአይ ተገደለ (36-46)

2  ዳዊት የሚሞትበት ቀን ሲቃረብ ልጁን ሰለሞንን እንዲህ ሲል አዘዘው፦  “እንግዲህ እኔ የምሞትበት ጊዜ ቀርቧል።* ስለሆነም በርታ፤+ ወንድ ሁን።+  በሙሴ ሕግ ላይ በተጻፈው መሠረት በመንገዶቹ በመሄድ እንዲሁም ደንቦቹን፣ ትእዛዛቱን፣ ፍርዶቹንና ማሳሰቢያዎቹን በመጠበቅ ለአምላክህ ለይሖዋ ያለብህን ግዴታ ፈጽም፤+ ይህን ካደረግክ የምታከናውነው ሁሉ ይሳካልሃል፤ በምትሄድበትም ሁሉ ይቃናልሃል።  ይሖዋም እንዲህ በማለት የገባልኝን ቃል ይፈጽማል፦ ‘ልጆችህ፣ በሙሉ ልባቸውና በሙሉ ነፍሳቸው*+ በፊቴ በታማኝነት በመመላለስ መንገዳቸውን ከጠበቁ ከዘር ሐረግህ በእስራኤል ዙፋን ላይ የሚቀመጥ ሰው አይታጣም።’+  “የጽሩያ ልጅ ኢዮዓብ በእኔ ላይ ያደረገውን ነገር ይኸውም በሁለቱ የእስራኤል ሠራዊት አለቆች ማለትም በኔር ልጅ በአበኔርና+ በየቴር ልጅ በአሜሳይ+ ላይ ያደረገውን በሚገባ ታውቃለህ። ይህ ሰው እነዚህን ሰዎች በመግደል ጦርነት ሳይኖር በሰላሙ ጊዜ ደም አፍስሷል፤+ እንዲሁም በወገቡ ላይ የታጠቀው ቀበቶና በእግሩ ላይ ያደረገው ጫማ በጦርነት ጊዜ በሚፈሰው ደም እንዲበከል አድርጓል።  እንግዲህ እንደ ጥበብህ አድርግ፤ ሽበቱ በሰላም ወደ መቃብር* እንዲወርድ አታድርግ።+  “ሆኖም ለቤርዜሊ+ ልጆች ታማኝ ፍቅር አሳያቸው፤ እነሱም ከማዕድህ ከሚበሉ ሰዎች መካከል ይሁኑ፤ ምክንያቱም ከወንድምህ ከአቢሴሎም ፊት በሸሸሁ ጊዜ+ እነሱም ከጎኔ ቆመው ነበር።+  “በተጨማሪም ከባሁሪም የመጣው ቢንያማዊው የጌራ ልጅ ሺምአይ አብሮህ አለ። ወደ ማሃናይም በሄድኩበት ዕለት+ ከባድ እርግማን የረገመኝ እሱ ነው፤+ ሆኖም እኔን ለማግኘት ወደ ዮርዳኖስ በወረደ ጊዜ ‘በሰይፍ አልገድልህም’ ብዬ በይሖዋ ማልኩለት።+  አንተ ጥበበኛ ስለሆንክና በእሱ ላይ ምን ማድረግ እንዳለብህ ስለምታውቅ ሳትቀጣ አትተወው፤+ ሽበቱ በደም ወደ መቃብር* እንዲወርድ አድርግ።”+ 10  ከዚያም ዳዊት ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊት ከተማም+ ተቀበረ። 11  ዳዊት በእስራኤል ላይ ንጉሥ ሆኖ የገዛው ለ40 ዓመት ነበር። በኬብሮን+ ለ7 ዓመት፣ በኢየሩሳሌም ደግሞ ለ33 ዓመት ነገሠ።+ 12  ከዚያም ሰለሞን በአባቱ በዳዊት ዙፋን ላይ ተቀመጠ፤ ቀስ በቀስም ንግሥናው እየጸና ሄደ።+ 13  ከጊዜ በኋላም የሃጊት ልጅ አዶንያስ ወደ ሰለሞን እናት ወደ ቤርሳቤህ መጣ። እሷም “የመጣኸው በሰላም ነው?” አለችው፤ እሱም “አዎ፣ በሰላም ነው” አላት። 14  ከዚያም “አንድ የምነግርሽ ጉዳይ አለኝ” አላት። እሷም “እሺ፣ ንገረኝ” አለችው። 15  እሱም እንዲህ አላት፦ “ንግሥናው የእኔ ሊሆን እንደነበረና እስራኤልም ሁሉ ይነግሣል ብለው ይጠብቁ እንደነበር* በሚገባ ታውቂያለሽ፤+ ይሁንና ንግሥናው የእኔ መሆኑ ቀርቶ የወንድሜ ሆነ፤ ምክንያቱም ይሖዋ ንግሥናው የእሱ እንዲሆን ወስኖ ነበር።+ 16  ሆኖም አሁን አንድ የምጠይቅሽ ነገር አለ። መቼም አታሳፍሪኝም።” እሷም “እሺ ንገረኝ” አለችው። 17  እሱም “እባክሽ፣ ንጉሥ ሰለሞን የጠየቅሽውን እንቢ ስለማይልሽ ሹነማዊቷን አቢሻግን+ እንዲድርልኝ ጠይቂው” አላት። 18  በዚህ ጊዜ ቤርሳቤህ “መልካም! ንጉሡን አነጋግርልሃለሁ” አለችው። 19  በመሆኑም ቤርሳቤህ የአዶንያስን ጉዳይ ልትነግረው ወደ ንጉሥ ሰለሞን ገባች። ንጉሡም ወዲያውኑ ሊቀበላት ተነሳ፤ ሰገደላትም። ከዚያም ዙፋኑ ላይ ተቀመጠ፤ የንጉሡም እናት በቀኙ እንድትቀመጥ ዙፋን አስመጣላት። 20  እሷም “አንዲት ትንሽ ነገር ልጠይቅህ አስቤ ነበር። መቼም እንቢ አትለኝም” አለችው። ንጉሡም “እናቴ ሆይ፣ ንገሪኝ፤ የጠየቅሽኝን እንቢ አልልሽም” አላት። 21  እሷም “ሹነማዊቷ አቢሻግ ለወንድምህ ለአዶንያስ ትዳርለት” አለችው። 22  በዚህ ጊዜ ንጉሥ ሰለሞን ለእናቱ እንዲህ ሲል መለሰላት፦ “ለአዶንያስ ሹነማዊቷን አቢሻግን ብቻ ለምን ትጠይቂለታለሽ? ታላቅ ወንድሜ+ ስለሆነ ንግሥናም ጠይቂለት እንጂ፤+ ካህኑ አብያታርና የጽሩያ+ ልጅ ኢዮዓብም+ እየደገፉት ነው።” 23  ከዚያም ንጉሥ ሰለሞን እንዲህ ሲል በይሖዋ ማለ፦ “አዶንያስ ይህን በመጠየቁ ሕይወቱን ሳያጣ ቢቀር* አምላክ ይህን ያድርግብኝ፤ ከዚህ የከፋም ነገር ያምጣብኝ። 24  አሁንም በሚገባ ባጸናኝ፣+ በአባቴ በዳዊት ዙፋን ላይ ባስቀመጠኝና በገባው ቃል መሠረት ቤት በሠራልኝ*+ ሕያው በሆነው በይሖዋ እምላለሁ፣ አዶንያስ በዛሬዋ ዕለት ይገደላል።”+ 25  ንጉሥ ሰለሞንም ወዲያውኑ የዮዳሄን ልጅ በናያህን+ ላከው፤ እሱም ወጥቶ አዶንያስን መታው፤* እሱም ሞተ። 26  ንጉሡም ካህኑን አብያታርን+ እንዲህ አለው፦ “በአናቶት+ ወደሚገኘው እርሻህ ሂድ! አንተ ሞት የሚገባህ ሰው ነህ፤ ሆኖም በአባቴ በዳዊት ፊት የሉዓላዊውን ጌታ የይሖዋን ታቦት ስለተሸከምክና+ በአባቴ ላይ የደረሰውን መከራ ሁሉ ስለተጋራህ ዛሬ አልገድልህም።”+ 27  በመሆኑም ይሖዋ በሴሎ፣+ በኤሊ ቤት+ ላይ እንደሚደርስ የተናገረው ነገር ይፈጸም ዘንድ ሰለሞን አብያታርን የይሖዋ ካህን ሆኖ እንዳያገለግል አባረረው። 28  ኢዮዓብ ቀደም ሲል ከአቢሴሎም+ጋር ወግኖ ያልነበረ ቢሆንም አዶንያስን+ ደግፎ ስለነበር ይህን ወሬ ሲሰማ ወደ ይሖዋ ድንኳን+ በመሸሽ የመሠዊያውን ቀንዶች ያዘ። 29  ከዚያም ንጉሥ ሰለሞን “ኢዮዓብ ወደ ይሖዋ ድንኳን ሸሽቶ እዚያ በመሠዊያው አጠገብ ይገኛል” ተብሎ ተነገረው። በመሆኑም ሰለሞን የዮዳሄን ልጅ በናያህን “ሂድና ግደለው!” ብሎ ላከው። 30  ስለዚህ በናያህ ወደ ይሖዋ ድንኳን ሄዶ ኢዮዓብን “ንጉሡ ‘ና ውጣ!’ ብሎሃል” አለው። እሱ ግን “እዚሁ እሞታታለሁ እንጂ በፍጹም አልወጣም!” አለ። በዚህ ጊዜ በናያህ “ኢዮዓብ እንዲህ እንዲህ ብሏል፤ እንዲህም ሲል መልሶልኛል” በማለት ለንጉሡ ተናገረ። 31  ከዚያም ንጉሡ እንዲህ አለው፦ “በል ልክ እንዳለው አድርግ፤ ግደለውና ቅበረው፤ ኢዮዓብ አላግባብ ካፈሰሰውም ደም እኔንና የአባቴን ቤት አንጻ።+ 32  ኢዮዓብ አባቴ ዳዊት ሳያውቅ ከእሱ ይልቅ ጻድቅና የተሻሉ የነበሩትን ሁለት ሰዎች ማለትም የእስራኤል ሠራዊት አለቃ+ የነበረውን የኔርን ልጅ አበኔርንና+ የይሁዳ ሠራዊት አለቃ+ የነበረውን የየቴርን ልጅ አሜሳይን+ በሰይፍ መትቶ በመግደሉ ይሖዋ ደሙን በራሱ ላይ ይመልስበታል። 33  ደማቸውም ለዘላለም በኢዮዓብ ራስና በዘሮቹ ራስ ላይ ይሆናል፤+ በዳዊት፣ በዘሮቹ፣ በቤቱና በዙፋኑ ላይ ግን የይሖዋ ሰላም ለዘላለም ይሁን።” 34  ከዚያም የዮዳሄ ልጅ በናያህ ወጥቶ ኢዮዓብን መትቶ ገደለው፤ እሱም በምድረ በዳ በሚገኘው በራሱ ቤት ተቀበረ። 35  ከዚያም ንጉሡ በኢዮዓብ ምትክ የዮዳሄን ልጅ በናያህን+ በሠራዊቱ ላይ ሾመው፤ በአብያታር ቦታ ደግሞ ካህኑን ሳዶቅን+ ሾመው። 36  ንጉሡም ሺምአይን+ አስጠርቶ እንዲህ አለው፦ “ኢየሩሳሌም ውስጥ ቤት ሠርተህ በዚያ ኑር፤ ከዚያም ወጥተህ ወደ ሌላ ቦታ አትሂድ። 37  ከዚያ ወጥተህ የቄድሮንን ሸለቆ+ የተሻገርክ ቀን ግን እንደምትሞት እወቅ። ደምህ በራስህ ላይ ይሆናል።” 38  ሺምአይም ንጉሡን “ጥሩ ሐሳብ ነው። አገልጋይህ፣ ጌታዬ ንጉሡ እንዳለው ያደርጋል” አለው። ስለሆነም ሺምአይ በኢየሩሳሌም ለብዙ ጊዜ ተቀመጠ። 39  ሆኖም ከሦስት ዓመት በኋላ ከሺምአይ ባሪያዎች መካከል ሁለቱ የጌት ንጉሥ ወደሆነው ወደ ማአካ ልጅ ወደ አንኩስ+ ኮበለሉ። ሺምአይም “ባሪያዎችህ ያሉት ጌት ነው” ተብሎ ሲነገረው 40  ወዲያውኑ አህያውን ጭኖ ባሪያዎቹን ለመፈለግ በጌት ወዳለው ወደ አንኩስ አቀና። ሺምአይ ባሪያዎቹን ይዞ ከጌት ሲመለስ 41  ለሰለሞን “ሺምአይ ከኢየሩሳሌም ወጥቶ ወደ ጌት ሄዶ ነበር፤ አሁን ግን ተመልሷል” ተብሎ ተነገረው። 42  በዚህ ጊዜ ንጉሡ ሺምአይን አስጠርቶ እንዲህ አለው፦ “‘ከዚህ ወጥተህ ወደ ሌላ ቦታ በሄድክ ቀን እንደምትሞት እወቅ’ ብዬ በይሖዋ አስምዬህና አስጠንቅቄህ አልነበረም? አንተስ ብትሆን ‘ጥሩ ሐሳብ ነው፤ እንዳልከኝ አደርጋለሁ’ ብለኸኝ አልነበረም?+ 43  ታዲያ በይሖዋ ፊት የገባኸውን መሐላና የሰጠሁህን ትእዛዝ ያልጠበቅከው ለምንድን ነው?” 44  ከዚያም ንጉሡ፣ ሺምአይን እንዲህ አለው፦ “በአባቴ በዳዊት ላይ ያደረግከውን ክፉ ነገር ሁሉ ልብህ ያውቀዋል፤+ ይሖዋም ያደረግከውን ክፉ ነገር በራስህ ላይ ይመልስብሃል።+ 45  ንጉሥ ሰለሞን ግን ይባረካል፤+ የዳዊትም ዙፋን በይሖዋ ፊት ለዘላለም ይጸናል።” 46  ከዚያም ንጉሡ የዮዳሄን ልጅ በናያህን አዘዘው፤ እሱም ወጥቶ ሺምአይን መትቶ ገደለው።+ በዚህ መንገድ መንግሥቱ በሰለሞን እጅ ጸና።+

የግርጌ ማስታወሻ

ቃል በቃል “የምድርን ሁሉ መንገድ ልሄድ ነው።”
ወይም “ሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “ሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ቃል በቃል “ፊታቸውን ወደ እኔ አቅንተው እንደነበር።”
ወይም “የጠየቀው በገዛ ነፍሱ ፈርዶ ካልሆነ።”
ወይም “ሥርወ መንግሥት ባቋቋመልኝ።”
ወይም “አዶንያስ ላይ ወደቀበት።”