አንደኛ ዜና መዋዕል 12:1-40

  • የዳዊት ደጋፊዎች (1-40)

12  ዳዊት ከቂስ ልጅ ከሳኦል የተነሳ ተደብቆ ይኖር+ በነበረበት ጊዜ እሱ ወዳለበት ወደ ጺቅላግ+ የመጡት ሰዎች እነዚህ ናቸው፤ እነሱም በጦርነት ከረዱት ኃያላን ተዋጊዎች መካከል ነበሩ።+  ቀስት የታጠቁ ነበሩ፤ በቀኝ እጃቸውም ሆነ በግራ እጃቸው+ ድንጋይ መወንጨፍ+ ወይም ፍላጻ ማስፈንጠር ይችሉ ነበር። እነሱ ከቢንያም ነገድ+ ሲሆኑ የሳኦል ወንድሞች ነበሩ።  መሪያቸው አሂዔዜር ሲሆን ከእሱ ጋር ዮአስ ነበር፤ ሁለቱም የጊብዓዊው+ የሸማህ ወንዶች ልጆች ነበሩ፤ ደግሞም የአዝማዌት ወንዶች ልጆች የዚኤል እና ጴሌጥ፣ ቤራካ፣ አናቶታዊው+ ኢዩ፣  ከሠላሳዎቹ አለቆች+ መካከል ኃያል ተዋጊና የሠላሳዎቹ መሪ የሆነው ገባኦናዊው+ ይሽማያህ፤ በተጨማሪም ኤርምያስ፣ ያሃዚኤል፣ ዮሃናን፣ ገዴራዊው ዮዛባድ፣  ኤልዑዛይ፣ የሪሞት፣ በአልያህ፣ ሸማርያህ፣ ሃሪፋዊው ሰፋጥያህ፣  ቆሬያውያን+ የሆኑት ሕልቃና፣ ይሽሺያህ፣ አዛርዔል፣ ዮኤዘር፣ ያሾብአም፤  የጌዶር ሰው የሆነው የየሮሃም ወንዶች ልጆች ዮኤላ እና ዘባድያህ ነበሩ።  አንዳንድ ጋዳውያን ዳዊት ወዳለበት በምድረ በዳ ወደሚገኘው ምሽግ+ መጥተው ከእሱ ጎን ተሰለፉ፤ እነሱም ኃያላን ተዋጊዎችና ለጦርነት የሠለጠኑ ወታደሮች ሲሆኑ ትልቅ ጋሻና ረጅም ጦር ታጥቀው የሚጠባበቁ ነበሩ፤ ፊታቸው እንደ አንበሳ ፊት ነበር፤ በተራሮችም ላይ እንደ ሜዳ ፍየል ፈጣኖች ነበሩ።  ኤጼር መሪ ነበር፤ ሁለተኛው አብድዩ፣ ሦስተኛው ኤልያብ፣ 10  አራተኛው ሚሽማና፣ አምስተኛው ኤርምያስ፣ 11  ስድስተኛው አታይ፣ ሰባተኛው ኤሊዔል፣ 12  ስምንተኛው ዮሃናን፣ ዘጠነኛው ኤልዛባድ፣ 13  አሥረኛው ኤርምያስ፣ አሥራ አንደኛው ማክባናይ ነበሩ። 14  እነዚህ የሠራዊቱ መሪዎች የሆኑ ጋዳውያን+ ነበሩ። ታናሽ የሆነው 100 ወታደሮችን፣ ታላቅ የሆነውም 1,000 ወታደሮችን ይቋቋም ነበር።+ 15  በመጀመሪያው ወር ዮርዳኖስ ከአፍ እስከ ገደፉ ሞልቶ እየፈሰሰ ሳለ፣ ወንዙን አቋርጠው በቆላው የሚኖሩትን ሰዎች ሁሉ ወደ ምሥራቅና ወደ ምዕራብ ያባረሩት እነዚህ ነበሩ። 16  በተጨማሪም ከቢንያምና ከይሁዳ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ዳዊት ወደሚኖርበት ወደ ምሽጉ መጡ።+ 17  ዳዊትም ወደ እነሱ ወጥቶ እንዲህ አላቸው፦ “የመጣችሁት በሰላም ከሆነና እኔን ለመርዳት ከሆነ ልቤ ከእናንተ ጋር አንድ ይሆናል። ሆኖም እጄ ከበደል ንጹሕ ሆኖ ሳለ ለጠላቶቼ አሳልፋችሁ ልትሰጡኝ ከሆነ የአባቶቻችን አምላክ ጉዳዩን አይቶ ይፍረድ።”+ 18  ከዚያም የሠላሳዎቹ መሪ በሆነው በአማሳይ ላይ መንፈስ ወረደበት፤*+ እሱም እንዲህ አለ፦ “ዳዊት ሆይ፣ እኛ የአንተ ነን፤ የእሴይ ልጅ ሆይ፣ እኛ ከአንተ ጋር ነን።+ ሰላም፣ አዎ ሰላም ለአንተ ይሁን፤ አንተን ለሚረዳም ሰላም ይሁን፤አምላክህ እየረዳህ ነውና።”+ ስለዚህ ዳዊት ተቀበላቸው፤ በሠራዊቱም መሪዎች መካከል ሾማቸው። 19  ከምናሴ ነገድ የሆኑ አንዳንድ ሰዎችም ከድተው ወደ እሱ መጡ፤ በዚህ ጊዜ ዳዊት ከፍልስጤማውያን ጋር ሆኖ ሳኦልን ለመውጋት ወጥቶ ነበር፤ ሆኖም ፍልስጤማውያንን አልረዳቸውም፤ ምክንያቱም የፍልስጤም ገዢዎች+ ከተመካከሩ በኋላ “ከድቶ ወደ ጌታው ወደ ሳኦል በመሄድ እኛን ያስጨርሰናል”+ ሲሉ መልሰውት ነበር። 20  ዳዊት ወደ ጺቅላግ+ በሄደ ጊዜ ከምናሴ ነገድ ከድተው ወደ እሱ የመጡት አድናህ፣ ዮዛባድ፣ የዲአዔል፣ ሚካኤል፣ ዮዛባድ፣ ኤሊሁ እና ጺለታይ ሲሆኑ እነሱም ከምናሴ ነገድ የሆኑ የሺህ አለቆች ነበሩ።+ 21  ሁሉም ኃያልና ደፋር+ ስለነበሩ ዳዊት ከወራሪ ኃይሎች ጋር በሚያደርገው ውጊያ ረዱት። ከዚያም በሠራዊቱ ውስጥ አለቆች ሆኑ። 22  ሠራዊቱም እንደ አምላክ ሠራዊት ታላቅ እስኪሆን ድረስ፣ ዳዊትን ለመርዳት በየዕለቱ ብዙ ሰዎች ይጎርፉ ነበር።+ 23  በይሖዋ ትእዛዝ መሠረት የሳኦልን ንግሥና ወደ ዳዊት ለማስተላለፍ በኬብሮን+ ወደሚገኘው ወደ ዳዊት የመጡት ለውጊያ የታጠቁ መሪዎች ቁጥር ይህ ነው።+ 24  ትልቅ ጋሻና ረጅም ጦር የያዙ ለውጊያ የታጠቁ የይሁዳ ሰዎች 6,800 ነበሩ። 25  ከስምዖናውያን መካከል ከሠራዊቱ ጋር የተቀላቀሉ 7,100 ኃያልና ደፋር ሰዎች ነበሩ። 26  ከሌዋውያን 4,600 ነበሩ። 27  ዮዳሄ+ የአሮን ልጆች+ መሪ የነበረ ሲሆን ከእሱም ጋር 3,700 ሰዎች ነበሩ፤ 28  በተጨማሪም ሳዶቅ+ የተባለው ኃያልና ደፋር ወጣት ከአባቶቹ ቤት ከተውጣጡ 22 አለቆች ጋር መጣ። 29  የሳኦል ወንድሞች ከሆኑት ቢንያማውያን+ መካከል 3,000 ነበሩ፤ ቀደም ሲል ብዙዎቹ የሳኦልን ቤት በታማኝነት ይደግፉ ነበር። 30  ከኤፍሬማውያን መካከል ከአባቶቻቸው ቤት የተውጣጡ 20,800 ኃያል፣ ደፋርና ስመ ጥር ሰዎች ነበሩ። 31  ከምናሴ ነገድ እኩሌታ ዳዊትን ለማንገሥ የመጡ በስም የተጠቀሱ 18,000 ሰዎች ነበሩ። 32  ከይሳኮር ነገድ መካከል ዘመኑን ያስተዋሉና እስራኤል ምን ማድረግ እንዳለበት የተገነዘቡ 200 መሪዎች ነበሩ፤ ወንድሞቻቸውም ሁሉ እነሱን ይታዘዙ ነበር። 33  ከዛብሎን ነገድ በሠራዊቱ ውስጥ ማገልገል የሚችሉ፣ ለውጊያ ዝግጁ የሆኑና ልዩ ልዩ ዓይነት መሣሪያዎች የታጠቁ 50,000 ሰዎች ነበሩ፤ ሁሉም ወደ ዳዊት የመጡት በፍጹም ታማኝነት ነበር።* 34  ከንፍታሌም ነገድ 1,000 አለቆች ነበሩ፤ ከእነሱም ጋር ትልቅ ጋሻና ጦር የያዙ 37,000 ሰዎች ነበሩ። 35  ከዳናውያን ለጦርነት ዝግጁ የሆኑ 28,600 ሰዎች ነበሩ። 36  ከአሴር ነገድ ደግሞ ለጦርነት ዝግጁ ሆነው በሠራዊቱ ውስጥ ማገልገል የሚችሉ 40,000 ሰዎች ነበሩ። 37  ከዮርዳኖስ ወንዝ ማዶ+ ካሉት ከሮቤላውያን፣ ከጋዳውያንና ከምናሴ ነገድ እኩሌታ ለጦርነት የሚያስፈልጉ የተለያዩ መሣሪያዎችን የታጠቁ 120,000 ወታደሮች ነበሩ። 38  እነዚህ ሁሉ በአንድነት ለውጊያ የተሰለፉና ለጦርነት ዝግጁ የሆኑ ወታደሮች ነበሩ፤ ዳዊትን በመላው እስራኤል ላይ ለማንገሥ በአንድ ልብ ሆነው ወደ ኬብሮን መጡ፤ በተጨማሪም የቀረው የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ በአንድ ልብ ሆኖ ዳዊትን ለማንገሥ ተነሳ።+ 39  ወንድሞቻቸው አዘጋጅተውላቸው ስለነበር በዚያ እየበሉና እየጠጡ ከዳዊት ጋር ሦስት ቀን ቆዩ። 40  በተጨማሪም በአቅራቢያቸው ያሉትም ሆኑ እስከ ይሳኮር፣ ዛብሎንና ንፍታሌም ድረስ ርቀው የሚገኙት ሰዎች በአህያ፣ በግመል፣ በበቅሎና በከብት ምግብ ጭነው መጡ፤ ይኸውም ከፍተኛ መጠን ያለው ዱቄት፣ የበለስና የዘቢብ ጥፍጥፍ፣ የወይን ጠጅ፣ ዘይት፣ ከብትና በግ ነበር፤ በእስራኤል ታላቅ ደስታ ሰፍኖ ነበርና።

የግርጌ ማስታወሻ

ቃል በቃል “ለበሰ።”
ወይም “ከዳዊት ጋር ያበሩት ሰዎች ሁሉ መንታ ልብ አልነበራቸውም።”