አንደኛ ዜና መዋዕል 13:1-14

  • ታቦቱ ከቂርያትየአሪም መጣ (1-14)

    • ዖዛ ተቀሰፈ (9, 10)

13  ዳዊት ከሺህ አለቆቹና ከመቶ አለቆቹ እንዲሁም ከመሪዎቹ ሁሉ ጋር ተማከረ።+  ከዚያም ዳዊት ለመላው የእስራኤል ጉባኤ እንዲህ አለ፦ “ነገሩ መልካም መስሎ ከታያችሁና በአምላካችን በይሖዋ ፊት ተቀባይነት ያለው ከሆነ፣ በእስራኤል ምድር ሁሉ ያሉት የቀሩት ወንድሞቻችን እንዲሁም የግጦሽ መሬቶች ባሏቸው ከተሞቻቸው የሚኖሩት ካህናትና ሌዋውያን+ ወደ እኛ እንዲሰበሰቡ መልእክት እንላክባቸው።  የአምላካችንንም ታቦት መልሰን እናምጣ።”+ በሳኦል ዘመን ታቦቱን ችላ ብለውት ነበርና።+  ነገሩ በሕዝቡ ሁሉ ፊት መልካም ሆኖ ስለተገኘ መላው ጉባኤ ይህን ለማድረግ ተስማማ።  በመሆኑም ዳዊት የእውነተኛውን አምላክ ታቦት ከቂርያትየአሪም ለማምጣት ከግብፅ ወንዝ* አንስቶ እስከ ሌቦሃማት*+ ድረስ ያለውን የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ሰበሰበ።+  ዳዊትና መላው የእስራኤል ሕዝብ ከኪሩቤል በላይ* በዙፋን የሚቀመጠውን+ የእውነተኛውን አምላክ ታቦት ይኸውም ሰዎች የይሖዋን ስም የሚጠሩበትን ታቦት ለማምጣት በይሁዳ ምድር ወደምትገኘው ቂርያትየአሪም ወደምትባለው ወደ ባዓላ+ ወጡ።  ይሁን እንጂ የእውነተኛውን አምላክ ታቦት በአዲስ ሠረገላ ላይ ጭነው+ ከአቢናዳብ ቤት አመጡት፤ ደግሞም ዖዛና አሂዮ ሠረገላውን እየነዱ ነበር።+  ዳዊትና መላው የእስራኤል ሕዝብ በመዝሙር፣ በበገና፣ በባለ አውታር መሣሪያዎች፣ በአታሞ፣+ በሲምባልና*+ በመለከት+ ታጅበው በሙሉ ኃይላቸው በእውነተኛው አምላክ ፊት በደስታ ይጨፍሩ ነበር።  ወደ ኪዶን አውድማ ሲደርሱ ግን ከብቶቹ ታቦቱን ሊጥሉት ተቃርበው ስለነበር ዖዛ እጁን ዘርግቶ ታቦቱን ያዘ። 10  በዚህ ጊዜ የይሖዋ ቁጣ በዖዛ ላይ ነደደ፤ ታቦቱን ለመያዝ እጁን በመዘርጋቱም ቀሰፈው፤+ እሱም በአምላክ ፊት እዚያው ሞተ።+ 11  ሆኖም የይሖዋ ቁጣ በዖዛ ላይ ስለነደደ ዳዊት ተበሳጨ፤* ያም ቦታ እስከ ዛሬ ድረስ ጴሬዝዖዛ* ተብሎ ይጠራል። 12  ዳዊትም በዚያን ዕለት እውነተኛውን አምላክ ፈርቶ “ታዲያ የእውነተኛውን አምላክ ታቦት እንዴት ወደ እኔ ማምጣት እችላለሁ?” አለ።+ 13  ዳዊት ታቦቱን እሱ ወዳለበት ወደ ዳዊት ከተማ አላመጣውም፤ ይልቁንም የጌት ሰው ወደሆነው ወደ ኦቤድዔዶም ቤት እንዲወሰድ አደረገ። 14  የእውነተኛው አምላክ ታቦት ከኦቤድዔዶም ቤተሰብ ጋር በቤቱ ለሦስት ወራት ያህል ተቀመጠ፤ ይሖዋም የኦቤድዔዶምን ቤተሰብና ያለውን ሁሉ ባረከ።+

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ከሺሆር።”
ወይም “እስከ ሃማት መግቢያ።”
“በኪሩቤል መካከል” ማለትም ሊሆን ይችላል።
እዚህ ላይ የገባው የዕብራይስጥ ቃል፣ እርስ በርሱ ሲጋጭ ኃይለኛ ድምፅ የሚያወጣን ክብ ቅርጽ ያለው ከብረት የተሠራ የሙዚቃ መሣሪያ ያመለክታል።
ወይም “አዘነ።”
“በዖዛ ላይ መገንፈል” የሚል ትርጉም አለው።