አንደኛ ዜና መዋዕል 14:1-17

  • የዳዊት ንግሥና ጸና (1, 2)

  • የዳዊት ቤተሰብ (3-7)

  • ፍልስጤማውያን ድል ተመቱ (8-17)

14  የጢሮስ ንጉሥ ኪራም+ ለዳዊት ቤት* እንዲሠሩለት መልእክተኞችን እንዲሁም የአርዘ ሊባኖስ ሳንቃዎችን፣ ድንጋይ ጠራቢዎችንና* አናጺዎችን ላከ።+  ዳዊትም ይሖዋ በእስራኤል ላይ ንጉሥ አድርጎ እንዳጸናው አወቀ፤+ ምክንያቱም አምላክ ስለ ሕዝቡ ስለ እስራኤል ሲል ንግሥናውን ከፍ ከፍ አድርጎለት ነበር።+  ዳዊት በኢየሩሳሌም ተጨማሪ ሚስቶች አገባ፤+ ደግሞም ተጨማሪ ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ወለደ።+  በኢየሩሳሌም ሳለ የተወለዱለት ልጆች ስም ይህ ነው፦+ ሻሙአ፣ ሾባብ፣ ናታን፣+ ሰለሞን፣+  ይብሃር፣ ኤሊሹዓ፣ ኤልፔሌት፣  ኖጋ፣ ኔፌግ፣ ያፊአ፣  ኤሊሻማ፣ ቤኤልያዳ እና ኤሊፌሌት።  ፍልስጤማውያንም በሙሉ ዳዊት በመላው እስራኤል ላይ ንጉሥ ሆኖ መቀባቱን+ ሲሰሙ እሱን ፍለጋ ወጡ።+ ዳዊትም ይህን በሰማ ጊዜ ሊገጥማቸው ወጣ።  ከዚያም ፍልስጤማውያን መጥተው በረፋይም ሸለቆ* ወረራ አካሄዱ።+ 10  ዳዊትም “ወጥቼ ፍልስጤማውያንን ልግጠም? በእጄ አሳልፈህ ትሰጣቸዋለህ?” ሲል አምላክን ጠየቀ። ይሖዋም “አዎ ውጣ፤ እኔም በእርግጥ በእጅህ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ” አለው።+ 11  በመሆኑም ዳዊት ወደ በዓልጰራጺም+ ወጥቶ በዚያ መታቸው። ከዚያም ዳዊት “እውነተኛው አምላክ፣ ውኃ እንደጣሰው ግድብ ጠላቶቼን በእጄ ደረማመሳቸው” አለ። ከዚህም የተነሳ ያን ቦታ በዓልጰራጺም* ብለው ጠሩት። 12  ፍልስጤማውያንም አማልክታቸውን በዚያ ጥለው ሸሹ፤ ዳዊት በሰጠው መመሪያ መሠረትም በእሳት አቃጠሏቸው።+ 13  ከጊዜ በኋላ ፍልስጤማውያን ሸለቆውን* እንደገና ወረሩ።+ 14  ዳዊት ዳግመኛ አምላክን ጠየቀ፤ ሆኖም እውነተኛው አምላክ እንዲህ አለው፦ “እነሱን ለመግጠም በቀጥታ አትውጣ። ይልቁንም ከኋላቸው ዙርና በባካ* ቁጥቋጦዎቹ ፊት መጥተህ ግጠማቸው።+ 15  ደግሞም በባካ ቁጥቋጦዎቹ አናት ላይ የሰልፍ ድምፅ ስትሰማ ጥቃት ሰንዝር፤ ምክንያቱም ይህ በሚሆንበት ጊዜ እውነተኛው አምላክ የፍልስጤማውያንን ሠራዊት ለመምታት በፊትህ ወጥቷል ማለት ነው።”+ 16  ስለዚህ ዳዊት ልክ እውነተኛው አምላክ እንዳዘዘው አደረገ፤+ የፍልስጤማውያንንም ሠራዊት ከገባኦን አንስቶ እስከ ጌዜር+ ድረስ መቷቸው። 17  የዳዊትም ዝና በአገሩ ሁሉ ተሰማ፤ ይሖዋም ብሔራት ሁሉ እንዲፈሩት አደረገ።+

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ቤተ መንግሥት።”
ወይም “ቅጥር የሚሠሩ ግንበኞችንና።”
ወይም “ረባዳማ ሜዳ።”
“በመደረማመስ የተዋጣለት” የሚል ትርጉም አለው።
ወይም “ረባዳማውን ሜዳ።”
“ባካ” የሚለው ስም የዕብራይስጥ ቃል ነው። የተክሉ ዓይነት በትክክል አይታወቅም።