አንደኛ ዜና መዋዕል 19:1-19

  • አሞናውያን የዳዊትን መልእክተኞች አዋረዷቸው (1-5)

  • በአሞናውያንና በሶርያውያን ላይ የተገኘ ድል (6-19)

19  ከጊዜ በኋላ የአሞናውያን ንጉሥ ናሃሽ ሞተ፤ በእሱም ፋንታ ልጁ ነገሠ።+  በዚህ ጊዜ ዳዊት “አባቱ ታማኝ ፍቅር+ ስላሳየኝ እኔም ለናሃሽ ልጅ ለሃኑን ታማኝ ፍቅር አሳየዋለሁ” አለ። በመሆኑም ዳዊት በአባቱ ሞት ከደረሰበት ሐዘን እንዲያጽናኑት መልእክተኞችን ላከ። ሆኖም የዳዊት አገልጋዮች ሃኑንን ለማጽናናት ወደ አሞናውያን+ ምድር ሲደርሱ  የአሞናውያን መኳንንት ሃኑንን እንዲህ አሉት፦ “ዳዊት አጽናኞችን ወደ አንተ የላከው አባትህን አክብሮ ይመስልሃል? አገልጋዮቹ ወደ አንተ የመጡት ምድሪቱን በሚገባ ለማጥናትና በውስጧ ያለውን ነገር ለመሰለል እንዲሁም አንተን ለመገልበጥ አይደለም?”  በመሆኑም ሃኑን የዳዊትን አገልጋዮች ወስዶ ላጫቸው፤+ ልብሳቸውንም እስከ መቀመጫቸው ድረስ አሳጥሮ በመቁረጥ መልሶ ላካቸው።  በአገልጋዮቹ ላይ የደረሰውን ነገር ለዳዊት በነገሩት ጊዜ ሰዎቹ በኀፍረት ተውጠው ስለነበር ዳዊት ወዲያውኑ መልእክተኞችን ወደ እነሱ ላከ፤ ንጉሡም “ጢማችሁ እስኪያድግ ድረስ በኢያሪኮ+ ቆዩ፤ ከዚያ በኋላ ተመለሱ” አላቸው።  ውሎ አድሮ አሞናውያን በዳዊት ዘንድ እንደ ጥንብ እንደተቆጠሩ ተገነዘቡ፤ በመሆኑም ሃኑን እና አሞናውያን ከሜሶጶጣሚያ፣* ከአራምመዓካና ከጾባህ+ ሠረገሎችንና ፈረሰኞችን ለመቅጠር 1,000 የብር ታላንት* ላኩ።  በዚህ መንገድ 32,000 ሠረገሎችን፣ የማአካን ንጉሥና ሕዝቡን ለራሳቸው ቀጠሩ። እነሱም መጥተው በመደባ+ ፊት ለፊት ሰፈሩ። አሞናውያን ደግሞ ከየከተሞቻቸው ተሰብስበው ለጦርነት መጡ።  ዳዊት ይህን በሰማ ጊዜ ኢዮአብን+ እንዲሁም እጅግ ኃያላን የሆኑትን ተዋጊዎቹን ጨምሮ መላውን ሠራዊት ላከ።+  አሞናውያንም ወጥተው በከተማዋ መግቢያ ላይ ለውጊያ ተሰለፉ፤ የመጡት ነገሥታት ደግሞ ለብቻቸው ሜዳ ላይ ተሰለፉ። 10  ኢዮዓብ ወታደሮቹ ከፊትና ከኋላ ጥቃት ለመሰንዘር ወደ እሱ እየገሰገሱ መምጣታቸውን ሲያይ በእስራኤል ካሉት ምርጥ የሆኑ ተዋጊዎች መካከል የተወሰኑትን መርጦ ሶርያውያንን እንዲገጥሙ አሰለፋቸው።+ 11  የቀሩትን ሰዎች ደግሞ በወንድሙ በአቢሳ+ አመራር ሥር* ሆነው አሞናውያንን እንዲገጥሙ አሰለፋቸው። 12  ከዚያም እንዲህ አለው፦ “ሶርያውያን+ ከበረቱብኝ አንተ ትደርስልኛለህ፤ አሞናውያን ከበረቱብህ ደግሞ እኔ እደርስልሃለሁ። 13  ለሕዝባችንና ለአምላካችን ከተሞች ስንል ብርቱና ደፋር መሆን አለብን፤+ ይሖዋም በፊቱ መልካም የሆነውን ነገር ያደርጋል።” 14  ከዚያም ኢዮዓብና አብረውት የነበሩት ሰዎች ሶርያውያንን ለመግጠም ወደ እነሱ ሲገሰግሱ ሶርያውያኑ ከፊቱ ሸሹ።+ 15  አሞናውያንም ሶርያውያን እንደ ሸሹ ሲያዩ እነሱም ከወንድሙ ከአቢሳ ፊት ሸሽተው ወደ ከተማዋ ገቡ። ከዚያም ኢዮዓብ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ። 16  ሶርያውያን በእስራኤላውያን ድል እንደተመቱ ሲያዩ መልእክተኞች ልከው በወንዙ*+ አካባቢ የነበሩትን ሶርያውያን አስጠሩ፤ የሃዳድኤዜር ሠራዊት አለቃ የሆነውም ሾፋክ* ይመራቸው ነበር።+ 17  ዳዊት ወሬው በተነገረው ጊዜ ወዲያውኑ እስራኤልን ሁሉ ሰብስቦ ዮርዳኖስን በመሻገር ወደ እነሱ መጣ፤ ተዋጊዎቹንም በእነሱ ላይ አሰለፈ። ዳዊት ሶርያውያንን ለመግጠም ተዋጊዎቹን ባሰለፈ ጊዜ ከእሱ ጋር ተዋጉ።+ 18  ይሁንና ሶርያውያን ከእስራኤል ፊት ሸሹ፤ ዳዊትም ከሶርያውያን መካከል 7,000 ሠረገለኞችንና 40,000 እግረኛ ወታደሮችን ገደለ፤ የሠራዊቱ አዛዥ የሆነውን ሾፋክንም ገደለው። 19  የሃዳድኤዜር አገልጋዮች በእስራኤል እንደተሸነፉ+ ባዩ ጊዜ ወዲያውኑ ከዳዊት ጋር እርቅ በመፍጠር ለእሱ ተገዙ፤+ ሶርያም ከዚህ በኋላ አሞናውያንን ለመርዳት ፈቃደኛ አልሆነችም።

የግርጌ ማስታወሻ

ቃል በቃል “ከአራምናሃራይም።”
አንድ ታላንት 34.2 ኪሎ ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ቃል በቃል “እጅ።”
ኤፍራጥስን ያመለክታል።
በ2ሳሙ 10:16 ላይ ሾባክ ተብሎም ተጠርቷል።