የዮሐንስ የመጀመሪያው ደብዳቤ 4:1-21

  • በመንፈስ የተነገረን ቃል መመርመር (1-6)

  • አምላክን ማወቅና መውደድ (7-21)

    • “አምላክ ፍቅር ነው” (8, 16)

    • “በፍቅር ፍርሃት የለም” (18)

4  የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ በመንፈስ የተነገረን ቃል* ሁሉ አትመኑ፤+ ከዚህ ይልቅ በመንፈስ የተነገሩት ቃላት* ከአምላክ የመነጩ መሆን አለመሆናቸውን መርምሩ፤+ ብዙ ሐሰተኛ ነቢያት ወደ ዓለም ወጥተዋልና።+  በመንፈስ የተነገረው ቃል ከአምላክ የመነጨ መሆኑን በዚህ ማወቅ ትችላላችሁ፦ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደመጣ የሚመሠክር በመንፈስ የተነገረ ቃል ሁሉ ከአምላክ የመነጨ ነው።+  ሆኖም ስለ ኢየሱስ የማይመሠክር በመንፈስ የተነገረ ቃል ሁሉ ከአምላክ የሚመነጭ አይደለም።+ ይህ በመንፈስ የተነገረ ቃል ከፀረ ክርስቶስ የሚመነጭ ነው፤ ፀረ ክርስቶስ እንዲህ ያሉ ነገሮችን እንደሚናገር ሰምታችኋል፤+ አሁንም እንኳ ይህ ቃል በዓለም ላይ እየተነገረ ነው።+  ልጆቼ ሆይ፣ እናንተ ከአምላክ ወገን ናችሁ፤ እነሱንም* አሸንፋችኋል፤+ ምክንያቱም ከእናንተ ጎን ያለው፣+ ከዓለም ጎን ካለው ይበልጣል።+  እነሱ የዓለም ወገን ናቸው፤+ ከዓለም የሚመነጨውን ነገር የሚናገሩትና ዓለምም የሚሰማቸው ለዚህ ነው።+  እኛ ከአምላክ ወገን ነን። አምላክን የሚያውቅ ሁሉ ይሰማናል፤+ ከአምላክ ወገን ያልሆነ ሁሉ አይሰማንም።+ በመንፈስ የተነገረውን የእውነት ቃልና በመንፈስ የተነገረውን የስህተት ቃል ለይተን የምናውቀው በዚህ መንገድ ነው።+  የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ እርስ በርስ መዋደዳችንን እንቀጥል፤+ ምክንያቱም ፍቅር ከአምላክ ነው፤ ፍቅር የሚያሳይ ሁሉ ከአምላክ የተወለደ ሲሆን አምላክን ያውቃል።+  ፍቅር የማያሳይ አምላክን አያውቅም፤ ምክንያቱም አምላክ ፍቅር ነው።+  የአምላክ ፍቅር ከእኛ ሁኔታ ጋር በተያያዘ በዚህ መንገድ ተገልጧል፤ እኛ በእሱ አማካኝነት ሕይወት ማግኘት እንድንችል+ አምላክ አንድያ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታል።+ 10  ይህ ፍቅር የተገለጠው በዚህ መንገድ ነው፦ እኛ አምላክን ስለወደድነው ሳይሆን እሱ ስለወደደንና ለኃጢአታችን የማስተሰረያ መሥዋዕት* እንዲሆን+ ልጁን ስለላከ ነው።+ 11  የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ አምላክ የወደደን በዚህ መንገድ ከሆነ እኛም እርስ በርሳችን የመዋደድ ግዴታ አለብን።+ 12  መቼም ቢሆን አምላክን ያየው ማንም የለም።+ እርስ በርስ መዋደዳችንን ከቀጠልን አምላክ ከእኛ ጋር ይሆናል፤ ፍቅሩም በመካከላችን ፍጹም ይሆናል።+ 13  እሱ መንፈሱን ስለሰጠን እኛ ከእሱ ጋር አንድነት እንዳለንና እሱም ከእኛ ጋር አንድነት እንዳለው እናውቃለን። 14  ከዚህ በተጨማሪ አብ ልጁን የዓለም አዳኝ አድርጎ እንደላከው እኛ ራሳችን አይተናል፤ ደግሞም እየመሠከርን ነው።+ 15  ማንም ሰው ኢየሱስ የአምላክ ልጅ መሆኑን የሚመሠክር+ ከሆነ አምላክ እንዲህ ካለው ሰው ጋር አንድነት ይኖረዋል፤ እሱም ከአምላክ ጋር አንድነት ይኖረዋል።+ 16  ደግሞም አምላክ ለእኛ ያለውን ፍቅር አውቀናል፤ እንዲሁም አምነናል።+ አምላክ ፍቅር ነው፤+ በፍቅር የሚኖር ከአምላክ ጋር ያለውን አንድነት ጠብቆ ይኖራል፤ አምላክም ከእሱ ጋር አንድነት ይኖረዋል።+ 17  በመሆኑም በፍርድ ቀን የመናገር ነፃነት* ይኖረን ዘንድ+ ፍቅር በእኛ መካከል ፍጹም የሆነው በዚህ መንገድ ነው፤ ምክንያቱም በዚህ ዓለም ውስጥ እኛ ራሳችን እንደ እሱ* ነን። 18  በፍቅር ፍርሃት የለም፤+ እንዲያውም ፍጹም ፍቅር ፍርሃትን አውጥቶ ይጥላል፤* ምክንያቱም ፍርሃት ወደኋላ እንድንል ያደርገናል። ደግሞም የሚፈራ ሰው ፍጹም የሆነ ፍቅር የለውም።+ 19  እሱ አስቀድሞ ስለወደደን እኛም ፍቅር እናሳያለን።+ 20  ማንም “አምላክን እወደዋለሁ” እያለ ወንድሙን የሚጠላ ከሆነ ይህ ሰው ውሸታም ነው።+ ያየውን ወንድሙን የማይወድ+ ያላየውን አምላክ ሊወድ አይችልምና።+ 21  እሱም “አምላክን የሚወድ ሁሉ ወንድሙንም መውደድ ይገባዋል” የሚለውን ይህን ትእዛዝ ሰጥቶናል።+

የግርጌ ማስታወሻ

ቃል በቃል “መናፍስት።”
ቃል በቃል “መንፈስን።”
ይህ ቃል ሐሰተኛ ነቢያትን ያመለክታል።
ወይም “የእርቅ መሥዋዕት።”
ወይም “የመተማመን ስሜት።”
ኢየሱስ ክርስቶስን ያመለክታል።
ወይም “ያስወግዳል።”