ለጢሞቴዎስ የተጻፈ የመጀመሪያው ደብዳቤ 1:1-20

  • ሰላምታ (1, 2)

  • ሐሰተኛ አስተማሪዎችን በተመለከተ የተሰጠ ማስጠንቀቂያ (3-11)

  • አምላክ ለጳውሎስ ያሳየው ጸጋ (12-16)

  • የዘላለም ንጉሥ (17)

  • ‘መልካሙን ውጊያ መዋጋትህን ቀጥል’ (18-20)

1  አዳኛችን በሆነው አምላክና ተስፋችን+ በሆነው በክርስቶስ ኢየሱስ ትእዛዝ የክርስቶስ ኢየሱስ ሐዋርያ ከሆነው ከጳውሎስ፣  በእምነት እውነተኛ ልጄ+ ለሆነው ለጢሞቴዎስ፦*+ አባት ከሆነው አምላክና ከጌታችን ከክርስቶስ ኢየሱስ ጸጋ፣ ምሕረትና ሰላም ለአንተ ይሁን።  ወደ መቄዶንያ ልሄድ በተነሳሁበት ጊዜ በኤፌሶን እንድትቆይ እንዳበረታታሁህ ሁሉ አሁንም አንዳንዶች የሐሰት ትምህርት እንዳያስፋፉ ታዛቸው ዘንድ በዚያው እንድትቆይ አበረታታሃለሁ፤  በተጨማሪም ለፈጠራ ወሬዎችና+ ለትውልድ ሐረግ ቆጠራ ትኩረት እንዳይሰጡ እዘዛቸው። እንዲህ ያሉ ነገሮች ለግምታዊ ሐሳቦች በር ከመክፈት ውጭ የሚያስገኙት ፋይዳ የለም፤+ አምላክ እምነትን ለማጠናከር ከሚሰጠው ነገር ጋር ምንም ግንኙነት የላቸውም።  የዚህ ትእዛዝ* ዓላማ ከንጹሕ ልብ፣ ከጥሩ ሕሊናና ግብዝነት ከሌለበት እምነት+ የሚመነጭ ፍቅር+ እንዲኖረን ነው።  አንዳንዶች እነዚህን ነገሮች በመተው ፍሬ ቢስ ወደሆነ ወሬ ፊታቸውን አዙረዋል።+  የሕግ አስተማሪዎች+ መሆን ይፈልጋሉ፤ ሆኖም የሚናገሯቸውን ነገሮችም ሆነ አጥብቀው የሚሟገቱላቸውን ነገሮች አያስተውሉም።  አንድ ሰው በአግባቡ ሥራ ላይ እስካዋለው ድረስ ሕጉ መልካም ነው፤  ደግሞም ሕግ የሚወጣው ለጻድቅ ሰው ሳይሆን ሕግ ለሚተላለፉና+ ለዓመፀኞች፣ ፈሪሃ አምላክ ለሌላቸውና ለኃጢአተኞች፣ ታማኞች ላልሆኑና* ቅዱስ የሆነውን ለሚንቁ፣ አባትንና እናትን ለሚገድሉ እንዲሁም ለነፍሰ ገዳዮች መሆኑን መገንዘብ ይኖርበታል፤ 10  በተጨማሪም ለሴሰኞች፣* ግብረ ሰዶም ለሚፈጽሙ ወንዶች፣* ለአፋኞች፣ ለውሸታሞችና በሐሰት ለሚምሉ* እንዲሁም ትክክለኛውን* ትምህርት+ ለሚጻረሩ ነገሮች ሁሉ ነው፤ 11  ይህ ትምህርት ደስተኛው አምላክ ከገለጸው ክብራማ ምሥራች ጋር የሚስማማ ሲሆን እሱም ምሥራቹን በአደራ ሰጥቶኛል።+ 12  ለአገልግሎቱ በመሾም ታማኝ አድርጎ ስለቆጠረኝ ኃይል የሰጠኝን ጌታችን ክርስቶስ ኢየሱስን አመሰግናለሁ፤+ 13  ምንም እንኳ ቀደም ሲል አምላክን የምሳደብ፣ አሳዳጅና እብሪተኛ የነበርኩ ብሆንም ይህን አድርጎልኛል።+ ደግሞም ባለማወቅና ባለማመን ስላደረግኩት፣ ምሕረት ተደርጎልኛል። 14  የጌታችን ጸጋም ከእምነት እንዲሁም የክርስቶስ ኢየሱስ ተከታይ በመሆኔ ምክንያት ካገኘሁት ፍቅር ጋር እጅግ ተትረፍርፎልኛል። 15  ‘ክርስቶስ ኢየሱስ ኃጢአተኞችን ለማዳን+ ወደ ዓለም መጣ’ የሚለው ቃል እምነት የሚጣልበትና ሙሉ ተቀባይነት ሊያገኝ የሚገባው ነው። ከኃጢአተኞች ደግሞ እኔ ዋነኛ ነኝ።+ 16  ይሁንና ለእኔ ምሕረት የተደረገው ክርስቶስ ኢየሱስ፣ ዋነኛ ኃጢአተኛ የሆንኩትን እኔን ምሳሌ አድርጎ በመጠቀም የዘላለም ሕይወት ለማግኘት እምነታቸውን በእሱ ላይ ለሚጥሉ ሰዎች ትዕግሥቱን ሁሉ ያሳይ ዘንድ ነው።+ 17  እንግዲህ ለማይጠፋውና+ ለማይታየው፣+ እሱ ብቻ አምላክ ለሆነው+ ለዘላለሙ ንጉሥ+ ክብርና ግርማ ለዘላለም ይሁን። አሜን። 18  ልጄ ጢሞቴዎስ፣ ከዚህ ቀደም ስለ አንተ በተነገሩት ትንቢቶች መሠረት ይህን ትእዛዝ* በአደራ እሰጥሃለሁ፤ ይኸውም ከእነዚህ ጋር በሚስማማ መንገድ መልካሙን ውጊያ መዋጋትህን እንድትቀጥል ነው፤+ 19  ይህን የምታደርገው እምነትንና ጥሩ ሕሊናን+ አጥብቀህ በመያዝ ነው፤ አንዳንዶች ሕሊናቸውን ወደ ጎን ገሸሽ በማድረጋቸው ባሕር ላይ አደጋ ደርሶበት እንደተሰባበረ መርከብ እምነታቸው ጠፍቷል። 20  ከእነሱም መካከል ሄሜኔዎስና+ እስክንድር ይገኙበታል፤ እነሱ ከተግሣጽ ተምረው በአምላክ ላይ የስድብ ቃል ከመናገር እንዲቆጠቡ ለሰይጣን አሳልፌ ሰጥቻቸዋለሁ።*+

የግርጌ ማስታወሻ

“አምላክን የሚያከብር ሰው” የሚል ትርጉም አለው።
ወይም “መመሪያ።”
ወይም “ታማኝ ፍቅር ለሌላቸውና።”
ወይም “መሐላ ለሚያፈርሱ።”
ወይም “ጤናማውን፤ ጠቃሚውን።”
የቃላት መፍቻው ላይ “የፆታ ብልግና” የሚለውን ተመልከት።
ወይም “ከወንዶች ጋር የፆታ ግንኙነት ለሚፈጽሙ ወንዶች።” ቃል በቃል “ከወንዶች ጋር ለሚተኙ ወንዶች።”
ወይም “መመሪያ።”
ከጉባኤ መወገዳቸውን ያመለክታል።