ለጢሞቴዎስ የተጻፈ የመጀመሪያው ደብዳቤ 5:1-25

  • ወጣቶችንና አረጋውያንን በአግባቡ መያዝ (1, 2)

  • ለመበለቶች የሚሰጥ ድጋፍ (3-16)

    • ለቤተሰብ አባላት የሚያስፈልገውን ማቅረብ (8)

  • ተግተው የሚሠሩ ሽማግሌዎችን ማክበር (17-25)

    • ‘ለሆድህ ጥቂት የወይን ጠጅ ጠጣ’ (23)

5  ሽማግሌ የሆነውን በኃይለ ቃል አትናገረው።+ ከዚህ ይልቅ እንደ አባት ቆጥረህ በደግነት ምከረው፤ ወጣት ወንዶችን እንደ ወንድሞች፣  አሮጊቶችን እንደ እናቶች፣ ወጣት ሴቶችን ደግሞ እንደ እህቶች አድርገህ በፍጹም ንጽሕና ያዛቸው።  በእርግጥ መበለት ለሆኑ መበለቶች*+ አሳቢነት* አሳያቸው።  ሆኖም አንዲት መበለት ልጆች ወይም የልጅ ልጆች ካሏት እነዚህ ልጆች በመጀመሪያ በራሳቸው ቤተሰብ+ ውስጥ ለአምላክ የማደርን ባሕርይ ማንጸባረቅን እንዲሁም ለወላጆቻቸውና ለአያቶቻቸው የሚገባቸውን ብድራት መክፈልን ይማሩ፤+ ይህ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ነገር ነውና።+  በእርግጥ መበለት የሆነችና ምንም የሌላት ሴት ተስፋዋን በአምላክ ላይ ትጥላለች+ እንዲሁም ሌት ተቀን ያለማሰለስ ምልጃና ጸሎት ታቀርባለች።+  ለሥጋዊ ፍላጎቷ ያደረች መበለት ግን በሕይወት ብትኖርም የሞተች ናት።  ስለዚህ ከነቀፋ ነፃ መሆን ይችሉ ዘንድ እነዚህን መመሪያዎች* መስጠትህን ቀጥል።  በእርግጥም አንድ ሰው የራሱ ለሆኑት በተለይ ደግሞ ለቤተሰቡ አባላት የሚያስፈልጋቸውን ነገር የማያቀርብ ከሆነ እምነትን የካደ ከመሆኑም በላይ እምነት የለሽ ከሆነ ሰው የከፋ ነው።+  አንዲት መበለት ከ60 ዓመት በላይ ከሆነች በመዝገብ ላይ ትጻፍ፤ ደግሞም የአንድ ባል ሚስት የነበረች ልትሆን ይገባል፤ 10  እንዲሁም ልጆችን በማሳደግ፣+ እንግዶችን በመቀበል፣+ የቅዱሳንን እግር በማጠብ፣+ የተቸገሩትን በመርዳትና+ ማንኛውንም በጎ ተግባር በትጋት በማከናወን በመልካም ሥራ ጥሩ ስም ያተረፈች+ ልትሆን ይገባል። 11  በዕድሜ ያልገፉ መበለቶች ግን መዝገብ ላይ መጻፍ የለባቸውም፤ የፆታ ፍላጎታቸው በክርስቲያናዊ አገልግሎታቸው ላይ እንቅፋት በሚፈጥርበት ጊዜ ማግባት ይፈልጋሉና። 12  ደግሞም የመጀመሪያውን የእምነት ቃላቸውን* ስላፈረሱ በራሳቸው ላይ ፍርድ ያመጣሉ። 13  ከዚህ በተጨማሪ በየቤቱ እየዞሩ ሥራ ፈት ይሆናሉ፤ ሥራ ፈት መሆን ብቻ ሳይሆን ማውራት ስለማይገባቸው ነገሮች እያወሩ ሐሜተኞችና በሌሎች ሰዎች ጉዳይ ጣልቃ የሚገቡ ይሆናሉ።+ 14  ስለዚህ በዕድሜ ያልገፉ መበለቶች እንዲያገቡ፣+ ልጆች እንዲወልዱ፣+ ቤታቸውን እንዲያስተዳድሩና ተቃዋሚው ትችት ሊሰነዝር የሚችልበት አጋጣሚ እንዲያገኝ ከማድረግ እንዲቆጠቡ እፈልጋለሁ። 15  እንዲያውም አንዳንዶቹ ከዚህ በፊት ሰይጣንን ለመከተል ዞር ብለዋል። 16  አንዲት አማኝ የሆነች ሴት፣ መበለት የሆኑ ዘመዶች ቢኖሯት ጉባኤው ሸክም እንዳይበዛበት እሷ ትርዳቸው። በዚህ መንገድ ጉባኤው በእርግጥ መበለት የሆኑትን* መርዳት ይችላል።+ 17  በመልካም ሁኔታ የሚያስተዳድሩ+ በተለይ ደግሞ በመናገርና በማስተማር ተግተው የሚሠሩ+ ሽማግሌዎች እጥፍ ክብር ሊሰጣቸው ይገባል።+ 18  የቅዱስ መጽሐፉ ቃል “እህል እያበራየ ያለውን በሬ አፉን አትሰር”፤+ እንዲሁም “ለሠራተኛ ደሞዙ ይገባዋል” ይላልና።+ 19  በሁለት ወይም በሦስት ምሥክሮች+ ማስረጃ ካልሆነ በቀር በሽማግሌ ላይ የሚቀርብን ክስ አትቀበል። 20  ለሌሎቹ ማስጠንቀቂያ እንዲሆን* ኃጢአት የመሥራት ልማድ ያላቸውን ሰዎች+ በሁሉ ፊት ውቀሳቸው።+ 21  እነዚህን መመሪያዎች መሠረተ ቢስ ከሆነ ጥላቻና ከአድልዎ በራቀ መንገድ እንድትጠብቅ በአምላክ፣ በክርስቶስ ኢየሱስና በተመረጡት መላእክት ፊት በጥብቅ አዝሃለሁ።+ 22  በማንም ሰው ላይ እጅህን ለመጫን አትቸኩል፤*+ እንዲሁም በሌሎች ኃጢአት ተካፋይ አትሁን፤ ራስህን በንጽሕና ጠብቅ። 23  ከእንግዲህ ውኃ አትጠጣ፤* ከዚህ ይልቅ ለሆድህና በተደጋጋሚ ለሚነሳብህ ሕመም ጥቂት የወይን ጠጅ ጠጣ። 24  የአንዳንድ ሰዎች ኃጢአት በይፋ የታወቀ ስለሚሆን ወዲያውኑ ፍርድ ያስከትላል፤ የሌሎቹ ሰዎች ኃጢአት ደግሞ ውሎ አድሮ መታወቁ አይቀርም።+ 25  በተመሳሳይም መልካም ሥራዎች በይፋ የታወቁ ናቸው፤+ በይፋ ያልታወቁትም ቢሆኑ ተደብቀው ሊቀሩ አይችሉም።+

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “በእርግጥ ለተቸገሩ መበለቶች።” ረዳት የሌላቸውን መበለቶች ያመለክታል።
ቃል በቃል “አክብሮት።”
ወይም “ትእዛዛት።”
ወይም “በፊት የገቡትን ቃል።”
ወይም “በእርግጥ የተቸገሩ መበለቶችን።” ረዳት የሌላቸውን መበለቶች ያመለክታል።
ቃል በቃል “ሌሎቹ እንዲፈሩ።”
ማንኛውንም ሰው ለመሾም አትቸኩል ማለት ነው።
ወይም “ውኃ ብቻ አትጠጣ።”