ለጢሞቴዎስ የተጻፈ የመጀመሪያው ደብዳቤ 6:1-21

  • ባሮች ጌቶቻቸውን ያክብሩ (1, 2)

  • የሐሰት አስተማሪዎችና የገንዘብ ፍቅር (3-10)

  • ለአምላክ ሰው የተሰጠ መመሪያ (11-16)

  • በመልካም ሥራዎች ባለጸጋ ሁኑ (17-19)

  • “በአደራ የተሰጠህን ነገር ጠብቅ” (20, 21)

6  የአምላክ ስምና ትምህርት ፈጽሞ እንዳይሰደብ በባርነት ቀንበር ሥር ያሉ ሁሉ ጌቶቻቸው ሙሉ ክብር እንደሚገባቸው ይገንዘቡ።+  በተጨማሪም አማኝ የሆኑ ጌቶች ያሏቸው ባሪያዎች፣ ጌቶቻቸው ወንድሞች ስለሆኑ ብቻ አክብሮት አይንፈጓቸው። ከዚህ ይልቅ እነሱ ከሚሰጡት ጥሩ አገልግሎት እየተጠቀሙ ያሉት፣ የእምነት ባልንጀሮቻቸውና የተወደዱ ወንድሞቻቸው ስለሆኑ ይበልጥ በትጋት ያገልግሏቸው። እነዚህን ነገሮች ማስተማርህንና እነዚህን ማሳሰቢያዎች መስጠትህን ቀጥል።  አንድ ሰው የተለየ ትምህርት ቢያስተምርና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ካስተማረው ትክክለኛ* ትምህርትም+ ሆነ ለአምላክ ማደርን ከሚያበረታታው ትምህርት+ ጋር የማይስማማ ቢሆን  ይህ ሰው በትዕቢት የተወጠረና ምንም የማያስተውል ነው።+ ስለ ቃላት የመጨቃጨቅና የመከራከር አባዜ* የተጠናወተው ነው።+ እንዲህ ያሉ ነገሮች ቅናት፣ ጠብ፣ ስም ማጥፋትና* መጥፎ ጥርጣሬ ያስከትላሉ፤  በተጨማሪም ለአምላክ ማደር ጥቅም ማግኛ እንደሆነ አድርገው በሚያስቡ፣+ አእምሯቸው በተበላሸና+ እውነትን መረዳት ባቆሙ ሰዎች መካከል ተራ በሆኑ ጉዳዮች የማያባራ ጭቅጭቅ ያስነሳሉ።  እንደ እውነቱ ከሆነ ለአምላክ ያደርን+ መሆናችንና ባለን ነገር ረክተን መኖራችን ትልቅ ጥቅም ያስገኛል።  ወደ ዓለም ያመጣነው ምንም ነገር የለምና፤ ምንም ነገር ይዘን መሄድም አንችልም።+  ስለዚህ ምግብና ልብስ* ካለን በእነዚህ ነገሮች ረክተን መኖር ይገባናል።+  ሀብታም ለመሆን ቆርጠው የተነሱ ግን ፈተናና ወጥመድ+ ውስጥ ይወድቃሉ፤ እንዲሁም ሰዎችን ጥፋትና ብልሽት ውስጥ በሚዘፍቁ ከንቱና ጎጂ በሆኑ ብዙ ምኞቶች ይያዛሉ።+ 10  የገንዘብ ፍቅር የብዙ ዓይነት ጎጂ ነገሮች ሥር ነውና፤ አንዳንዶች በዚህ ፍቅር ተሸንፈው ከእምነት ጎዳና ስተው ወጥተዋል፤ እንዲሁም ሁለንተናቸውን በብዙ ሥቃይ ወግተዋል።+ 11  የአምላክ ሰው ሆይ፣ አንተ ግን ከእነዚህ ነገሮች ሽሽ። ከዚህ ይልቅ ጽድቅን፣ ለአምላክ ማደርን፣ እምነትን፣ ፍቅርን፣ ጽናትንና ገርነትን+ ተከታተል። 12  መልካሙን የእምነት ገድል ተጋደል፤ የተጠራህለትንና በብዙ ምሥክሮች ፊት በጥሩ ሁኔታ በይፋ የተናገርክለትን የዘላለም ሕይወት አጥብቀህ ያዝ። 13  ሁሉንም ነገሮች ሕያው አድርጎ በሚያኖረው አምላክና ለጳንጥዮስ ጲላጦስ+ በይፋ ግሩም ምሥክርነት በሰጠው በክርስቶስ ኢየሱስ ፊት ይህን አዝሃለሁ፦ 14  ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እስኪገለጥ+ ድረስ ትእዛዙን ያለእንከንና ያለነቀፋ ጠብቅ፤ 15  ደስተኛውና ብቸኛው ኃያል ገዢ በተወሰነለት ጊዜ ራሱን ይገልጣል። እሱ የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ ነው፤+ 16  ያለመሞትን ባሕርይ+ የተላበሰው እሱ ብቻ ነው፤ ሊቀረብ በማይችል ብርሃን ውስጥ ይኖራል፤+ እሱን ያየ ወይም ሊያየው የሚችል አንድም ሰው የለም።+ ክብርና ዘላለማዊ ኃይል ለእሱ ይሁን። አሜን። 17  አሁን ባለው ሥርዓት* ሀብታም የሆኑትን ሰዎች እንዳይታበዩ እንዲሁም ተስፋቸውን አስተማማኝነት በሌለው ሀብት+ ላይ ሳይሆን የሚያስደስቱንን ነገሮች ሁሉ አትረፍርፎ በሚሰጠን አምላክ ላይ እንዲጥሉ እዘዛቸው።+ 18  በተጨማሪም መልካም ነገር እንዲያደርጉ፣ በመልካም ሥራዎች ባለጸጋ እንዲሆኑ እንዲሁም ለጋሶችና ለሌሎች ለማካፈል ዝግጁ እንዲሆኑ ምከራቸው፤+ 19  እውነተኛ የሆነውን ሕይወት አጥብቀው መያዝ ይችሉ ዘንድ+ ለራሳቸው ውድ ሀብት ማከማቸታቸውን ይኸውም ለወደፊቱ ጊዜ የሚሆን መልካም መሠረት መጣላቸውን ይቀጥሉ።+ 20  ጢሞቴዎስ ሆይ፣ ቅዱስ የሆነውን ነገር ከሚጻረሩ ከንቱ ንግግሮችና በውሸት “እውቀት” ተብለው ከሚጠሩ እርስ በርሳቸው ከሚቃረኑ ሐሳቦች በመራቅ+ በአደራ የተሰጠህን ነገር ጠብቅ።+ 21  አንዳንዶች እንዲህ ዓይነቱ እውቀት እንዲታይላቸው ለማድረግ ሲጣጣሩ ከእምነት ጎዳና ወጥተዋል። የአምላክ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ጤናማ፤ ጠቃሚ።”
ወይም “ክፉ ጉጉት።”
ወይም “ስድብና።”
“መጠለያ” ማለትም ሊሆን ይችላል። ቃል በቃል “መሸፈኛ።”
ወይም “በአሁኑ ዘመን።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።