የጴጥሮስ የመጀመሪያው ደብዳቤ 3:1-22

  • ሚስቶችና ባሎች (1-7)

  • የሌላውን ስሜት መረዳት፤ ሰላምን መፈለግ (8-12)

  • ለጽድቅ ሲባል መከራ መቀበል (13-22)

    • ስለ ተስፋችሁ መልስ ለመስጠት ዝግጁ ሁኑ (15)

    • ጥምቀትና ጥሩ ሕሊና (21)

3  በተመሳሳይም እናንተ ሚስቶች፣ ለቃሉ የማይታዘዙ ባሎች ካሉ ያለቃል በሚስቶቻቸው ምግባር እንዲማረኩ+ ለባሎቻችሁ ተገዙ፤+  ሊማረኩ የሚችሉትም ንጹሕ ምግባራችሁንና+ የምታሳዩትን ጥልቅ አክብሮት ሲመለከቱ ነው።  ውበታችሁ በውጫዊ ነገሮች በማጌጥ ይኸውም ሹሩባ በመሠራት፣ የወርቅ ጌጣጌጦች በማድረግ+ ወይም ያማረ ልብስ በመልበስ አይሁን፤  ከዚህ ይልቅ ውበታችሁ የማይጠፋውን ጌጥ ይኸውም በአምላክ ፊት ከፍተኛ ግምት የሚሰጠውን የሰከነና ገር መንፈስ የተላበሰ+ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁን።  ተስፋቸውን በአምላክ ላይ የጣሉ በቀድሞ ጊዜ የነበሩ ቅዱሳን ሴቶች ራሳቸውን ለባሎቻቸው በማስገዛት በዚህ ዓይነት ሁኔታ ራሳቸውን ያስውቡ ነበርና፤  ሣራም አብርሃምን ጌታዬ እያለች በመጥራት ትታዘዘው ነበር።+ እናንተም መልካም ማድረጋችሁን ከቀጠላችሁና በፍርሃት ካልተሸነፋችሁ+ ልጆቿ ናችሁ።  በተመሳሳይም እናንተ ባሎች ከእነሱ ጋር በእውቀት* አብራችሁ ኑሩ። እነሱም ከእናንተ ጋር የሕይወትን ጸጋ አብረው ስለሚወርሱ+ ጸሎታችሁ እንዳይታገድ ከእናንተ ይበልጥ እንደ ተሰባሪ ዕቃ የሆኑትን ሴቶችን አክብሯቸው።+  በመጨረሻም ሁላችሁም የአስተሳሰብ አንድነት* ይኑራችሁ፤+ የሌላውን ስሜት የምትረዱ ሁኑ፤ የወንድማማች መዋደድ ይኑራችሁ፤ ከአንጀት የምትራሩ ሁኑ፤+ ትሑታን ሁኑ።+  ክፉን በክፉ+ ወይም ስድብን በስድብ አትመልሱ።+ ከዚህ ይልቅ ባርኩ፤+ የተጠራችሁት ይህን ጎዳና በመከተል በረከትን እንድትወርሱ ነውና። 10  ስለዚህ “ሕይወትን የሚወድና መልካም ቀኖችን ማየት የሚፈልግ ሰው በምላሱ ክፉ ነገር ከመናገር፣+ በከንፈሩም ከማታለል ይቆጠብ። 11  ክፉ ከሆነ ነገር ይራቅ፤+ መልካም የሆነውንም ያድርግ፤+ ሰላምን ይፈልግ፤ ይከተለውም።+ 12  የይሖዋ* ዓይኖች ጻድቃንን ይመለከታሉና፤ ጆሮዎቹም ምልጃቸውን ይሰማሉ፤+ የይሖዋ* ፊት ግን ክፉ ነገሮችን በሚያደርጉ ላይ ነው።”+ 13  መልካም ነገር ለማድረግ ቀናተኞች ብትሆኑ ጉዳት የሚያደርስባችሁ ማን ነው?+ 14  ሆኖም ለጽድቅ ስትሉ መከራ ብትቀበሉ ደስተኞች ናችሁ።+ ይሁን እንጂ እነሱ የሚፈሩትን እናንተ አትፍሩ፤* ደግሞም አትሸበሩ።+ 15  ነገር ግን ክርስቶስን እንደ ጌታ አድርጋችሁ በልባችሁ ቀድሱት። እናንተ ስላላችሁ ተስፋ፣ ምክንያት እንድታቀርቡ ለሚጠይቃችሁ ሰው ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር ዝግጁ ሁኑ፤ ይህን ስታደርጉ ግን በገርነት* መንፈስና+ በጥልቅ አክብሮት ይሁን።+ 16  ስለ እናንተ መጥፎ ነገር የሚናገሩ ሰዎች፣ የክርስቶስ ተከታዮች እንደመሆናችሁ መጠን በምታሳዩት መልካም ምግባር+ የተነሳ ስለ እናንተ በሚናገሩት በማንኛውም መጥፎ ነገር እንዲያፍሩ+ ጥሩ ሕሊና ይኑራችሁ።+ 17  ክፉ ነገር ሠርታችሁ መከራ ከምትቀበሉ+ ይልቅ የአምላክ ፈቃድ ከሆነ፣ መልካም ነገር ሠርታችሁ መከራ ብትቀበሉ ይሻላልና።+ 18  ጻድቅ የሆነው ክርስቶስ እንኳ ለዓመፀኞች+ ሲል ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በመሞት+ ከኃጢአት ነፃ አውጥቷቸዋልና። ይህን ያደረገው እናንተን ወደ አምላክ ለመምራት ነው።+ ሥጋ ሆኖ ተገደለ፤+ ሆኖም መንፈስ ሆኖ ሕያው ሆነ።+ 19  በዚህ ሁኔታ እያለም ሄዶ በእስር ላሉት መናፍስት ሰበከላቸው፤*+ 20  እነዚህ መናፍስት ቀደም ሲል ማለትም በኖኅ ዘመን ጥቂት ሰዎች ይኸውም ስምንት ነፍሳት* በውኃው መካከል አልፈው የዳኑበት+ መርከብ እየተሠራ በነበረበት ጊዜ፣+ አምላክ በትዕግሥት እየጠበቀ ሳለ* ሳይታዘዙ የቀሩ ናቸው።+ 21  አሁንም ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆነው ጥምቀት በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ አማካኝነት እናንተን እያዳናችሁ ነው። ጥምቀት የሰውነትን እድፍ የሚያስወግድ ሳይሆን ጥሩ ሕሊና ለማግኘት ለአምላክ የሚቀርብ ልመና ነው።+ 22  ኢየሱስ ወደ ሰማይ የሄደ ሲሆን አሁን በአምላክ ቀኝ ይገኛል፤+ እንዲሁም መላእክት፣ ሥልጣናትና ኃይላት እንዲገዙለት ተደርጓል።+

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ለእነሱ አሳቢነት በማሳየት፤ ሁኔታቸውን በመረዳት።”
ወይም “የሐሳብ ስምምነት።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
“ዛቻቸውን አትፍሩ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
“ልዝብ፤ ለስላሳ፤ ሻካራ ያልሆነ” የሚል ትርጉም አለው።
ወይም “የፍርድ መልእክት አወጀ።”
ወይም “ሰዎች።”
ቃል በቃል “የአምላክ ትዕግሥት እየጠበቀ ሳለ።”