የጴጥሮስ የመጀመሪያው ደብዳቤ 5:1-14

  • “የአምላክን መንጋ እንደ እረኞች ሆናችሁ ተንከባከቡ” (1-4)

  • ትሑት ሁኑ፤ ንቁ ሆናችሁ ኑሩ! (5-11)

    • ‘የሚያስጨንቃችሁን ነገር ሁሉ በእሱ ላይ ጣሉ’ (7)

    • ዲያብሎስ እንደሚያገሳ አንበሳ ነው (8)

  • የመደምደሚያ ቃላት (12-14)

5  ስለዚህ እኔም እንደ እነሱ ሽማግሌ እንዲሁም የክርስቶስ መከራ ምሥክርና ወደፊት የሚገለጠው ክብር ተካፋይ እንደመሆኔ መጠን+ በመካከላችሁ ያሉትን ሽማግሌዎች እንዲህ በማለት አጥብቄ እለምናለሁ፦*  የበላይ ተመልካቾች ሆናችሁ በማገልገል* በአደራ የተሰጣችሁን የአምላክን መንጋ እንደ እረኞች ሆናችሁ ተንከባከቡ፤+ ሥራችሁን በግዴታ ሳይሆን በአምላክ ፊት በፈቃደኝነት ተወጡ፤+ አግባብ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት በመመኘት ሳይሆን+ ለማገልገል በመጓጓት፣  የአምላክ ንብረት በሆኑት ላይ ሥልጣናችሁን በማሳየት ሳይሆን+ ለመንጋው ምሳሌ በመሆን ጠብቁ።+  የእረኞች አለቃ+ በሚገለጥበት ጊዜ የማይጠፋ የክብር አክሊል ትቀበላላችሁ።+  በተመሳሳይም እናንተ ወጣቶች፣ ለሽማግሌዎች ተገዙ።+ ይሁንና እርስ በርስ ባላችሁ ግንኙነት ሁላችሁም ትሕትናን ልበሱ፤* ምክንያቱም አምላክ ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል።+  ስለዚህ በተገቢው ጊዜ ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኃይለኛው የአምላክ እጅ በታች ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ፤+  የሚያስጨንቃችሁንም* ነገር ሁሉ በእሱ ላይ ጣሉ፤+ ምክንያቱም እሱ ስለ እናንተ ያስባል።+  የማስተዋል ስሜታችሁን ጠብቁ፤ ንቁ ሆናችሁ ኑሩ!+ ጠላታችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሳ አንበሳ ይንጎራደዳል።+  ሆኖም በዓለም ዙሪያ በመላው የወንድማማች ማኅበር ውስጥ ያሉት ወንድሞቻችሁ ተመሳሳይ መከራ እየደረሰባቸው እንዳለ ተገንዝባችሁ+ በእምነት ጸንታችሁ በመቆም ተቃወሙት።+ 10  ከክርስቶስ ጋር ባላችሁ አንድነት ወደ ዘላለማዊ ክብሩ የጠራችሁ+ የጸጋ ሁሉ አምላክ ለጥቂት ጊዜ መከራ ከተቀበላችሁ በኋላ እሱ ራሱ ሥልጠናችሁ እንዲጠናቀቅ ያደርጋል። ጽኑ እንድትሆኑ ያደርጋችኋል፤+ ደግሞም ያጠነክራችኋል፤+ አጽንቶም ያቆማችኋል። 11  ኃይል ለዘላለም የእሱ ይሁን። አሜን። 12  እኔ ታማኝ ወንድም አድርጌ በምቆጥረው በስልዋኖስ*+ አማካኝነት ይህን በአጭሩ ጽፌላችኋለሁ፤ የጻፍኩላችሁም እናንተን ለማበረታታትና ይህ የአምላክ እውነተኛ ጸጋ እንደሆነ አጥብቄ ለመመሥከር ነው። ይህን ጸጋ አጥብቃችሁ ያዙ። 13  እንደ እናንተ የተመረጠችው በባቢሎን የምትገኘው ሰላምታ ታቀርብላችኋለች፤ ልጄ ማርቆስም+ ሰላምታ ያቀርብላችኋል። 14  በፍቅር እርስ በርስ በመሳሳም ሰላምታ ተለዋወጡ። ከክርስቶስ ጋር አንድነት ያላችሁ ሁሉ፣ ሰላም ለእናንተ ይሁን።

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “እመክራለሁ።”
ወይም “መንጋውን በጥንቃቄ በመከታተል።”
ወይም “ታጠቁ።”
ወይም “የሚያሳስባችሁንም።”
ሲላስ ተብሎም ይጠራል።