ሁለተኛ ሳሙኤል 12:1-31
12 በመሆኑም ይሖዋ ናታንን+ ወደ ዳዊት ላከው። እሱም ወደ ዳዊት መጥቶ+ እንዲህ አለው፦ “በአንዲት ከተማ ውስጥ የሚኖሩ ሁለት ሰዎች ነበሩ፤ አንደኛው ሀብታም ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ድሃ ነበር።
2 ሀብታሙ ሰው እጅግ ብዙ በጎችና ከብቶች ነበሩት፤+
3 ድሃው ሰው ግን ከገዛት አንዲት ትንሽ የበግ ጠቦት ሌላ ምንም አልነበረውም።+ እሱም ይንከባከባት ነበር፤ እሷም ከእሱና ከወንዶች ልጆቹ ጋር አብራ እየኖረች አደገች። ያለችውን ጥቂት ምግብ አብራ ትበላ፣ ከጽዋውም ትጠጣ እንዲሁም በእቅፉ ትተኛ ነበር። ለእሱም እንደ ሴት ልጁ ነበረች።
4 አንድ ቀን ሀብታሙ ሰው እንግዳ መጣበት፤ ሆኖም ይህ ሰው ወደ እሱ ለመጣው መንገደኛ የሚበላ ነገር ለማዘጋጀት ከራሱ በጎችና ከብቶች ላይ አልወሰደም። ከዚህ ይልቅ የድሃውን ሰው የበግ ጠቦት ወስዶ ወደ እሱ ለመጣው እንግዳ አዘጋጅቶ አቀረበለት።”+
5 በዚህ ጊዜ ዳዊት በሰውየው ላይ እጅግ ተቆጥቶ ናታንን እንዲህ አለው፦ “ሕያው በሆነው በይሖዋ እምላለሁ፣+ ይህን ያደረገው ሰው ሞት ይገባዋል!
6 ይህ ሰው እንዲህ ያለውን ነገር ስላደረገና ርኅራኄ ስላላሳየ በበግ ጠቦቷ ምትክ አራት እጥፍ መክፈል አለበት።”+
7 ከዚያም ናታን ዳዊትን እንዲህ አለው፦ “ያ ሰው አንተ ነህ! የእስራኤል አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘በእስራኤል ላይ ንጉሥ እንድትሆን እኔ ራሴ ቀባሁህ፤+ ከሳኦልም እጅ ታደግኩህ።+
8 የጌታህን ቤት ልሰጥህ፣+ የጌታህንም ሚስቶች+ በእቅፍህ ላደርግልህ ፈቃደኛ ነበርኩ፤ የእስራኤልንና የይሁዳንም ቤት ሰጠሁህ።+ ይህም ሁሉ አንሶህ ቢሆን ኖሮ ከዚህ የበለጠ ነገር ላደርግልህ ፈቃደኛ ነበርኩ።+
9 ታዲያ በፊቱ መጥፎ ነገር በመሥራት የይሖዋን ቃል ያቃለልከው ለምንድን ነው? ሂታዊውን ኦርዮን በሰይፍ መታኸው!+ በአሞናውያን ሰይፍ ከገደልከውም+ በኋላ ሚስቱን ወስደህ ሚስትህ አደረግካት።+
10 ስለዚህ የሂታዊውን የኦርዮን ሚስት ወስደህ ሚስትህ በማድረግ እኔን ስለናቅክ ሰይፍ ከቤትህ ፈጽሞ አይለይም።’+
11 ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ከገዛ ቤትህ መከራ አመጣብሃለሁ፤+ ዓይንህ እያየም ሚስቶችህን ወስጄ ለሌላ ሰው* እሰጣቸዋለሁ፤+ እሱም በቀን ብርሃን* ከሚስቶችህ ጋር ይተኛል።+
12 አንተ ይህን በድብቅ ብታደርገውም+ እኔ ግን በመላው እስራኤል ፊት በቀን ብርሃን* አደርገዋለሁ።’”
13 ከዚያም ዳዊት ናታንን “በይሖዋ ላይ ኃጢአት ሠርቻለሁ” አለው።+ ናታንም ዳዊትን እንዲህ አለው፦ “ይሖዋም ኃጢአትህን ይቅር ይላል።*+ አትሞትም።+
14 ይሁንና ይህን ድርጊት በመፈጸም ይሖዋን እጅግ ስለናቅክ አሁን የተወለደልህ ልጅ ይሞታል።”
15 ከዚያም ናታን ወደ ቤቱ ሄደ።
ይሖዋም የኦርዮ ሚስት ለዳዊት የወለደችለትን ልጅ በመቅሰፍት መታው፤ ልጁም ታመመ።
16 ዳዊትም ስለ ልጁ እውነተኛውን አምላክ ተማጸነ። ምንም ነገር ሳይቀምስም ጾመ፤ ወደ ክፍሉ ገብቶም ሌሊቱን ሙሉ መሬት ላይ ተኝቶ አደረ።+
17 በቤቱ ያሉ ሽማግሌዎችም መጥተው አጠገቡ ቆሙ፤ ከመሬት ሊያነሱትም ሞከሩ። እሱ ግን ፈቃደኛ አልሆነም፤ አብሯቸውም ምግብ አልበላም።
18 በሰባተኛው ቀን ልጁ ሞተ፤ የዳዊት አገልጋዮች ግን የልጁን መሞት ለእሱ መንገር ፈሩ። እነሱም እንዲህ አሉ፦ “ልጁ በሕይወት ሳለ ዳዊትን አነጋግረነው ነበር፤ እሱ ግን ሊሰማን ፈቃደኛ አልሆነም። ታዲያ አሁን ልጁ መሞቱን እንዴት እንነግረዋለን? መቼም ይህን ብንነግረው መጥፎ ነገር ሊያደርግ ይችላል።”
19 ዳዊት አገልጋዮቹ በሹክሹክታ ሲነጋገሩ ሲያይ ልጁ እንደሞተ ገባው። በመሆኑም አገልጋዮቹን “ልጁ ሞተ?” አላቸው። እነሱም “አዎ፣ ሞቷል” ብለው መለሱለት።
20 በዚህ ጊዜ ዳዊት ከመሬት ተነሳ። ከታጠበ፣ ዘይት ከተቀባና+ ልብሱን ከቀየረ በኋላም ወደ ይሖዋ ቤት+ ሄዶ ሰገደ። ወደ ቤቱም* ሄዶ ምግብ እንዲያቀርቡለት ጠየቀ፤ ከዚያም በላ።
21 አገልጋዮቹም “እንዲህ ያደረግከው ለምንድን ነው? ልጁ በሕይወት ሳለ ስትጾምና ስታለቅስ ነበር፤ ልጁ ሲሞት ግን ወዲያውኑ ተነሳህ፤ ምግብም በላህ” አሉት።
22 እሱም እንዲህ አለ፦ “ልጁ በሕይወት ሳለ ‘ማን ያውቃል፣ ይሖዋ ይራራልኝና ልጁን በሕይወት ያኖርልኝ ይሆናል’+ ብዬ ስላሰብኩ ጾምኩ፤+ እንዲሁም አለቀስኩ።
23 አሁን ግን ልጁ ሞቷል፤ ታዲያ የምጾመው ለምንድን ነው? መልሼ ላመጣው እችላለሁ?+ እኔ ወደ እሱ እሄዳለሁ+ እንጂ እሱ ወደ እኔ አይመለስም።”+
24 ከዚያም ዳዊት ሚስቱን ቤርሳቤህን+ አጽናናት። ወደ እሷም ገብቶ አብሯት ተኛ። ከጊዜ በኋላም ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙም ሰለሞን*+ ተባለ። ይሖዋም ወደደው፤+
25 በነቢዩ ናታን+ በኩል መልእክት ልኮም ለይሖዋ ሲል ስሙን ይዲድያህ* አለው።
26 ኢዮአብ የአሞናውያን+ ከተማ የሆነችውን ራባን+ መውጋቱን ቀጠለ፤ የነገሥታቱንም* ከተማ ተቆጣጠረ።+
27 በመሆኑም ኢዮአብ እንዲህ ብለው እንዲነግሩት መልእክተኞችን ወደ ዳዊት ላከ፦ “ከራባ+ ጋር ተዋግቼ የውኃዎችን ከተማ* ይዣለሁ።
28 በል አሁን የቀረውን ሠራዊት ሰብስብና ከተማዋን ከበህ በቁጥጥርህ ሥር አድርጋት። አለዚያ ከተማዋን እይዛትና ክብሩ ለእኔ ይሆናል።”*
29 በመሆኑም ዳዊት ሠራዊቱን ሁሉ ሰብስቦ ወደ ራባ ሄደ፤ ከተማዋንም ወግቶ በቁጥጥር ሥር አደረጋት።
30 ከዚያም የማልካምን* ዘውድ ከራሱ ላይ ወሰደ። የዘውዱም ክብደት አንድ ታላንት* ወርቅ ነበር፤ በላዩም ላይ የከበሩ ድንጋዮች ነበሩ፤ ዘውዱም በዳዊት ራስ ላይ ተደረገ። በተጨማሪም ከከተማዋ+ በጣም ብዙ ምርኮ ወሰደ።+
31 ነዋሪዎቿንም አውጥቶ ድንጋይ እንዲቆርጡ፣ ስለት ባላቸው የብረት መሣሪያዎችና በብረት መጥረቢያዎች እንዲሠሩ እንዲሁም ጡብ እንዲያመርቱ አደረጋቸው። በአሞናውያን ከተሞች ሁሉ እንዲሁ አደረገ። በመጨረሻም ዳዊትና ሠራዊቱ ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።
የግርጌ ማስታወሻ
^ ወይም “ለባልንጀራህ።”
^ ቃል በቃል “በዚህች ፀሐይ ዓይኖች።”
^ ቃል በቃል “በፀሐይ ፊት።”
^ ወይም “ኃጢአትህ አልፎ እንዲሄድ ያደርጋል።”
^ ወይም “ቤተ መንግሥቱም።”
^ “ሰላም” የሚል ትርጉም ካለው የዕብራይስጥ ቃል የመጣ ነው።
^ “በያህ የተወደደ” የሚል ትርጉም አለው።
^ ወይም “የመንግሥቱንም።”
^ ከተማዋ ውኃ የምታገኝባቸውን የውኃ ምንጮች የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።
^ ቃል በቃል “ስሜ ይጠራባታል።”
^ ይህ የአሞናውያን ጣዖት ሳይሆን አይቀርም፤ በሌላ ቦታ ላይ ሞሎክ ወይም ሚልኮም ተብሎም ተጠርቷል።