ሁለተኛ ሳሙኤል 16:1-23

  • ሲባ የሜፊቦስቴን ስም አጠፋ (1-4)

  • ሺምአይ ዳዊትን ረገመው (5-14)

  • አቢሴሎም ኩሲን ተቀበለው (15-19)

  • የአኪጦፌል ምክር (20-23)

16  ዳዊት የተራራውን ጫፍ+ አልፎ ጥቂት እንደሄደ ሲባ+ የተባለው የሜፊቦስቴ+ አገልጋይ 200 ዳቦዎች፣ 100 የዘቢብ ቂጣዎች፣ ከበጋ ፍሬ* የተዘጋጁ 100 ቂጣዎችና አንድ እንስራ የወይን ጠጅ የተጫነባቸው ሁለት አህዮች እየነዳ ሊያገኘው መጣ።+  ንጉሡም ሲባን “እነዚህን ነገሮች ያመጣኸው ለምንድን ነው?” አለው። ሲባም “አህዮቹን የንጉሡ ቤተሰብ እንዲቀመጥባቸው፣ ዳቦውንና የበጋ ፍሬውን ደግሞ ወጣቶቹ እንዲበሏቸው፣ የወይን ጠጁንም በምድረ በዳ የደከሙ ሰዎች እንዲጠጡት ነው” ሲል መለሰ።+  ንጉሡም “የጌታህ ልጅ* የት አለ?” አለው።+ በዚህ ጊዜ ሲባ ንጉሡን “‘ዛሬ የእስራኤል ቤት የአባቴን ንጉሣዊ ሥልጣን ይመልስልኛል’ ብሎ ስላሰበ ኢየሩሳሌም ቀርቷል” አለው።+  ንጉሡም ሲባን “እንግዲህ የሜፊቦስቴ የሆነው ሁሉ የአንተ ነው” አለው።+ ሲባም “በፊትህ እሰግዳለሁ። ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፣ በአንተ ዘንድ ሞገስ ላግኝ” ሲል መለሰ።+  ንጉሥ ዳዊትም ባሁሪም ሲደርስ ከሳኦል ቤት የሆነ ሺምአይ+ የተባለ ሰው ከዚያ ወጥቶ እየተራገመ+ ወደ እነሱ ቀረበ፤ እሱም የጌራ ልጅ ነበር።  ሺምአይ በንጉሥ ዳዊትና በአገልጋዮቹ ሁሉ ላይ እንዲሁም በንጉሡ ግራና ቀኝ በነበረው ሕዝብ ሁሉና በኃያላኑ ላይ ድንጋይ ይወረውር ነበር።  ሺምአይም እንዲህ እያለ ይራገም ነበር፦ “ውጣ፣ ከዚህ ውጣ፣ አንተ የደም ሰው! አንተ የማትረባ ሰው!  ንግሥናውን በወሰድክበት በሳኦል ቤት የተነሳ ያለብህን የደም ዕዳ በሙሉ ይሖዋ በአንተ ላይ እያመጣብህ ነው፤ ይሖዋም መንግሥትህን ለልጅህ ለአቢሴሎም አሳልፎ ይሰጠዋል። የደም ሰው ስለሆንክ ይኸው መከራህን እያየህ ነው!”+  ከዚያም የጽሩያ+ ልጅ አቢሳ ንጉሡን “ይህ የሞተ ውሻ+ ጌታዬን ንጉሡን የሚራገመው ለምንድን ነው?+ እባክህ ልሂድና ራሱን ልቁረጠው”+ አለው። 10  ንጉሡ ግን “እናንተ የጽሩያ ልጆች፣ ከእናንተ ጋር ምን የሚያገናኘኝ ጉዳይ አለ?+ ተዉት ይርገመኝ፤+ ምክንያቱም ይሖዋ ‘ዳዊትን እርገመው!’ ብሎታል።+ ታዲያ ‘ለምን እንዲህ ታደርጋለህ?’ ማን ሊለው ይችላል?” አለው። 11  ከዚያም ዳዊት አቢሳንና አገልጋዮቹን በሙሉ እንዲህ አላቸው፦ “ከአብራኬ የወጣው የገዛ ልጄ እንኳ ይኸው ሕይወቴን* እየፈለገ አይደል?+ ታዲያ አንድ ቢንያማዊ+ እንዲህ ቢያደርግ ምን ያስደንቃል! ተዉት ይርገመኝ፤ ይሖዋ እርገመው ብሎት ነው! 12  ምናልባትም ይሖዋ መከራዬን ያይልኝና+ በዛሬው እርግማን ፋንታ ይሖዋ መልካም ነገር ያደርግልኝ ይሆናል።”+ 13  ከዚያም ዳዊትና ሰዎቹ መንገዱን ይዘው ቁልቁል ወረዱ፤ ሺምአይም በተራራው ጥግ ከዳዊት ጎን ጎን እየሄደ ይራገም፣+ ድንጋይ ይወረውርና አቧራ ይበትን ነበር። 14  በኋላም ንጉሡና አብሮት የነበረው ሕዝብ በሙሉ ወዳሰቡበት ቦታ ደረሱ፤ እነሱም በጣም ደክሟቸው ነበር፤ በዚያም አረፉ። 15  ይህ በእንዲህ እንዳለ አቢሴሎምና የእስራኤል ሰዎች በሙሉ ኢየሩሳሌም ደረሱ፤ አኪጦፌልም+ አብሮት ነበር። 16  የዳዊት ወዳጅ* አርካዊው+ ኩሲም+ ልክ ወደ አቢሴሎም እንደገባ አቢሴሎምን “ንጉሡ ለዘላለም ይኑር!+ ንጉሡ ለዘላለም ይኑር!” አለው። 17  በዚህ ጊዜ አቢሴሎም ኩሲን “ለወዳጅህ ታማኝ ፍቅር የምታሳየው በዚህ መንገድ ነው? ከወዳጅህ ጋር አብረህ ያልሄድከው ለምንድን ነው?” አለው። 18  ኩሲም አቢሴሎምን እንዲህ አለው፦ “በጭራሽ፣ እንዲህማ አላደርግም፤ ይሖዋ፣ ይህ ሕዝብና የእስራኤል ሰዎች በሙሉ ከመረጡት ሰው ጎን እቆማለሁ። ከእሱም ጋር እቀመጣለሁ። 19  ደግሜ ይህን እናገራለሁ፣ ማገልገል ያለብኝ ማንን ነው? ልጁን አይደለም? አባትህን እንዳገለገልኩ ሁሉ አንተንም አገለግላለሁ።”+ 20  ከዚያም አቢሴሎም አኪጦፌልን “እስቲ ምክር ስጡኝ።+ ምን ብናደርግ ይሻላል?” አለው። 21  አኪጦፌልም አቢሴሎምን “አባትህ፣ ቤቱን* እንዲጠብቁ ከተዋቸው+ ቁባቶቹ ጋር ግንኙነት ፈጽም።+ ከዚያም እስራኤላውያን ሁሉ ራስህን በአባትህ ዘንድ እንደ ጥንብ እንዳስቆጠርክ ይሰማሉ፤ አንተንም የሚደግፉ ብርታት ያገኛሉ” አለው። 22  በመሆኑም ለአቢሴሎም በጣሪያው ላይ ድንኳን ተከሉለት፤+ አቢሴሎምም እስራኤላውያን ሁሉ እያዩት+ ከአባቱ ቁባቶች ጋር ግንኙነት ፈጸመ።+ 23  በዚያ ዘመን አኪጦፌል+ የሚሰጠው ምክር እንደ እውነተኛው አምላክ ቃል ተደርጎ* ይቆጠር ነበር። ዳዊትም ሆነ አቢሴሎም የአኪጦፌልን ምክር ሁሉ የሚያዩት እንደዚያ ነበር።

የግርጌ ማስታወሻ

የበጋ ፍሬ በዋነኝነት የሚያመለክተው በለስን ሲሆን ቴምርንም ሊጨምር ይችላል።
ወይም “የልጅ ልጅ።”
ወይም “ነፍሴን።”
ወይም “የዳዊት ሚስጥረኛ።”
ወይም “ቤተ መንግሥቱን።”
ወይም “አንድ ሰው የእውነተኛውን አምላክ ቃል እንደጠየቀ ተደርጎ።”