ሁለተኛ ሳሙኤል 22:1-51

  • ዳዊት፣ ይሖዋ ከጠላቶቹ ስለታደገው ውዳሴ አቀረበ (1-51)

    • “ይሖዋ ቋጥኜ፣ ምሽጌና ታዳጊዬ ነው” (2)

    • ይሖዋ ታማኝ ለሆነ ሰው ታማኝ ይሆናል (26)

22  ዳዊት፣ ይሖዋ ከጠላቶቹ ሁሉ እጅና ከሳኦል እጅ+ በታደገው+ ቀን የዚህን መዝሙር ቃል ለይሖዋ ዘመረ።+  እንዲህም አለ፦ “ይሖዋ ቋጥኜ፣ ምሽጌና+ ታዳጊዬ ነው።+   አምላኬ የምሸሸግበት ዓለቴ ነው፤+ጋሻዬ፣+ የመዳኔ ቀንድና* አስተማማኝ መጠጊያዬ ነው፤+መሸሻዬና+ አዳኜ ነው፤+ አንተ ከዓመፅ ታድነኛለህ።   ውዳሴ የሚገባውን ይሖዋን እጠራለሁ፤ከጠላቶቼም እድናለሁ።   የሞት ማዕበል ዙሪያዬን ከቦኛል፤+የማይረቡ ሰዎች የለቀቁት ድንገተኛ ጎርፍ አሸበረኝ።+   የመቃብር* ገመድ ተጠመጠመብኝ፤+የሞት ወጥመድ ተጋረጠብኝ።+   በጭንቅ ውስጥ ሳለሁ ይሖዋን ጠራሁት፤+አምላኬን ደጋግሜ ጠራሁት። እሱም በመቅደሱ ሆኖ ድምፄን ሰማ፣እርዳታ ለማግኘት የማሰማውም ጩኸት ወደ ጆሮው ደረሰ።+   ምድርም ወዲያና ወዲህ ትናወጥና ትንቀጠቀጥ ጀመር፤+የሰማያት መሠረቶች ተንቀጠቀጡ፤+እሱ ስለተቆጣም ራዱ።+   ከአፍንጫው ጭስ ወጣ፤የሚባላም እሳት ከአፉ ወጣ፤+ፍምም ከእሱ ፈለቀ። 10  ወደ ታች ሲወርድ ሰማያት እንዲያጎነብሱ አደረገ፤+ከእግሮቹም በታች ጥቅጥቅ ያለ ደመና ነበር።+ 11  በኪሩብ ላይ ተቀምጦ+ እየበረረ መጣ። በመንፈስ ክንፎችም* ላይ ሆኖ ይታይ ነበር።+ 12  ከዚያም ጨለማን በዙሪያው እንደ መጠለያ አደረገ፣+ጨለማውም ጥቁር ውኃና ጥቅጥቅ ያለ ደመና ነበረው። 13  በፊቱ ካለው ብርሃን ፍም ፈለቀ። 14  ከዚያም ይሖዋ ከሰማይ ያንጎደጉድ ጀመር፤+ልዑሉ አምላክ ድምፁን አሰማ።+ 15  ፍላጻዎቹን+ አስፈንጥሮ በታተናቸው፤መብረቁን አብርቆ ግራ አጋባቸው።+ 16  በይሖዋ ተግሣጽ፣ ከአፍንጫውም በሚወጣው ኃይለኛ እስትንፋስ+የባሕር ወለሎች ታዩ፤+የምድር መሠረቶችም ተገለጡ። 17  ከላይ ሆኖ እጁን ሰደደ፤ከጥልቅ ውኃ ውስጥም አወጣኝ።+ 18  ከብርቱ ጠላቴ አዳነኝ፤+ከእኔ ይበልጥ ብርቱዎች ከሆኑት፣ ከሚጠሉኝ ሰዎች ታደገኝ። 19  ችግር ላይ በወደቅኩበት ቀን ተነሱብኝ፤+ይሖዋ ግን ድጋፍ ሆነልኝ። 20  ደህንነት ወደሚገኝበት ስፍራ* አመጣኝ፤+በእኔ ስለተደሰተ ታደገኝ።+ 21  ይሖዋ እንደ ጽድቄ ወሮታ ይከፍለኛል፤+እንደ እጄ ንጽሕና ብድራት ይመልስልኛል።+ 22  የይሖዋን መንገድ ጠብቄአለሁና፤አምላኬን በመተው ክፉ ድርጊት አልፈጸምኩም። 23  ፍርዱ+ ሁሉ በፊቴ ነው፤ደንቦቹን+ አልተላለፍም። 24  በፊቱ እንከን የለሽ+ ሆኜ እኖራለሁ፤ራሴንም ከስህተት እጠብቃለሁ።+ 25  ይሖዋ እንደ ጽድቄ፣+በፊቱም እንዳለኝ ንጽሕና ብድራት ይመልስልኝ።+ 26  ታማኝ ለሆነ ሰው ታማኝ ትሆናለህ፤+እንከን የለሽ ለሆነ ኃያል ሰው እንከን የለሽ ትሆናለህ፤+ 27  ከንጹሕ ሰው ጋር ንጹሕ ሆነህ ትገኛለህ፤+ጠማማ ለሆነ ሰው ግን ብልህ መሆንህን ታሳያለህ።*+ 28  ትሑት የሆኑትን ታድናለህና፤+ዓይኖችህ ግን በትዕቢተኞች ላይ ናቸው፤ አንተም ታዋርዳቸዋለህ።+ 29  ይሖዋ ሆይ፣ አንተ መብራቴ ነህና፤+ጨለማዬን ብርሃን የሚያደርገው ይሖዋ ነው።+ 30  በአንተ እርዳታ ወራሪውን ቡድን መጋፈጥ እችላለሁ፤በአምላክ ኃይል ቅጥር መውጣት እችላለሁ።+ 31  የእውነተኛው አምላክ መንገድ ፍጹም ነው፤+የይሖዋ ቃል የነጠረ ነው።+ እሱ መጠጊያ ለሚያደርጉት ሁሉ ጋሻቸው ነው።+ 32  ደግሞስ ከይሖዋ ሌላ አምላክ ማን ነው?+ ከአምላካችንስ በቀር ዓለት ማን ነው?+ 33  እውነተኛው አምላክ ጠንካራ ምሽጌ ነው፤+መንገዴንም ፍጹም ያደርግልኛል።+ 34  እግሮቼን እንደ ዋልያ እግሮች ያደርጋል፤በከፍታ ቦታዎች ላይ ያቆመኛል።+ 35  እጆቼን ለጦርነት ያሠለጥናል፤ክንዶቼ የመዳብ ደጋን ማጠፍ ይችላሉ። 36  የመዳን ጋሻህን ትሰጠኛለህ፤ትሕትናህም ታላቅ ያደርገኛል።+ 37  ለእርምጃዬ መንገዱን ታሰፋልኛለህ፤እግሮቼ* አያዳልጣቸውም።+ 38  ጠላቶቼን አሳድጄ አጠፋቸዋለሁ፤ተጠራርገው እስኪጠፉ ድረስ ወደ ኋላ አልመለስም። 39  እንዳያንሰራሩም ጠራርጌ አጠፋቸዋለሁ፣ አደቃቸዋለሁ፤+እግሬ ሥር ይወድቃሉ። 40  ለውጊያው ብርታት ታስታጥቀኛለህ፤+ጠላቶቼ ሥሬ እንዲወድቁ ታደርጋለህ።+ 41  ጠላቶቼ ከእኔ እንዲሸሹ ታደርጋለህ፤*+እኔም የሚጠሉኝን አጠፋለሁ።*+ 42  እርዳታ ለማግኘት ይጮኻሉ፤ ሆኖም የሚያድናቸው የለም፤ወደ ይሖዋም ይጮኻሉ፤ እሱ ግን አይመልስላቸውም።+ 43  በምድር ላይ እንዳለ አቧራ አደቃቸዋለሁ፤በመንገድ ላይ እንዳለ ጭቃ እረግጣቸዋለሁ፤ አደቃቸዋለሁ። 44  ስህተት ከሚለቃቅሙት ሕዝቦቼ ታድነኛለህ።+ የብሔራት መሪ እንድሆን ትጠብቀኛለህ፤+የማላውቀው ሕዝብ ያገለግለኛል።+ 45  ባዕዳንም ተሸማቀው ወደ ፊቴ ይቀርባሉ፤+ስለ እኔ የሚሰሙትም እንዲታዘዙኝ ያደርጋቸዋል።* 46  የባዕድ አገር ሰዎች ወኔ ይከዳቸዋል፤*ከምሽጎቻቸው እየተንቀጠቀጡ ይወጣሉ። 47  ይሖዋ ሕያው ነው! ዓለቴ ይወደስ!+ የመዳኔ ዓለት የሆነው አምላክ ከፍ ከፍ ይበል።+ 48  እውነተኛው አምላክ ይበቀልልኛል፤+ሕዝቦችንም ከበታቼ ያስገዛልኛል፤+ 49  እሱ ከጠላቶቼ ያድነኛል። ከሚያጠቁኝ ሰዎች በላይ ከፍ ከፍ ታደርገኛለህ፤+ከዓመፀኛ ሰው ታድነኛለህ።+ 50  ይሖዋ ሆይ፣ በብሔራት መካከል የማመሰግንህ ለዚህ ነው፤+ለስምህም እንዲህ ብዬ የውዳሴ መዝሙር እዘምራለሁ፦+ 51  ለንጉሡ ታላላቅ የማዳን ሥራዎችን ያከናውናል፤*+ለቀባውም ታማኝ ፍቅር ያሳያል፤ለዳዊትና ለዘሩ ለዘላለም ይህን ያደርጋል።”+

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ኃያል አዳኜና።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “የሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “በነፋስ ክንፎችም።”
ወይም “ሰፊ ወደሆነ ስፍራ።”
“እንደ ሞኝ ትሆናለህ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ቁርጭምጭሚቶቼ።”
ወይም “የጠላቶቼን ማጅራት ትሰጠኛለህ።”
ቃል በቃል “ጸጥ አሰኛለሁ።”
ቃል በቃል “ጆሮ በሰማው ይታዘዙኛል።”
ወይም “ይከስማሉ።”
ወይም “ታላላቅ ድሎችን ያጎናጽፋል።”