ሁለተኛ ሳሙኤል 24:1-25

  • ዳዊት ሕዝቡን በመቁጠር የፈጸመው ኃጢአት (1-14)

  • ይሖዋ በላከው ቸነፈር 70,000 ሰዎች ሞቱ (15-17)

  • ዳዊት መሠዊያ ሠራ (18-25)

    • ‘ምንም ያልከፈልኩበትን ነገር መሥዋዕት አድርጌ አላቀርብም’ (24)

24  ዳዊትንም “ሂድ፣ እስራኤልንና ይሁዳን+ ቁጠር”+ ብሎ በእነሱ ላይ ባነሳሳው* ጊዜ የይሖዋ ቁጣ እንደገና በእስራኤል ላይ ነደደ።+  ንጉሡም ከእሱ ጋር አብሮት የነበረውን የሠራዊቱን አለቃ ኢዮዓብን+ “የሕዝቡን ብዛት እንዳውቅ እስቲ ከዳን እስከ ቤርሳቤህ+ ባሉት በሁሉም የእስራኤል ነገዶች መካከል ተዘዋውራችሁ ሕዝቡን መዝግቡ” አለው።  ኢዮዓብ ግን ንጉሡን “አምላክህ ይሖዋ ሕዝቡን 100 እጥፍ ያብዛው፤ የጌታዬ የንጉሡም ዓይኖች ይህን ይዩ፤ ሆኖም ጌታዬ ንጉሡ ይህን ማድረግ የፈለገው ለምንድን ነው?” አለው።  ሆኖም የንጉሡ ቃል ኢዮዓብንና የሠራዊቱን አዛዦች አሸነፋቸው። በመሆኑም ኢዮዓብና የሠራዊቱ አዛዦች የእስራኤልን ሕዝብ ለመመዝገብ+ ከንጉሡ ፊት ወጥተው ሄዱ።  እነሱም ዮርዳኖስን ተሻግረው በሸለቆ* ውስጥ ከምትገኘው ከተማ በስተ ቀኝ* ባለችው በአሮዔር+ ሰፈሩ፤ ከዚያም ወደ ጋዳውያን፣ ወደ ያዜር+ ሄዱ።  በኋላም ወደ ጊልያድና+ ወደ ታህቲምሆድሺ ምድር ሄዱ፤ ከዚያም ወደ ዳንየዓን ቀጠሉ፤ ዞረውም ወደ ሲዶና+ ሄዱ።  ከዚያም ወደ ጢሮስ+ ምሽግ እንዲሁም ወደ ሂዋውያንና+ ወደ ከነአናውያን ከተሞች በሙሉ ሄዱ፤ በመጨረሻም በይሁዳ ባለችው በኔጌብ+ ወደምትገኘው ወደ ቤርሳቤህ+ መጡ።  በዚህ መንገድ በመላው ምድር ሲዘዋወሩ ቆይተው ከዘጠኝ ወር ከሃያ ቀን በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ።  ኢዮዓብም የተመዘገበውን የሕዝቡን ቁጥር ለንጉሡ ሰጠው። በእስራኤል ውስጥ ሰይፍ የታጠቁ 800,000 ተዋጊዎች ነበሩ፤ የይሁዳ ሰዎች ደግሞ 500,000 ነበሩ።+ 10  ሆኖም ዳዊት ሕዝቡን ከቆጠረ በኋላ ልቡ* ወቀሰው።+ ከዚያም ዳዊት ይሖዋን “ይህን በማድረጌ ከባድ ኃጢአት ሠርቻለሁ።+ አሁንም ይሖዋ ሆይ፣ እባክህ የአገልጋይህን በደል ይቅር በል፤+ ታላቅ የሞኝነት ድርጊት ፈጽሜአለሁና” አለው።+ 11  ዳዊት ጠዋት ላይ ሲነሳ እንዲህ የሚል የይሖዋ ቃል የዳዊት ባለ ራእይ ወደሆነው ወደ ነቢዩ ጋድ+ መጣ፦ 12  “ሂድና ዳዊትን እንዲህ በለው፦ ‘ይሖዋ “ሦስት ምርጫዎችን ሰጥቼሃለሁ። በአንተ ላይ አመጣብህ ዘንድ አንዱን ምረጥ” ይላል።’”+ 13  ስለዚህ ጋድ ወደ ዳዊት ገብቶ እንዲህ አለው፦ “በምድርህ ላይ ለሰባት ዓመት ረሃብ+ ይሁን ወይስ ጠላቶችህ እያሳደዱህ ለሦስት ወር ከእነሱ ብትሸሽ ይሻልሃል?+ ወይስ ደግሞ በምድርህ ላይ ለሦስት ቀን ቸነፈር ይምጣ?+ እንግዲህ አሁን ለላከኝ ምን መልስ እንደምሰጥ በጥሞና አስብበት።” 14  ስለዚህ ዳዊት ጋድን “ሁኔታው በጣም አስጨንቆኛል። ምሕረቱ ታላቅ ስለሆነ+ እባክህ በይሖዋ እጅ እንውደቅ፤+ ሰው እጅ ላይ ግን አትጣለኝ”+ አለው። 15  ከዚያም ይሖዋ ከጠዋት አንስቶ እስከተወሰነው ጊዜ ድረስ በእስራኤል ላይ ቸነፈር ላከ፤+ በዚህም የተነሳ ከዳን አንስቶ እስከ ቤርሳቤህ+ ድረስ ካለው ሕዝብ መካከል 70,000 ሰዎች ሞቱ።+ 16  መልአኩም ኢየሩሳሌምን ለማጥፋት እጁን ወደ እሷ በዘረጋ ጊዜ ይሖዋ በደረሰው ጥፋት ተጸጸተ፤*+ በመሆኑም በሕዝቡ ላይ ጥፋት እያመጣ የነበረውን መልአክ “ይብቃ! አሁን እጅህን መልስ” አለው። የይሖዋ መልአክ በኢያቡሳዊው+ በአረውና+ አውድማ አጠገብ ነበር። 17  ዳዊትም ሕዝቡን እየገደለ ያለውን መልአክ ሲያይ ይሖዋን “ኃጢአት የሠራሁት እኮ እኔ ነኝ፤ ያጠፋሁትም እኔ ነኝ፤ ታዲያ እነዚህ በጎች+ ምን አደረጉ? እባክህ እጅህ በእኔና በአባቴ ቤት ላይ ትሁን”+ አለው። 18  በመሆኑም ጋድ በዚያው ቀን ወደ ዳዊት መጥቶ “ውጣና በኢያቡሳዊው በአረውና አውድማ ላይ ለይሖዋ መሠዊያ ሥራ” አለው።+ 19  ስለዚህ ዳዊት፣ ጋድ በነገረው መሠረት ይሖዋ እንዳዘዘው ተነስቶ ወጣ። 20  አረውናም ቁልቁል ሲመለከት ንጉሡና አገልጋዮቹ ወደ እሱ ሲመጡ አየ፤ እሱም ወዲያውኑ ወጥቶ በግንባሩ መሬት ላይ በመደፋት ለንጉሡ ሰገደ። 21  ከዚያም አረውና “ጌታዬ ንጉሡ ወደ አገልጋዩ የመጣው ለምንድን ነው?” አለው። ዳዊትም “በሕዝቡ ላይ እየወረደ ያለው መቅሰፍት እንዲቆም+ ለይሖዋ መሠዊያ ለመሥራት ይህን አውድማ ከአንተ ላይ ለመግዛት ነው” አለው። 22  አረውና ግን ዳዊትን እንዲህ አለው፦ “ጌታዬ ንጉሡ አውድማውን ወስዶ መልካም መስሎ የታየውን ነገር ያቅርብበት። ለሚቃጠል መባ የሚሆኑት ከብቶች እነዚሁልህ፣ ማሄጃውና* ከብቶቹ ላይ የሚውሉት መሣሪያዎች ደግሞ ለማገዶ ይሁኑ። 23  ንጉሥ ሆይ፣ አረውና እነዚህን ሁሉ ለንጉሡ ሰጥቷል።” አክሎም አረውና ንጉሡን “አምላክህ ይሖዋ ሞገስ ያሳይህ” አለው። 24  ሆኖም ንጉሡ አረውናን “በፍጹም አይሆንም! ዋጋውን ልከፍልህ ይገባል። ደግሞም ምንም ያልከፈልኩበትን ነገር ለአምላኬ ለይሖዋ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጌ አላቀርብም” አለው። ስለዚህ ዳዊት አውድማውንና ከብቶቹን በ50 የብር ሰቅል* ገዛ።+ 25  ዳዊትም በዚያ ለይሖዋ መሠዊያ+ ሠርቶ የሚቃጠሉ መሥዋዕቶችንና የኅብረት መሥዋዕቶችን አቀረበ። ይሖዋም ስለ ምድሪቱ የቀረበውን ልመና ሰማ፤+ በእስራኤል ላይ ይወርድ የነበረው መቅሰፍትም ቆመ።

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ዳዊት በተነሳሳ።”
ወይም “በደረቁ ወንዝ።”
ወይም “በስተ ደቡብ።”
ወይም “ሕሊናው።”
ወይም “አዘነ።”
ጥርስ መሳይ ጉጦች ያሉት የእህል መውቂያ።
አንድ ሰቅል 11.4 ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።