ሁለተኛ ሳሙኤል 4:1-12

  • ኢያቡስቴ ተገደለ (1-8)

  • ዳዊት የኢያቡስቴን ገዳዮች አስገደላቸው (9-12)

4  የሳኦል ልጅ ኢያቡስቴ፣*+ አበኔር በኬብሮን መሞቱን+ ሲሰማ ወኔ ከዳው፤* እስራኤላውያንም በሙሉ ተረበሹ።  የሳኦል ልጅ የሚመራቸው ወራሪ ቡድኖች አለቃ የሆኑ ሁለት ሰዎች ነበሩ፤ የአንደኛው ስም ባአናህ ሲሆን የሌላኛው ስም ደግሞ ሬካብ ነበር። እነሱም ከቢንያም ነገድ የሆነው የበኤሮታዊው የሪሞን ልጆች ነበሩ። (ምክንያቱም በኤሮት+ ከቢንያም ወገን እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠር ነበር።  በኤሮታውያን ወደ ጊታይም+ ሸሹ፤ እስከ ዛሬም ድረስ በዚያ የባዕድ አገር ሰው ሆነው ይኖራሉ።)  የሳኦል ልጅ ዮናታን+ እግሮቹ ሽባ የሆኑ አንድ ልጅ ነበረው።+ እሱም ስለ ሳኦልና ስለ ዮናታን የሚገልጸው ወሬ ከኢይዝራኤል+ በመጣ ጊዜ የአምስት ዓመት ልጅ ነበር፤ ሞግዚቱም አንስታው መሸሽ ጀመረች፤ ሆኖም በድንጋጤ ሸሽታ ስትሮጥ ከእጇ ላይ ወድቆ ሽባ ሆነ። ስሙም ሜፊቦስቴ+ ነበር።  የበኤሮታዊው የሪሞን ልጆች ሬካብ እና ባአናህ ሞቃታማ በሆነው የቀኑ ክፍለ ጊዜ ወደ ኢያቡስቴ ቤት ሄዱ፤ እሱም ቀትር ላይ አረፍ ብሎ ነበር።  እነሱም ስንዴ የሚወስዱ ሰዎች መስለው ወደ ቤቱ ውስጥ ዘልቀው ገቡ፤ ኢያቡስቴንም ሆዱ ላይ ወጉት፤ ከዚያም ሬካብ እና ወንድሙ ባአናህ+ ሸሽተው አመለጡ።  ወደ ቤት ሲገቡ ኢያቡስቴ መኝታ ቤቱ ውስጥ አልጋው ላይ ጋደም ብሎ ነበር፤ እነሱም መትተው ገደሉት፤ ከዚያም ራሱን ቆርጠው በመውሰድ ወደ አረባ በሚወስደው መንገድ ሌሊቱን ሙሉ ሲጓዙ አደሩ።  የኢያቡስቴንም+ ራስ በኬብሮን ወዳለው ወደ ዳዊት አምጥተው ንጉሡን “ሕይወትህን* ሲፈልጋት+ የነበረው የጠላትህ+ የሳኦል ልጅ የኢያቡስቴ ራስ ይኸውልህ። ይሖዋ በዛሬው ዕለት ሳኦልንና ዘሮቹን ለጌታዬ ለንጉሡ ተበቀለለት” አሉት።  ሆኖም ዳዊት ለበኤሮታዊው ለሪሞን ልጆች ለሬካብ እና ለወንድሙ ለባአናህ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ሕይወቴን ከመከራ ሁሉ በታደገልኝ*+ ሕያው በሆነው በይሖዋ እምላለሁ፣ 10  አንድ ሰው ምሥራች ያበሰረኝ መስሎት ‘ሳኦል እኮ ሞተ’+ ብሎ በነገረኝ ጊዜ ጺቅላግ ላይ ገደልኩት።+ መልእክተኛው ከእኔ ያገኘው ሽልማት ይህ ነበር! 11  ታዲያ በገዛ ቤቱ አልጋው ላይ ተኝቶ የነበረውን ጻድቅ ሰው የገደሉ ክፉ ሰዎችማ እንዴት ከዚህ የባሰ ነገር አይጠብቃቸው! እና አሁን ደሙን ከእጃችሁ መጠየቅም+ ሆነ እናንተን ከምድር ገጽ ማጥፋት አይገባኝም?” 12  ከዚያም ዳዊት እንዲገድሏቸው ለወጣቶቹ ትእዛዝ ሰጠ።+ እነሱም እጆቻቸውንና እግሮቻቸውን ቆርጠው በኬብሮን በሚገኘው ኩሬ አጠገብ ሰቀሏቸው።+ የኢያቡስቴን ራስ ግን ወስደው በኬብሮን ባለው በአበኔር የመቃብር ቦታ ቀበሩት።

የግርጌ ማስታወሻ

ቃል በቃል “የሳኦል ወንድ ልጅ።”
ቃል በቃል “እጆቹ ዛሉ።”
ወይም “ነፍስህን።”
ወይም “ነፍሴን ከመከራ ሁሉ በተቤዠልኝ።”