ሁለተኛ ሳሙኤል 5:1-25

  • ዳዊት በመላው እስራኤል ላይ ነገሠ (1-5)

  • ኢየሩሳሌም ተያዘች (6-16)

    • የዳዊት ከተማ ተብላ የምትጠራው ጽዮን (7)

  • ዳዊት ፍልስጤማውያንን ድል አደረገ (17-25)

5  ከጊዜ በኋላ የእስራኤል ነገዶች በሙሉ በኬብሮን+ ወደሚገኘው ወደ ዳዊት መጥተው እንዲህ አሉት፦ “እንግዲህ እኛ የአጥንትህ ፍላጭ፣ የሥጋህም ቁራጭ ነን።*+  ባለፉት ዘመናት ሳኦል ንጉሣችን በነበረበት ጊዜ እስራኤል ወደ ጦርነት ሲወጣ የምትመራው* አንተ ነበርክ።+ ይሖዋም ‘ሕዝቤን እስራኤልን እረኛ ሆነህ ትጠብቃለህ፣ በእስራኤልም ላይ መሪ ትሆናለህ’ ብሎህ ነበር።”+  በመሆኑም የእስራኤል ሽማግሌዎች በሙሉ ንጉሡ ወዳለበት ወደ ኬብሮን መጡ፤ ንጉሥ ዳዊትም በኬብሮን ከእነሱ ጋር በይሖዋ ፊት ቃል ኪዳን ገባ።+ እነሱም ዳዊትን በእስራኤል ላይ ንጉሥ አድርገው ቀቡት።+  ዳዊት በነገሠ ጊዜ 30 ዓመቱ ነበር፤ ለ40 ዓመትም ገዛ።+  በኬብሮን ተቀምጦ በይሁዳ ላይ ለ7 ዓመት ከ6 ወር ገዛ፤ በኢየሩሳሌም+ ሆኖ ደግሞ በመላው እስራኤልና ይሁዳ ላይ ለ33 ዓመት ገዛ።  ዳዊትና ሰዎቹም በምድሪቱ የሚኖሩትን ኢያቡሳውያን+ ለመውጋት ወደ ኢየሩሳሌም ዘመቱ። እነሱም ዳዊትን “ፈጽሞ ወደዚህ አትገባም! ዕውሮችና ሽባዎች እንኳ ያባርሩሃል” በማለት ተሳለቁበት። ይህን ያሉት ‘ዳዊት ፈጽሞ ወደዚህ አይገባም’ ብለው ስላሰቡ ነበር።+  ይሁን እንጂ ዳዊት በአሁኑ ጊዜ የዳዊት ከተማ+ ተብላ የምትጠራውን የጽዮንን ምሽግ ያዘ።  ስለሆነም በዚያን ቀን ዳዊት “በኢያቡሳውያን ላይ ጥቃት የሚሰነዝር ማንኛውም ሰው ዳዊት የሚጠላቸውን* ‘ሽባዎችንና ዕውሮችን’ ለመምታት በውኃ መውረጃው ቦይ በኩል ማለፍ አለበት!” አለ። “ዕውርና ሽባ ፈጽሞ ወደ ቤት አይገቡም” የሚባለውም በዚህ የተነሳ ነው።  ከዚያም ዳዊት በምሽጉ ውስጥ መኖር ጀመረ፤ ስፍራውም የዳዊት ከተማ ተብሎ ይጠራ ነበር፤* እሱም ከጉብታው*+ አንስቶ ወደ ውስጥ ዙሪያውን መገንባት ጀመረ።+ 10  በዚህ ሁኔታ ዳዊት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበረታ ሄደ፤+ የሠራዊት አምላክ ይሖዋም ከእሱ ጋር ነበር።+ 11  የጢሮስ ንጉሥ ኪራም+ መልእክተኞችን ወደ ዳዊት ላከ፤ እንዲሁም የአርዘ ሊባኖስ ሳንቃዎችን፣+ አናጺዎችንና ለቅጥር የሚሆን ድንጋይ የሚጠርቡ ሰዎችን ላከ፤ እነሱም ለዳዊት ቤት* መሥራት ጀመሩ።+ 12  ዳዊትም ይሖዋ በእስራኤል ላይ ንጉሥ አድርጎ እንዳጸናውና+ ስለ ሕዝቡ ስለ እስራኤል ሲል+ መንግሥቱን ከፍ ከፍ እንዳደረገለት+ አወቀ። 13  ዳዊት ከኬብሮን ከመጣ በኋላ በኢየሩሳሌም ተጨማሪ ቁባቶችን+ አስቀመጠ፤ እንዲሁም ሌሎች ሚስቶችን አገባ፤ ተጨማሪ ወንዶችና ሴቶች ልጆችም ተወለዱለት።+ 14  በኢየሩሳሌም ሳለ የተወለዱለት ልጆች ስም ይህ ነው፦ ሻሙአ፣ ሾባብ፣ ናታን፣+ ሰለሞን፣+ 15  ይብሃር፣ ኤሊሹዓ፣ ኔፌግ፣ ያፊአ፣ 16  ኤሊሻማ፣ ኤሊያዳ እና ኤሊፌሌት። 17  ፍልስጤማውያንም በሙሉ ዳዊት በእስራኤል ላይ ንጉሥ ሆኖ መቀባቱን+ ሲሰሙ እሱን ፍለጋ ወጡ።+ ዳዊትም ይህን ሲሰማ ወደ ምሽጉ ወረደ።+ 18  ከዚያም ፍልስጤማውያን መጥተው በረፋይም ሸለቆ*+ ተበታትነው ሰፈሩ። 19  ዳዊትም “ወጥቼ ፍልስጤማውያንን ልግጠም? አንተስ በእጄ አሳልፈህ ትሰጣቸዋለህ?” ሲል ይሖዋን ጠየቀ።+ ይሖዋም ዳዊትን “አዎ ውጣ፤ እኔም በእርግጥ ፍልስጤማውያንን በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁ” አለው።+ 20  በመሆኑም ዳዊት ወደ በዓልጰራጺም መጥቶ በዚያ መታቸው። እሱም “ይሖዋ፣ ውኃ እንደጣሰው ግድብ ጠላቶቼን በፊቴ ደረማመሳቸው” አለ።+ ከዚህም የተነሳ ያን ቦታ በዓልጰራጺም*+ ብሎ ጠራው። 21  ፍልስጤማውያንም ጣዖቶቻቸውን በዚያ ጥለው ሸሹ፤ ዳዊትና ሰዎቹም ወሰዷቸው።* 22  ከጊዜ በኋላ ፍልስጤማውያን እንደገና ወደ ረፋይም ሸለቆ*+ መጥተው ተበታትነው ሰፈሩ። 23  ዳዊትም ይሖዋን ጠየቀ፤ እሱ ግን እንዲህ አለው፦ “በቀጥታ አትውጣ። ይልቁንም ከኋላቸው ዞረህ በባካ* ቁጥቋጦዎቹ ፊት ለፊት ግጠማቸው። 24  በባካ ቁጥቋጦዎቹ አናት ላይ የሰልፍ ድምፅ ስትሰማ ቆራጥ እርምጃ ውሰድ፤ ምክንያቱም ይህ በሚሆንበት ጊዜ ይሖዋ የፍልስጤማውያንን ሠራዊት ለመምታት በፊትህ ወጥቷል ማለት ነው።” 25  በመሆኑም ዳዊት ልክ ይሖዋ እንዳዘዘው አደረገ፤ ፍልስጤማውያንንም ከጌባ+ አንስቶ እስከ ጌዜር+ ድረስ መታቸው።+

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “የሥጋ ዘመዶችህ ነን።”
ቃል በቃል “እስራኤልን የምታስወጣውና የምታስገባው።”
ወይም “የዳዊት ነፍስ የምትጠላቸውን።”
“ስፍራውንም የዳዊት ከተማ ብሎ ጠራው” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ከሚሎ።” “መሙላት” የሚል ትርጉም ያለው የዕብራይስጥ ቃል ነው።
ወይም “ቤተ መንግሥት።”
ወይም “ረባዳማ ሜዳ።”
“በመደረማመስ የተዋጣለት” የሚል ትርጉም አለው።
ዳዊትና ሰዎቹ ጣዖታቱን ወስደው እንዳጠፏቸው ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። አንደኛ ዜና 14:12ን ተመልከት።
ወይም “ረባዳማ ሜዳ።”
“ባካ” የሚለው ስም የዕብራይስጥ ቃል ነው። የተክሉ ዓይነት በትክክል አይታወቅም።