ሁለተኛ ሳሙኤል 6:1-23

  • ታቦቱ ወደ ኢየሩሳሌም ተወሰደ (1-23)

    • ዖዛ ታቦቱን በመያዙ ተቀሰፈ (6-8)

    • ሜልኮል ዳዊትን ናቀችው (16, 20-23)

6  ዳዊትም በእስራኤል ውስጥ ያሉትን ምርጥ የሆኑ ተዋጊዎች በሙሉ በድጋሚ ሰበሰበ፤ ብዛታቸውም 30,000 ነበር።  ከዚያም አብሮት ከነበረው ሕዝብ ሁሉ ጋር ተነስቶ የእውነተኛውን አምላክ ታቦት+ ለማምጣት በዙፋን ላይ ከኪሩቤል በላይ የተቀመጠው*+ የሠራዊት ጌታ የይሖዋ+ ስም ወደተጠራበት ወደ በዓለይሁዳ ሄደ።  ይሁን እንጂ የእውነተኛውን አምላክ ታቦት በኮረብታ ላይ ካለው ከአቢናዳብ+ ቤት ለማምጣት በአዲስ ሠረገላ ላይ ጫኑት፤+ የአቢናዳብ ልጆች የሆኑት ዖዛ እና አሂዮም አዲሱን ሠረገላ ይነዱ ነበር።  በመሆኑም የእውነተኛውን አምላክ ታቦት በኮረብታ ላይ ከነበረው ከአቢናዳብ ቤት ይዘው ጉዞ ጀመሩ፤ አሂዮም ከታቦቱ ፊት ፊት ይሄድ ነበር።  ዳዊትና መላው የእስራኤል ቤት ከጥድ እንጨት በተሠሩ የተለያዩ መሣሪያዎች፣ በበገና፣ በባለ አውታር መሣሪያዎች፣+ በአታሞ፣+ በጸናጽልና በሲምባል*+ ታጅበው በይሖዋ ፊት በደስታ ይጨፍሩ ነበር።  ወደ ናኮን አውድማ ሲደርሱ ግን ከብቶቹ ታቦቱን ሊጥሉት ተቃርበው ስለነበር ዖዛ እጁን ዘርግቶ የእውነተኛውን አምላክ ታቦት ያዘ።+  በዚህ ጊዜ የይሖዋ ቁጣ በዖዛ ላይ ነደደ፤ በመሆኑም ዖዛ እንዲህ ያለ የድፍረት ድርጊት+ በመፈጸሙ እውነተኛው አምላክ እዚያው ቀሰፈው፤+ እሱም በእውነተኛው አምላክ ታቦት አጠገብ እዚያው ሞተ።  ሆኖም የይሖዋ ቁጣ በዖዛ ላይ ስለነደደ ዳዊት ተበሳጨ፤* ያም ቦታ እስከ ዛሬ ድረስ ጴሬዝዖዛ* ተብሎ ይጠራል።  ዳዊትም በዚያን ዕለት ይሖዋን ፈርቶ+ “ታዲያ የይሖዋ ታቦት እንዴት ወደ እኔ ይመጣል?” አለ።+ 10  ዳዊትም የይሖዋ ታቦት እሱ ወዳለበት ወደ ዳዊት ከተማ+ እንዲመጣ አልፈለገም። ይልቁንም ታቦቱ የጌት ሰው ወደሆነው ወደ ኦቤድዔዶም+ ቤት እንዲወሰድ አደረገ። 11  የይሖዋም ታቦት የጌት ሰው በሆነው በኦቤድዔዶም ቤት ለሦስት ወር ተቀመጠ፤ ይሖዋም ኦቤድዔዶምን እና ቤተሰቡን በሙሉ ባረከ።+ 12  በመጨረሻም ዳዊት “ይሖዋ በእውነተኛው አምላክ ታቦት የተነሳ የኦቤድዔዶምን ቤትና የእሱ የሆነውን ነገር ሁሉ ባርኳል” ተብሎ ተነገረው። ስለሆነም ዳዊት የእውነተኛውን አምላክ ታቦት ከኦቤድዔዶም ቤት ወደ ዳዊት ከተማ በታላቅ ደስታ ለማምጣት ሄደ።+ 13  የይሖዋን ታቦት የተሸከሙት+ ሰዎች ስድስት እርምጃ ከተራመዱ በኋላ ዳዊት አንድ በሬና አንድ የሰባ ጥጃ ሠዋ። 14  ዳዊትም በሙሉ ኃይሉ በይሖዋ ፊት ይጨፍር ነበር፤ በዚህ ጊዜ ሁሉ ከበፍታ የተሠራ ኤፉድ ለብሶ* ነበር።+ 15  ዳዊትና የእስራኤል ቤት በሙሉ የይሖዋን ታቦት+ በእልልታና+ በቀንደ መለከት+ አጅበው አመጡት። 16  ይሁንና የይሖዋ ታቦት ወደ ዳዊት ከተማ በመጣ ጊዜ የሳኦል ልጅ ሜልኮል+ በመስኮት ሆና ወደ ታች ተመለከተች፤ እሷም ንጉሥ ዳዊት በይሖዋ ፊት ሲዘልና ሲጨፍር አይታ በልቧ ናቀችው።+ 17  በዚህ መንገድ የይሖዋን ታቦት አምጥተው ዳዊት በተከለለት ድንኳን ውስጥ በተዘጋጀለት ቦታ ላይ አስቀመጡት።+ ከዚያም ዳዊት የሚቃጠሉ መባዎችንና+ የኅብረት መሥዋዕቶችን+ በይሖዋ ፊት አቀረበ።+ 18  ዳዊት የሚቃጠሉትን መባዎችና የኅብረት መሥዋዕቶቹን አቅርቦ ሲጨርስ ሕዝቡን በሠራዊት ጌታ በይሖዋ ስም ባረከ። 19  በተጨማሪም ለሕዝቡ ሁሉ ይኸውም ለተሰበሰቡት እስራኤላውያን በሙሉ፣ ለእያንዳንዱ ወንድና ሴት አንድ ዳቦ፣ አንድ የቴምር ጥፍጥፍና አንድ የዘቢብ ጥፍጥፍ አከፋፈለ፤ ከዚያም ሕዝቡ ሁሉ ወደየቤቱ ሄደ። 20  በዚህ ጊዜ ዳዊት የራሱን ቤት ለመባረክ ተመለሰ፤ የሳኦል ልጅ ሜልኮልም+ ዳዊትን ልትቀበለው ወጥታ “ዛሬ የእስራኤል ንጉሥ እንደ አንድ ተራ ሰው በአገልጋዮቹ ሴት ባሪያዎች ፊት እርቃኑን በመሆኑ እንዴት ራሱን አስከብሯል!” አለችው።+ 21  በዚህ ጊዜ ዳዊት ሜልኮልን እንዲህ አላት፦ “የጨፈርኩት እኮ ከአባትሽና በቤቱ ካሉት ሁሉ ይልቅ እኔን መርጦ በይሖዋ ሕዝብ በእስራኤል ላይ መሪ አድርጎ በሾመኝ በይሖዋ ፊት ነው፤+ አሁንም ቢሆን በይሖዋ ፊት እጨፍራለሁ። 22  እንዲያውም ከዚህ የባሰ ራሴን አዋርዳለሁ፤ ራሴንም እንቃለሁ። ሆኖም አንቺ በጠቀስሻቸው ሴት ባሪያዎች ፊት እከበራለሁ።” 23  የሳኦል ልጅ ሜልኮልም+ እስከሞተችበት ቀን ድረስ ልጅ አልወለደችም።

የግርጌ ማስታወሻ

“በኪሩቤል መካከል የተቀመጠው” ማለትም ሊሆን ይችላል።
እዚህ ላይ የገባው የዕብራይስጥ ቃል፣ እርስ በርሱ ሲጋጭ ኃይለኛ ድምፅ የሚያወጣን ክብ ቅርጽ ያለው ከብረት የተሠራ የሙዚቃ መሣሪያ ያመለክታል።
ወይም “ዳዊት አዘነ።”
“በዖዛ ላይ መገንፈል” የሚል ትርጉም አለው።
ቃል በቃል “ታጥቆ።”