ሁለተኛ ሳሙኤል 7:1-29

  • ዳዊት ቤተ መቅደሱን እንደማይሠራ ተነገረው (1-7)

  • ለዳዊት የመንግሥት ቃል ኪዳን ተገባለት (8-17)

  • ዳዊት ያቀረበው የምስጋና ጸሎት (18-29)

7  ንጉሡ በራሱ ቤት* መኖር በጀመረና+ ይሖዋም በዙሪያው ካሉት ጠላቶቹ ሁሉ እረፍት በሰጠው ጊዜ  ነቢዩ ናታንን+ “የእውነተኛው አምላክ ታቦት በድንኳን ውስጥ+ ተቀምጦ ሳለ ይኸው እኔ ከአርዘ ሊባኖስ በተሠራ+ ቤት ውስጥ እየኖርኩ ነው” አለው።  ናታንም ንጉሡን “ይሖዋ ከአንተ ጋር ስለሆነ ሄደህ በልብህ ያለውን ነገር ሁሉ አድርግ” አለው።+  በዚያው ሌሊት የይሖዋ ቃል እንዲህ ሲል ወደ ናታን መጣ፦  “ሂድና አገልጋዬን ዳዊትን እንዲህ በለው፦ ‘ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “አንተ የምኖርበትን ቤት መሥራት ይኖርብሃል?+  እስራኤላውያንን ከግብፅ ካወጣሁበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በድንኳንና በማደሪያ ድንኳን እጓዝ ነበር እንጂ በቤት ውስጥ አልኖርኩም።+  ከእስራኤላውያን* ሁሉ ጋር በተጓዝኩበት ጊዜ በሙሉ ሕዝቤን እስራኤልን እረኛ ሆነው እንዲጠብቁ ከሾምኳቸው የነገድ መሪዎች መካከል ‘በአርዘ ሊባኖስ ቤት ያልሠራህልኝ ለምንድን ነው?’ ያልኩት ማን አለ?”’  አሁንም አገልጋዬን ዳዊትን እንዲህ በለው፦ ‘የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “በሕዝቤ በእስራኤል ላይ መሪ እንድትሆን+ መንጋ ከምትጠብቅበት ስፍራ+ ወሰድኩህ።  እኔም በምትሄድበት ሁሉ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤+ ጠላቶችህንም ሁሉ ከፊትህ አጠፋለሁ፤+ ስምህንም በምድር ላይ እንዳሉ ታላላቅ ሰዎች ስም ገናና አደርገዋለሁ።+ 10  ለሕዝቤ ለእስራኤል ቦታ እሰጣቸዋለሁ፤ ተረጋግተው እንዲቀመጡም አደርጋለሁ፤ በዚያም ይኖራሉ፤ ከእንግዲህም የሚረብሻቸው አይኖርም፤ ክፉዎች እንደቀድሞው ዳግመኛ አይጨቁኗቸውም፤+ 11  በሕዝቤ በእስራኤል ላይ መሳፍንትን ከሾምኩበት+ ጊዜ አንስቶ ሲያደርጉ እንደነበሩት አያደርጉባቸውም። እኔም ከጠላቶችህ ሁሉ እረፍት እሰጥሃለሁ።+ “‘“በተጨማሪም ይሖዋ ቤት* እንደሚሠራልህ ይሖዋ ራሱ ነግሮሃል።+ 12  የሕይወት ዘመንህ አብቅቶ+ ከአባቶችህ ጋር በምታንቀላፋበት ጊዜ ከአንተ በኋላ ከአብራክህ የሚወጣውን ዘርህን አስነሳለሁ፤ መንግሥቱንም አጸናለሁ።+ 13  ለስሜ የሚሆን ቤት የሚሠራልኝ እሱ ነው፤+ እኔም የመንግሥቱን ዙፋን ለዘላለም አጸናለሁ።+ 14  አባት እሆነዋለሁ፤ እሱም ልጄ ይሆናል።+ ጥፋት በሚያጠፋበት ጊዜም በሰዎች በትር፣ በሰው* ልጆች አለንጋ እቀጣዋለሁ።+ 15  ከፊትህ ካስወገድኩት ከሳኦል ላይ ታማኝ ፍቅሬን እንደወሰድኩ+ ከእሱ ላይ አይወሰድም። 16  ቤትህና መንግሥትህ ለዘላለም በፊትህ ጸንቶ ይኖራል፤ ዙፋንህም ለዘላለም የጸና ይሆናል።”’”+ 17  ናታንም ይህን ቃል ሁሉና ይህን ራእይ በሙሉ ለዳዊት ነገረው።+ 18  በዚህ ጊዜ ንጉሥ ዳዊት ገብቶ በይሖዋ ፊት ተቀመጠ፤ እንዲህም አለ፦ “ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ ኧረ ለመሆኑ እኔ ማን ነኝ? እስከዚህ ድረስ ያደረስከኝስ ቤቴ ምን ስለሆነ ነው?+ 19  ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ ይህ ሳያንስ ስለ አገልጋይህ ቤት ገና ወደፊት የሚሆነውንም ነገር ተናገርክ፤ ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ ይህ ለሰው ዘር ሁሉ የተሰጠ መመሪያ* ነው። 20  ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ ታዲያ አገልጋይህ ዳዊት ከዚህ በላይ ምን ሊልህ ይችላል? አንተ በሚገባ ታውቀኝ የለ?+ 21  ለቃልህ ስትል፣ ከልብህ ጋር በሚስማማ ሁኔታ* እነዚህን ሁሉ ታላላቅ ነገሮች ፈጽመሃል፤ እንዲሁም ለአገልጋይህ ገልጠህለታል።+ 22  ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ አንተ በእርግጥም ታላቅ+ የሆንከው ለዚህ ነው። እንደ አንተ ያለ ማንም የለም፤+ ከአንተ በቀር አምላክ የለም፤+ በጆሯችን የሰማነው ነገር ሁሉ ይህን ያረጋግጣል። 23  በምድር ላይ እንደ ሕዝብህ እንደ እስራኤል ያለ ሌላ ብሔር ማን አለ?+ አምላክ ሄዶ ለእነሱ ሲል ታላላቅና አስፈሪ ነገሮችን+ በመፈጸም እንዲሁም ስሙን በማስጠራት+ ሕዝቡ አድርጎ ዋጃቸው።+ ከግብፅ ለዋጀኸው ሕዝብ ስትል ብሔራትንና አማልክታቸውን አባረርክ። 24  ሕዝብህን እስራኤልን እስከ ወዲያኛው የራስህ ሕዝብ አድርገህ አጸናኸው፤+ ይሖዋ ሆይ፣ አንተም አምላኩ ሆንክ።+ 25  “አሁንም ይሖዋ አምላክ ሆይ፣ አገልጋይህንና ቤቱን በተመለከተ የገባኸውን ቃል እስከ ወዲያኛው ፈጽም፤ ቃል እንደገባኸውም አድርግ።+ 26  ሰዎች ‘የሠራዊት ጌታ ይሖዋ በእስራኤል ላይ አምላክ ነው’ እንዲሉ ስምህ ለዘላለም ከፍ ከፍ ይበል፤+ የአገልጋይህም የዳዊት ቤት በፊትህ የጸና ይሁን።+ 27  የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ‘ለአንተ ቤት* እሠራልሃለሁ’+ በማለት ለአገልጋይህ ራእይ ገልጠህለታል። አገልጋይህ ይህን ጸሎት ወደ አንተ ለማቅረብ ድፍረት* ያገኘው በዚህ ምክንያት ነው። 28  አሁንም ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ እውነተኛው አምላክ አንተ ነህ፤ ቃልህ እውነት ነው፤+ ለአገልጋይህም እነዚህን መልካም ነገሮች ለማድረግ ቃል ገብተህለታል። 29  በመሆኑም የአገልጋይህን ቤት እባክህ ባርክ፤ በፊትህም ለዘላለም የጸና ይሁን፤+ ምክንያቱም ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ራስህ ቃል ገብተሃል፤ በአንተም በረከት የአገልጋይህ ቤት ለዘላለም የተባረከ ይሁን።”+

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “በቤተ መንግሥቱ።”
ቃል በቃል “ከእስራኤል ወንዶች ልጆች።”
ወይም “ሥርወ መንግሥት።”
“በአዳም” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ሕግ።”
ወይም “ከፈቃድህ ጋር በሚስማማ ሁኔታ።”
ወይም “ሥርወ መንግሥት።”
ቃል በቃል “ልብ።”