ሁለተኛ ሳሙኤል 8:1-18

  • ዳዊት የተቀዳጃቸው ድሎች (1-14)

  • የዳዊት አስተዳደር (15-18)

8  ከጊዜ በኋላም ዳዊት ፍልስጤማውያንን+ ድል በማድረግ በቁጥጥር ሥር አዋላቸው፤+ መተግአማህንም ከፍልስጤማውያን እጅ ወሰደ።  ሞዓባውያንንም ድል አደረጋቸው፤+ እነሱንም መሬት ላይ አጋድሞ በገመድ ለካቸው። ይህን ያደረገው በገመዱ ርዝመት ሁለት እጅ የሚሆኑትን ለመግደል እንዲሁም በገመዱ ርዝመት አንድ እጅ የሚሆኑትን በሕይወት ለመተው ነው።+ ሞዓባውያንም የዳዊት አገልጋዮች ሆኑ፤ ግብርም ገበሩለት።+  የሬሆብ ልጅ የሆነው የጾባህ+ ንጉሥ ሃዳድኤዜር በኤፍራጥስ ወንዝ+ ላይ ያለውን የበላይነት ዳግመኛ ለማረጋገጥ በሄደ ጊዜ ዳዊት ድል አደረገው።  ዳዊትም ከእሱ ላይ 1,700 ፈረሰኞችንና 20,000 እግረኛ ወታደሮችን ማረከ። ከዚያም ዳዊት 100 የሠረገላ ፈረሶችን ብቻ አስቀርቶ ሌሎቹን በሙሉ ቋንጃቸውን ቆረጠ።+  የደማስቆዎቹ ሶርያውያን፣+ የጾባህን ንጉሥ ሃዳድኤዜርን ለመርዳት በመጡ ጊዜ ዳዊት ከሶርያውያን መካከል 22,000 ሰዎችን ገደለ።+  ከዚያም ዳዊት በደማስቆ ሶርያ የጦር ሰፈሮች አቋቋመ፤ ሶርያውያንም የዳዊት አገልጋዮች ሆኑ፤ ግብርም ገበሩለት። ይሖዋ ዳዊትን በሄደበት ሁሉ ድል አቀዳጀው።*+  በተጨማሪም ዳዊት ከሃዳድኤዜር አገልጋዮች ላይ ከወርቅ የተሠሩ ክብ ጋሻዎችን ወሰደ፤ ወደ ኢየሩሳሌምም አመጣቸው።+  ደግሞም ንጉሥ ዳዊት የሃዳድኤዜር ከተሞች ከሆኑት ከቤጣህ እና ከበሮታይ እጅግ ብዙ መዳብ ወሰደ።  በዚህ ጊዜ የሃማት+ ንጉሥ ቶአይ ዳዊት የጾባህን ንጉሥ የሃዳድኤዜርን+ ሠራዊት በሙሉ ድል እንዳደረገ ሰማ። 10  በመሆኑም ቶአይ የንጉሥ ዳዊትን ደህንነት እንዲጠይቅና ከሃዳድኤዜር ጋር ተዋግቶ ድል በማድረጉ የተሰማውን ደስታ እንዲገልጽለት ልጁን ዮራምን ወደ ዳዊት ላከው (ምክንያቱም ሃዳድኤዜር ከቶአይ ጋር ብዙ ጊዜ ይዋጋ ነበር)፤ እሱም ከብር፣ ከወርቅና ከመዳብ የተሠሩ ዕቃዎችን ይዞ መጣ። 11  ንጉሥ ዳዊት እነዚህን ዕቃዎች ተገዢዎቹ ካደረጋቸው ብሔራት ሁሉ ላይ ወስዶ ከቀደሰው ብርና ወርቅ ጋር አብሮ ለይሖዋ ቀደሳቸው፤+ 12  ዕቃዎቹም ከሶርያ፣ ከሞዓብ፣+ ከአሞናውያን፣ ከፍልስጤማውያንና+ ከአማሌቃውያን+ ላይ የወሰዳቸው እንዲሁም የሬሆብ ልጅ ከሆነው ከጾባህ ንጉሥ ከሃዳድኤዜር+ ላይ የማረካቸው ናቸው። 13  ዳዊት በጨው ሸለቆ 18,000 ኤዶማውያንን ገድሎ ከተመለሰ በኋላ ስሙ ገነነ።+ 14  በኤዶምም የጦር ሰፈሮችን አቋቋመ። በመላው ኤዶም የጦር ሰፈሮችን ከማቋቋሙም ሌላ ኤዶማውያን ሁሉ የዳዊት አገልጋዮች ሆኑ።+ ይሖዋም ዳዊትን በሄደበት ሁሉ ድል አቀዳጀው።*+ 15  ዳዊት በመላው እስራኤል ላይ መግዛቱን ቀጠለ፤+ ለሕዝቡም ሁሉ+ ፍትሕንና ጽድቅን አሰፈነላቸው።+ 16  የጽሩያ ልጅ ኢዮዓብ+ የሠራዊቱ አዛዥ ነበር፤ የአሂሉድ ልጅ ኢዮሳፍጥ+ ታሪክ ጸሐፊ ነበር። 17  የአኪጡብ ልጅ ሳዶቅና+ የአብያታር ልጅ አሂሜሌክ ካህናት ነበሩ፤ ሰራያህ ደግሞ ጸሐፊ ነበር። 18  የዮዳሄ ልጅ በናያህ+ የከሪታውያንና የጴሌታውያን+ አዛዥ ነበር። የዳዊት ወንዶች ልጆችም ዋና ኃላፊዎች* ሆኑ።

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “አዳነው።”
ወይም “አዳነው።”
ቃል በቃል “ካህናት።”