ለቆሮንቶስ ሰዎች የተጻፈ ሁለተኛው ደብዳቤ 4:1-18
4 ስለዚህ በተደረገልን ምሕረት የተነሳ ይህ አገልግሎት ስላለን ተስፋ አንቆርጥም።
2 ከዚህ ይልቅ አሳፋሪ የሆኑትን ስውር ነገሮች ትተናል፤ በተንኮል አንመላለስም፤ የአምላክንም ቃል አንበርዝም፤+ ነገር ግን እውነትን በመግለጥ በአምላክ ፊት የሰውን ሁሉ ሕሊና በሚማርክ መንገድ ራሳችንን ብቁ አድርገን እናቀርባለን።+
3 እንግዲህ የምናውጀው ምሥራች በእርግጥ የተሸፈነ ከሆነ የተሸፈነው ወደ ጥፋት እያመሩ ላሉት ነው፤
4 የአምላክ አምሳል ስለሆነው ስለ ክርስቶስ+ የሚገልጸውና ክብራማ የሆነው ምሥራች የሚፈነጥቀው ብርሃን በእነሱ ላይ እንዳያበራ+ የዚህ ሥርዓት* አምላክ+ የማያምኑትን ሰዎች አእምሮ አሳውሯል።+
5 እኛ የምንሰብከው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ መሆኑንና እኛም ስለ ኢየሱስ ስንል የእናንተ ባሪያዎች መሆናችንን እንጂ ስለ ራሳችን አይደለምና።
6 “በጨለማ ውስጥ ብርሃን ይብራ” ያለው አምላክ ነውና፤+ ስለሆነም በክርስቶስ ፊት አማካኝነት፣ በልባችን ውስጥ ስለ አምላክ አስደናቂ እውቀት ይፈነጥቅ ዘንድ በልባችን ላይ ብርሃን አብርቷል።+
7 ይሁን እንጂ ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነው ኃይል ከእኛ ሳይሆን ከአምላክ የመነጨ መሆኑ ይታወቅ ዘንድ+ ይህ ውድ ሀብት+ በሸክላ ዕቃ+ ውስጥ አለን።
8 በየአቅጣጫው ብንደቆስም መፈናፈኛ አናጣም፤ ግራ ብንጋባም መውጫ ቀዳዳ አናጣም፤*+
9 ስደት ቢደርስብንም አልተተውንም፤+ በጭንቀት ብንዋጥም* አንጠፋም።+
10 የኢየሱስ ሕይወት በእኛም ሰውነት እንዲገለጥ በኢየሱስ ላይ የደረሰውን ለሞት ሊዳርግ የሚችል መከራ ዘወትር በሰውነታችን እንሸከማለን።+
11 የኢየሱስ ሕይወት ሟች በሆነው ሥጋችንም ይገለጥ ዘንድ እኛ ሕያዋን የሆን ለኢየሱስ ስንል ዘወትር ከሞት ጋር እንፋጠጣለንና።+
12 ስለሆነም በእኛ ላይ ሞት፣ በእናንተ ላይ ግን ሕይወት እየሠራ ነው።
13 “አመንኩ፤ ስለዚህም ተናገርኩ” ተብሎ ተጽፏል።+ እኛም እንዲህ ዓይነት የእምነት መንፈስ ስላለን እናምናለን፤ ስለዚህም እንናገራለን፤
14 ኢየሱስን ያስነሳው እሱ፣ እኛንም ከኢየሱስ ጋር እንደሚያስነሳንና ከእናንተ ጋር አንድ ላይ በፊቱ እንደሚያቀርበን እናውቃለን።+
15 ይህ ሁሉ የሆነው ለእናንተ ሲባል ነውና፤ ይኸውም ብዙ ሰዎች ለአምላክ ክብር ምስጋና እያቀረቡ ስለሆነ የተትረፈረፈው ጸጋ ይበልጥ እንዲበዛ ነው።+
16 ስለዚህ ተስፋ አንቆርጥም፤ ምንም እንኳ ውጫዊው ሰውነታችን እየመነመነ ቢሄድም ውስጣዊው ሰውነታችን ከቀን ወደ ቀን እየታደሰ እንደሚሄድ ምንም ጥርጥር የለውም።
17 የሚደርስብን መከራ* ጊዜያዊና ቀላል ቢሆንም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሄድና ዘላለማዊ የሆነ ክብር ያስገኝልናል፤+
18 ስለዚህ ዓይናችን እንዲያተኩር የምናደርገው በሚታዩት ነገሮች ላይ ሳይሆን በማይታዩት ነገሮች ላይ ነው።+ የሚታዩት ጊዜያዊ ናቸውና፤ የማይታዩት ግን ዘላለማዊ ናቸው።
የግርጌ ማስታወሻ
^ ወይም “የዚህ ዘመን።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
^ “ተስፋ አንቆርጥም” ማለትም ሊሆን ይችላል።
^ ቃል በቃል “ብንወድቅም።”
^ ወይም “ፈተና።”