ለቆሮንቶስ ሰዎች የተጻፈ ሁለተኛው ደብዳቤ 6:1-18

  • የአምላክን ጸጋ አላግባብ መጠቀም አይገባም (1, 2)

  • ስለ ጳውሎስ አገልግሎት የተሰጠ መግለጫ (3-13)

  • “አቻ ባልሆነ መንገድ አትጠመዱ” (14-18)

6  ደግሞም ከእሱ ጋር አብረን የምንሠራ+ እንደመሆናችን መጠን የአምላክን ጸጋ ከተቀበላችሁ በኋላ ዓላማውን እንዳትስቱ እናሳስባችኋለን።+  እሱ “ሞገስ በማሳይበት ጊዜ ሰምቼሃለሁ፤ በመዳንም ቀን ረድቼሃለሁ” ይላልና።+ እነሆ፣ አምላክ ሞገስ የሚያሳይበት ልዩ ጊዜ አሁን ነው። እነሆ፣ የመዳን ቀን አሁን ነው።  አገልግሎታችን እንከን እንዳይገኝበት በምንም መንገድ ማሰናከያ እንዲኖር አናደርግም፤+  ከዚህ ይልቅ በሁሉም ነገር ራሳችንን ብቁ የአምላክ አገልጋዮች አድርገን እናቀርባለን፤+ ይህን የምናደርገው በብዙ ነገር በመጽናት፣ በመከራ፣ በእጦት፣ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች፣+  በድብደባ፣ በእስር፣+ በሁከት፣ በከባድ ሥራ፣ እንቅልፍ አጥቶ በማደርና ጾም በመዋል ነው።+  የአምላክ አገልጋዮች መሆናችንን በንጽሕና፣ በእውቀት፣ በትዕግሥት፣+ በደግነት፣+ በመንፈስ ቅዱስ፣ ግብዝነት በሌለው ፍቅር፣+  እውነት የሆነውን በመናገርና በአምላክ ኃይል እናሳያለን።+ እንዲሁም በቀኝ እጅና* በግራ እጅ* የጽድቅ መሣሪያዎችን በመያዝ፣+  ክብርንም ሆነ ውርደትን እንዲሁም ነቀፋንም ሆነ ምስጋናን በመቀበል የአምላክ አገልጋዮች መሆናችንን እናስመሠክራለን። እውነተኞች ሆነን ሳለን እንደ አታላዮች ተቆጥረናል፤  በሚገባ የታወቅን ሆነን ሳለን እንደማንታወቅ ተቆጥረናል፤ የምንሞት ስንመስል* እነሆ፣ ሕያዋን ነን፤+ ብንቀጣም ለሞት አልተዳረግንም፤+ 10  ሐዘንተኞች ተደርገን ብንታይም ምንጊዜም ደስተኞች ነን፤ እንደ ድሆች ብንቆጠርም ብዙዎችን ባለጸጋ እያደረግን ነው፤ ምንም የሌለን ብንመስልም ሁሉ ነገር አለን።+ 11  የቆሮንቶስ ወንድሞች ሆይ፣ በግልጽ ነግረናችኋል፤ ልባችንም ወለል ብሎ ተከፍቶላችኋል። 12  እኛ ፍቅራችንን አልነፈግናችሁም፤+ እናንተ ግን ጥልቅ ፍቅራችሁን ነፍጋችሁናል። 13  ስለዚህ ልጆቼን እንደማናግር ሆኜ አናግራችኋለሁ፤ እናንተም በአጸፋው ልባችሁን ወለል አድርጋችሁ ክፈቱ።+ 14  ከማያምኑ ጋር አቻ ባልሆነ መንገድ አትጠመዱ።*+ ጽድቅ ከዓመፅ ጋር ምን ኅብረት አለው?+ ወይስ ብርሃን ከጨለማ ጋር ምን ያገናኘዋል?+ 15  በተጨማሪም በክርስቶስና በቤልሆር* መካከል ምን ስምምነት አለ?+ ወይስ የሚያምን ከማያምን ጋር ምን ድርሻ አለው?+ 16  እንዲሁም የአምላክ ቤተ መቅደስ ከጣዖቶች ጋር ምን ስምምነት አለው?+ እኛ የሕያው አምላክ ቤተ መቅደስ ነንና፤+ አምላክ “በመካከላቸው እኖራለሁ፤+ ከእነሱም ጋር እሄዳለሁ፤ እኔ አምላካቸው እሆናለሁ፣ እነሱ ደግሞ ሕዝቤ ይሆናሉ” ብሎ እንደተናገረው ነው።+ 17  “‘ስለዚህ ከመካከላቸው ውጡና ራሳችሁን ለዩ’ ይላል ይሖዋ፤* ‘ርኩስ የሆነውንም ነገር አትንኩ’”፤*+ “‘እኔም እቀበላችኋለሁ።’”+ 18  “‘እኔ አባት እሆናችኋለሁ፤+ እናንተ ደግሞ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ትሆኑኛላችሁ’+ ይላል ሁሉን ቻይ የሆነው ይሖዋ።”*

የግርጌ ማስታወሻ

ጥቃት ለመሰንዘር ሊሆን ይችላል።
ለመከላከል ሊሆን ይችላል።
ወይም “ሞት ይገባቸዋል ስንባል።”
ወይም “አትቆራኙ።”
“የማይረባ” የሚል ትርጉም ካለው የዕብራይስጥ ቃል የመጣ ሲሆን ሰይጣንን ያመለክታል።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “መንካት አቁሙ።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።