ለቆሮንቶስ ሰዎች የተጻፈ ሁለተኛው ደብዳቤ 7:1-16

  • “ከሚያረክስ ነገር ሁሉ ራሳችንን እናንጻ” (1)

  • ጳውሎስ በቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የተነሳ የተሰማው ደስታ (2-4)

  • ቲቶ ጥሩ ዜና ይዞ መጣ (5-7)

  • አምላካዊ ሐዘንና ንስሐ መግባት (8-16)

7  ስለዚህ የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ እነዚህ ተስፋዎች ስላሉን+ ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ነገር ሁሉ ራሳችንን እናንጻ፤+ እንዲሁም አምላክን በመፍራት ቅድስናችንን ፍጹም እናድርግ።  በልባችሁ ውስጥ ቦታ ስጡን።+ እኛ ማንንም አልበደልንም፤ ማንንም አላበላሸንም፤ ማንንም መጠቀሚያ አላደረግንም።+  ይህን የምለው ልኮንናችሁ አይደለም። ከዚህ በፊት እንደነገርኳችሁ በልባችን ውስጥ ስለሆናችሁ ብንሞትም ሆነ ብንኖር አብረን ነን።  እናንተን በግልጽ ለማናገር ነፃነት ይሰማኛል። በእናንተ በጣም እኮራለሁ። እንዲሁም እጅግ ተጽናንቻለሁ፤ በመከራችንም ሁሉ ደስታዬ ወሰን የለውም።+  መቄዶንያ+ በደረስን ጊዜ በሁሉም አቅጣጫ መከራ ደረሰብን እንጂ ሰውነታችን* ምንም እረፍት አላገኘም፤ በውጭ ጠብ፣ በውስጥ ፍርሃት ነበረብን።  ይሁንና ያዘኑትን የሚያጽናናው አምላክ፣+ ቲቶ በመካከላችን በመገኘቱ እንድንጽናና አደረገን፤  የተጽናናነውም እሱ በመካከላችን በመገኘቱ ብቻ ሳይሆን እሱ በእናንተ ምክንያት ባገኘው መጽናኛ ጭምር ነው፤ ተመልሶ በመጣ ጊዜ እኔን ስለመናፈቃችሁ፣ ስለተሰማችሁ ጥልቅ ሐዘንና ለእኔ ስላላችሁ ልባዊ አሳቢነት* ነግሮናል፤ ስለዚህ ከበፊቱ ይበልጥ ደስ ብሎኛል።  በደብዳቤዬ አሳዝኛችሁ ቢሆን እንኳ+ በዚህ አልጸጸትም። መጀመሪያ ላይ ብጸጸት እንኳ፣ ደብዳቤው እንድታዝኑ ያደረጋችሁ ለአጭር ጊዜ ብቻ እንደሆነ ስለተረዳሁ  አሁን የምደሰተው እንዲያው በማዘናችሁ ሳይሆን ሐዘናችሁ ለንስሐ ስላበቃችሁ ነው። ያዘናችሁት ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ ነውና፤ በመሆኑም በእኛ የተነሳ ምንም ጉዳት አልደረሰባችሁም። 10  ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ ማዘን ለመዳን የሚያበቃ ንስሐ ያስገኛልና፤ ይህ ደግሞ ለጸጸት አይዳርግም፤+ የዚህ ዓለም ሐዘን ግን ሞት ያስከትላል። 11  አምላካዊ በሆነ መንገድ ማዘናችሁ እንዴት ለተግባር እንዳነሳሳችሁ ተመልከቱ! አዎ፣ አቋማችሁን ለማስተካከል እርምጃ እንድትወስዱ አነሳስቷችኋል፤ ደግሞም እንዴት ያለ ቁጣ፣ እንዴት ያለ ፍርሃት፣ እንዴት ያለ ጉጉት፣ እንዴት ያለ ቅንዓት እንዳስገኘ ተመልከቱ! በእርግጥም ስህተታችሁን ለማረም እርምጃ እንድትወስዱ አድርጓችኋል።+ በዚህ ጉዳይ ንጹሕ* መሆናችሁን በሁሉም ረገድ አስመሥክራችኋል። 12  ምንም እንኳ ለእናንተ ብጽፍም የጻፍኩት በደል ለሠራው+ ወይም በደል ለተፈጸመበት ሰው ብዬ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ለመልእክታችን በጎ ምላሽ ለመስጠት የምታደርጉት ጥረት በእናንተ ዘንድና በአምላክ ፊት ግልጽ ሆኖ እንዲታይ ነው። 13  እኛም የተጽናናነው ለዚህ ነው። ይሁን እንጂ ከመጽናናታችንም በተጨማሪ ሁላችሁም የቲቶ መንፈስ እንዲታደስ ስላደረጋችሁ በእሱ ደስታ እኛም ይበልጥ ተደስተናል። 14  ምክንያቱም ስለ እናንተ ለእሱ በኩራት ተናግሬ ቢሆን እንኳ አላሳፈራችሁኝም፤ ይሁንና ለእናንተ የተናገርነው ነገር በሙሉ እውነት እንደሆነ ሁሉ ለቲቶ በኩራት የተናገርነውም ነገር እውነት እንደሆነ ተረጋግጧል። 15  በተጨማሪም ሁላችሁም ያሳያችሁትን ታዛዥነት እንዲሁም በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ እንዴት እንደተቀበላችሁት ሲያስታውስ ለእናንተ ያለው ጥልቅ ፍቅር ጨምሯል።+ 16  እኔም በሁሉም መንገድ በእናንተ መተማመን* በመቻሌ እጅግ ደስ ብሎኛል።

የግርጌ ማስታወሻ

ቃል በቃል “ሥጋችን።”
ቃል በቃል “ለእኔ ስላላችሁ ቅንዓት።”
ወይም “ቅን።”
“መበረታታት” ማለትም ሊሆን ይችላል።