ሁለተኛ ነገሥት 22:1-20

  • ኢዮስያስ በይሁዳ ላይ ነገሠ (1, 2)

  • ቤተ መቅደሱ እንዲጠገን መመሪያ ሰጠ (3-7)

  • የሕጉ መጽሐፍ ተገኘ (8-13)

  • ሕልዳና ጥፋት እንደሚመጣ ትንቢት ተናገረች (14-20)

22  ኢዮስያስ+ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ስምንት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለ31 ዓመት ገዛ።+ እናቱ ይዲዳ ትባል ነበር፤ እሷም የቦጽቃት+ ሰው የሆነው የአዳያህ ልጅ ነበረች።  ኢዮስያስም በይሖዋ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር አደረገ፤ በአባቱም በዳዊት መንገድ ሄደ፤+ ወደ ቀኝም ወደ ግራም ፈቀቅ አላለም።  ንጉሥ ኢዮስያስ፣ በነገሠ በ18ኛው ዓመት የመሹላም ልጅ፣ የአዜልያ ልጅ የሆነውን ጸሐፊውን ሳፋንን እንዲህ ሲል ወደ ይሖዋ ቤት ላከው፦+  “ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ኬልቅያስ+ ሂድ፤ በር ጠባቂዎቹ ከሕዝቡ ላይ የሰበሰቡትንና ወደ ይሖዋ ቤት የገባውን ገንዘብ በአጠቃላይ እንዲሰበስብ አድርግ።+  ገንዘቡን በይሖዋ ቤት የሚከናወነውን ሥራ እንዲቆጣጠሩ ለተሾሙት ሰዎች ይስጧቸው፤ እነሱ ደግሞ በይሖዋ ቤት ውስጥ የፈረሰውን* ለሚጠግኑት ሠራተኞች ይስጡ፤+  ይኸውም ለእጅ ጥበብ ባለሙያዎቹ፣ ለግንባታ ባለሙያዎቹና ለግንበኞቹ ያስረክቡ፤ እነሱም ገንዘቡን ለቤቱ ጥገና የሚያስፈልጉትን ሳንቃዎችና ጥርብ ድንጋዮች ለመግዛት ይጠቀሙበታል።+  ነገር ግን ሰዎቹ እምነት የሚጣልባቸው ስለሆኑ ለተሰጣቸው ገንዘብ ስሌት እንዲያቀርቡ መጠየቅ አያስፈልግም።”+  በኋላም ሊቀ ካህናቱ ኬልቅያስ ጸሐፊውን ሳፋንን+ “የሕጉን መጽሐፍ+ በይሖዋ ቤት ውስጥ አገኘሁት” አለው። ኬልቅያስም መጽሐፉን ለሳፋን ሰጠው፤ እሱም ያነበው ጀመር።+  ከዚያም ጸሐፊው ሳፋን ወደ ንጉሡ ሄዶ “አገልጋዮችህ በቤቱ ውስጥ የተገኘውን ገንዘብ በሙሉ አውጥተው በይሖዋ ቤት የሚከናወነውን ሥራ እንዲቆጣጠሩ ለተሾሙት ሰዎች አስረክበዋል” አለው።+ 10  በተጨማሪም ጸሐፊው ሳፋን ንጉሡን “ካህኑ ኬልቅያስ የሰጠኝ አንድ መጽሐፍ+ አለ” አለው። ከዚያም ሳፋን መጽሐፉን በንጉሡ ፊት ማንበብ ጀመረ። 11  ንጉሡ የሕጉን መጽሐፍ ቃል ሲሰማ ልብሱን ቀደደ።+ 12  ከዚያም ንጉሡ ካህኑን ኬልቅያስን፣ የሳፋንን ልጅ አኪቃምን፣+ የሚካያህን ልጅ አክቦርን፣ ጸሐፊውን ሳፋንን እና የንጉሡን አገልጋይ አሳያህን እንዲህ ሲል አዘዛቸው፦ 13  “ሄዳችሁ በተገኘው በዚህ መጽሐፍ ላይ የሰፈረውን ቃል በተመለከተ እኔን፣ ሕዝቡንና መላውን ይሁዳ ወክላችሁ ይሖዋን ጠይቁ፤ ምክንያቱም አባቶቻችን በዚህ መጽሐፍ ላይ እኛን አስመልክቶ የሰፈረውን ቃል ስላልታዘዙ የይሖዋ ታላቅ ቁጣ በእኛ ላይ ነዷል።”+ 14  በመሆኑም ካህኑ ኬልቅያስ፣ አኪቃም፣ አክቦር፣ ሳፋንና አሳያህ ወደ ነቢዪቱ ሕልዳና+ ሄዱ። ሕልዳና የሃርሐስ ልጅ፣ የቲቅዋ ልጅ፣ የአልባሳት ጠባቂው የሻሉም ሚስት ስትሆን ኢየሩሳሌም ውስጥ በሁለተኛው ክፍል ትኖር ነበር፤ እነሱም በዚያ አነጋገሯት።+ 15  እሷም እንዲህ አለቻቸው፦ “የእስራኤል አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ወደ እኔ የላካችሁን ሰው እንዲህ በሉት፦ 16  “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘በዚህ ቦታና በነዋሪዎቹ ላይ መከራ አመጣለሁ፤ የይሁዳ ንጉሥ ባነበበው መጽሐፍ+ ላይ የሰፈረውን ቃል ሁሉ እፈጽማለሁ። 17  እኔን በመተው በእጆቻቸው ሥራ+ ሁሉ ያስቆጡኝ ዘንድ ለሌሎች አማልክት የሚጨስ መሥዋዕት ስለሚያቀርቡ+ ቁጣዬ በዚህ ቦታ ላይ ይነዳል፤ ደግሞም አይጠፋም።’”+ 18  ይሖዋን እንድትጠይቁ ለላካችሁ ለይሁዳ ንጉሥ ግን እንዲህ በሉት፦ “የእስራኤል አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘የሰማኸውን ቃል በተመለከተ፣ 19  ይህን ቦታም ሆነ ነዋሪዎቹን መቀጣጫ እንደማደርግና እንደምረግም የተናገርኩትን ነገር ስትሰማ ልብህ ስለተነካ፣* በይሖዋም ፊት ራስህን ስላዋረድክ+ እንዲሁም ልብስህን ስለቀደድክና+ በፊቴ ስላለቀስክ እኔም ሰምቼሃለሁ ይላል ይሖዋ። 20  ወደ አባቶችህ የምሰበስብህ* በዚህ የተነሳ ነው፤ አንተም በሰላም በመቃብርህ ታርፋለህ፤ በዚህ ቦታ ላይ የማመጣውን መከራ ሁሉ ዓይኖችህ አያዩም።’”’” ከዚያም ሰዎቹ መልሱን ለንጉሡ አመጡለት።

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ያሉትን ስንጥቆች።”
ቃል በቃል “ልብህ ስለለሰለሰ።”
ይህ ሞትን የሚያመለክት ቅኔያዊ አነጋገር ነው።