ሁለተኛ ዜና መዋዕል 14:1-15
14 በመጨረሻም አቢያህ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊት ከተማም+ ቀበሩት፤ በምትኩም ልጁ አሳ ነገሠ። በእሱም ዘመን ምድሪቱ ለአሥር ዓመት አረፈች።
2 አሳ በአምላኩ በይሖዋ ፊት መልካምና ትክክል የሆነውን ነገር አደረገ።
3 የባዕድ አማልክቱን መሠዊያዎችና+ ከፍ ያሉትን የማምለኪያ ቦታዎች አስወገደ፤ የማምለኪያ ዓምዶቹንም ሰባበረ፤+ እንዲሁም የማምለኪያ ግንዶቹን* ቆራረጠ።+
4 በተጨማሪም የይሁዳ ሰዎች የአባቶቻቸውን አምላክ ይሖዋን እንዲፈልጉ እንዲሁም ሕጉንና ትእዛዙን እንዲያከብሩ አዘዘ።
5 ከይሁዳም ከተሞች ሁሉ ከፍ ያሉትን የማምለኪያ ቦታዎችና የዕጣን ማጨሻዎቹን አስወገደ፤+ መንግሥቱም በእሱ አገዛዝ ሥር ሰላም አገኘ።
6 ምድሪቱ እረፍት አግኝታ ስለነበር በይሁዳ የተመሸጉ ከተሞችን ገነባ፤+ ይሖዋ እረፍት ሰጥቶት ስለነበር በእነዚያ ዓመታት በእሱ ላይ ጦርነት የከፈተ አልነበረም።+
7 የይሁዳንም ሰዎች እንዲህ አላቸው፦ “እነዚህን ከተሞች እንገንባ፤ በዙሪያቸውም ቅጥርና ማማዎች+ እንዲሁም በሮችና* መቀርቀሪያዎች እንሥራ። አምላካችንን ይሖዋን ስለፈለግነው ምድሪቱ አሁንም በእጃችን ናት። እኛ ፈልገነዋል፤ እሱም በዙሪያችን ካሉት ጠላቶቻችን ሁሉ እረፍት ሰጥቶናል።” በመሆኑም የግንባታ ሥራቸው ስኬታማ ሆነ።+
8 አሳ ትልቅ ጋሻና ጦር የታጠቁ 300,000 የይሁዳ ሰዎችን ያቀፈ ሠራዊት ነበረው። ከቢንያምም ነገድ ትንሽ ጋሻ* የሚያነግቡና ደጋን የሚይዙ* 280,000 ኃያላን ተዋጊዎች ነበሩ።+
9 ከጊዜ በኋላ ኢትዮጵያዊው ዛራ 1,000,000 ሰዎችንና 300 ሠረገሎችን ያቀፈ ሠራዊት አስከትሎ ዘመተባቸው።+ ማሬሻህ+ በደረሰ ጊዜ
10 አሳ ሊገጥመው ወጣ፤ በማሬሻህ በሚገኘው በጸፋታ ሸለቆም ለውጊያ ተሰለፉ።
11 በዚህ ጊዜ አሳ ወደ አምላኩ ወደ ይሖዋ እንዲህ ሲል ጮኸ፦+ “ይሖዋ ሆይ፣ የምትረዳው ሕዝብ ብዛት ያለውም ይሁን ደካማ ለአንተ የሚያመጣው ለውጥ የለም።+ ይሖዋ አምላካችን ሆይ፣ እርዳን፤ በአንተ ታምነናልና፤*+ በስምህ ይህን ታላቅ ሠራዊት ለመግጠም ወጥተናል።+ ይሖዋ ሆይ፣ አንተ አምላካችን ነህ። ሟች የሆነ ሰው በአንተ ላይ አይበርታ።”+
12 በመሆኑም ይሖዋ ኢትዮጵያውያንን በአሳና በይሁዳ ፊት ድል አደረጋቸው፤ ኢትዮጵያውያኑም ሸሹ።+
13 አሳና ከእሱ ጋር ያለው ሕዝብም እስከ ጌራራ+ ድረስ አሳደዷቸው፤ ኢትዮጵያውያኑም ፈጽመው እስኪጠፉ ድረስ ተመተው ወደቁ፤ በይሖዋና በሠራዊቱ ተደምስሰው ነበርና። በኋላም የይሁዳ ሰዎች እጅግ ብዙ ምርኮ ወሰዱ።
14 በተጨማሪም ይሖዋ በከተሞቹ ላይ ታላቅ ፍርሃት ለቆባቸው ስለነበር በጌራራ ዙሪያ ያሉትን ከተሞች ሁሉ መቱ፤ እነሱም በከተሞቹ ውስጥ ብዙ የሚበዘበዝ ነገር ስለነበር ከተሞቹን ሁሉ በዘበዙ።
15 በተጨማሪም የእረኞችን ድንኳኖች በመምታት እጅግ ብዙ በጎችንና ግመሎችን ማረኩ፤ ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።