ሁለተኛ ዜና መዋዕል 16:1-14

  • አሳ ከሶርያ ጋር ተዋዋለ (1-6)

  • ሃናኒ አሳን ገሠጸው (7-10)

  • አሳ ሞተ (11-14)

16  አሳ በነገሠ በ36ኛው ዓመት የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ+ በይሁዳ ላይ ዘመተ፤ እሱም ማንም ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ አሳ እንዳይገባና እንዳይወጣ*+ ለማድረግ ራማን+ መገንባት* ጀመረ።  በዚህ ጊዜ አሳ ከይሖዋ ቤትና ከንጉሡ ቤት* ግምጃ ቤቶች ብርና ወርቅ አውጥቶ+ በደማስቆ ወደሚገኘው የሶርያ ንጉሥ ወደ ቤንሃዳድ+ እንዲህ ሲል ላከ፦  “በእኔና በአንተ እንዲሁም በአባቴና በአባትህ መካከል ውል* አለ። እኔ ብርና ወርቅ ልኬልሃለሁ። ስለዚህ ና፣ የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ ከእኔ እንዲርቅ ከእሱ ጋር የገባኸውን ውል* አፍርስ።”  ቤንሃዳድ የንጉሥ አሳን ሐሳብ ተቀብሎ የጦር ሠራዊቱን አለቆች በእስራኤል ከተሞች ላይ አዘመተ፤ እነሱም ኢዮንን፣+ ዳንን፣+ አቤልማይምን እና በንፍታሌም+ ከተሞች ውስጥ ያሉትን የማከማቻ ስፍራዎች ሁሉ መቱ።  ባኦስም ይህን ሲሰማ ወዲያውኑ ራማን መገንባቱን* አቆመ፤ ሥራውንም አቋረጠ።  ከዚያም ንጉሡ አሳ የይሁዳን ሰዎች ሁሉ ይዞ ሄደ፤ እነሱም ባኦስ እየገነባባቸው የነበሩትን+ የራማን+ ድንጋዮችና ሳንቃዎች አጋዙ፤ እሱም በድንጋዮቹና በሳንቃዎቹ ጌባንና+ ምጽጳን+ ገነባ።*  በዚህ ጊዜ ባለ ራእዩ ሃናኒ+ ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ አሳ መጥቶ እንዲህ አለው፦ “በአምላክህ በይሖዋ ከመታመን* ይልቅ በሶርያ ንጉሥ ስለታመንክ* የሶርያ ንጉሥ ሠራዊት ከእጅህ አምልጧል።+  ኢትዮጵያውያንና ሊቢያውያን ብዙ ሠረገሎችና ፈረሰኞች ያሏቸው ታላቅ ሠራዊት አልነበሩም? ይሁንና በይሖዋ በመታመንህ በእጅህ አሳልፎ ሰጣቸው።+  አዎ፣ በሙሉ ልባቸው ወደ እሱ ላዘነበሉት ሰዎች*+ ብርታቱን ያሳይ ዘንድ* የይሖዋ ዓይኖች በምድር ሁሉ ላይ ይመላለሳሉ።+ በዚህ ረገድ የሞኝነት ድርጊት ፈጽመሃል፤ ከእንግዲህ ወዲያ ጦርነት አይለይህም።”+ 10  ሆኖም አሳ በባለ ራእዩ ተቆጣ፤ በዚህ ጉዳይ በጣም ስለተናደደበትም እስር ቤት* አስገባው። በዚያ ወቅት አሳ በሌሎች ሰዎችም ላይ በደል መፈጸም ጀመረ። 11  ከመጀመሪያ አንስቶ እስከ መጨረሻ ድረስ ያለው የአሳ ታሪክ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፏል።+ 12  አሳ በ39ኛው የግዛት ዘመኑ እግሩን ታመመ፤ ሕመሙም ጠናበት፤ ታሞ ሳለም እንኳ የባለ መድኃኒቶችን እንጂ የይሖዋን እርዳታ አልፈለገም። 13  በመጨረሻም አሳ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤+ በ41ኛው የግዛት ዘመኑም ሞተ። 14  እነሱም በዳዊት ከተማ+ ለራሱ ባስቆፈረው ታላቅ የመቃብር ቦታ ቀበሩት፤ የበለሳን ዘይት እንዲሁም ከተለያዩ ቅመሞች የተዘጋጀ ልዩ ቅባት በሞላበት ቃሬዛ ላይ አኖሩት።+ በተጨማሪም ለክብሩ ታላቅ እሳት አነደዱለት።*

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ማጠናከር፤ መልሶ መገንባት።”
ወይም “ከይሁዳ ንጉሥ ከአሳ ግዛት ማንም እንዳይወጣ ወይም ማንም ወደዚያ እንዳይገባ።”
ወይም “ቤተ መንግሥት።”
ወይም “ቃል ኪዳን።”
ወይም “ቃል ኪዳን።”
ወይም “ማጠናከሩን፤ መልሶ መገንባቱን።”
ወይም “አጠናከረ፤ መልሶ ገነባ።”
ቃል በቃል “ከመደገፍ።”
ቃል በቃል “ስለተደገፍክ።”
ወይም “ያዘነበሉትን ሰዎች ይረዳ ዘንድ።”
ወይም “ሙሉ በሙሉ ለእሱ ላደሩ ሰዎች።”
ቃል በቃል “የእግር ግንድ ቤት ውስጥ።”
ያነደዱት የአሳን አስከሬን ሳይሆን የተለያዩ ቅመማ ቅመሞችን እንደሆነ ግልጽ ነው።