ሁለተኛ ዜና መዋዕል 19:1-11

  • ኢዩ ኢዮሳፍጥን ገሠጸው (1-3)

  • ኢዮሳፍጥ ያካሄደው ተሃድሶ (4-11)

19  ከዚያም የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሳፍጥ በኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ቤቱ* በደህና ተመለሰ።+  ባለ ራእዩ የሃናኒ+ ልጅ ኢዩ+ ከንጉሥ ኢዮሳፍጥ ጋር ለመገናኘት ሄደ፤ እንዲህም አለው፦ “ለክፉ ሰው እርዳታ መስጠት ይገባሃል?+ ይሖዋን የሚጠሉትንስ መውደድ ይገባሃል?+ በዚህ ምክንያት ይሖዋ በአንተ ላይ ተቆጥቷል።  ይሁንና የማምለኪያ ግንዶቹን* ከምድሪቱ ስላስወገድክና እውነተኛውን አምላክ ለመፈለግ ልብህን ስላዘጋጀህ*+ መልካም ነገር ተገኝቶብሃል።”+  ኢዮሳፍጥ በኢየሩሳሌም መኖሩን ቀጠለ፤ ወደ አባቶቻቸው አምላክ ወደ ይሖዋ ይመልሳቸውም ዘንድ ከቤርሳቤህ አንስቶ እስከ ተራራማው የኤፍሬም ምድር+ ድረስ ወዳለው ሕዝብ ዳግመኛ ወጣ።+  በተጨማሪም በመላ ምድሪቱ ይኸውም በተመሸጉት የይሁዳ ከተሞች ሁሉ ላይ፣ በእያንዳንዱ ከተማ ፈራጆችን መደበ።+  ፈራጆቹንም እንዲህ አላቸው፦ “የምትፈርዱት ለሰው ሳይሆን ለይሖዋ ስለሆነ የምታደርጉትን ነገር በጥንቃቄ አከናውኑ፤ እሱም በምትፈርዱበት ጊዜ ከእናንተ ጋር ነው።+  አሁንም ይሖዋን መፍራት በእናንተ ላይ ይሁን።+ በአምላካችን በይሖዋ ዘንድ ፍትሕ ማዛባት፣+ አድልዎ+ ወይም ጉቦ መቀበል+ ስለሌለ የምታደርጉትን ነገር በጥንቃቄ አከናውኑ።”  ኢዮሳፍጥ በኢየሩሳሌምም የተወሰኑ ሌዋውያንንና ካህናትን እንዲሁም ከእስራኤል የአባቶች ቤት መሪዎች መካከል አንዳንዶቹን ፈራጆች ሆነው ይሖዋን እንዲያገለግሉና የኢየሩሳሌምን ነዋሪዎች ሙግት እንዲቋጩ መደበ።+  እንዲህም ሲል አዘዛቸው፦ “ይሖዋን በመፍራት በታማኝነትና በሙሉ ልብ* ይህን ልታደርጉ ይገባል፦ 10  በየከተሞቻቸው የሚኖሩት ወንድሞቻችሁ ከደም መፋሰስ ጋር የተያያዘ ክስ+ አሊያም ከሕግ፣ ከትእዛዝ፣ ከሥርዓት ወይም ከድንጋጌዎች ጋር የተያያዘ ጥያቄ ይዘው በሚመጡበት ጊዜ ሁሉ በይሖዋ ፊት በደለኛ እንዳይሆኑ ልታስጠነቅቋቸው ይገባል፤ ይህ ካልሆነ ግን በእናንተም ሆነ በወንድሞቻችሁ ላይ ቁጣው ይመጣል። በደለኛ እንዳትሆኑ ይህን ልታደርጉ ይገባል። 11  እነሆ፣ የይሖዋ በሆነው ነገር ሁሉ ላይ በእናንተ ላይ የተሾመው የካህናቱ አለቃ አማርያህ አለ።+ የእስማኤል ልጅ ዘባድያህ ከንጉሡ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ሁሉ የይሁዳ ቤት መሪ ነው። ሌዋውያኑ ደግሞ አለቆች ሆነው ያገለግሏችኋል። በርቱ፤ ሥራችሁንም በትጋት አከናውኑ፤ ይሖዋም መልካም የሆነውን ነገር ከሚያደርጉት* ጋር ይሁን።”+

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ቤተ መንግሥቱ።”
ወይም “ልብህ ስለቆረጠ።”
ወይም “ሙሉ በሙሉ ለአምላክ ባደረ ልብ።”
ወይም “መልካም ከሆነው ነገር።”