ሁለተኛ ዜና መዋዕል 20:1-37

  • አጎራባች ብሔራት ይሁዳን ስጋት ላይ ጣሏት (1-4)

  • ኢዮሳፍጥ ይሖዋ እንዲረዳው ጸለየ (5-13)

  • ይሖዋ ጸሎቱን መለሰለት (14-19)

  • አምላክ ይሁዳን በተአምር አዳናት (20-30)

  • የኢዮሳፍጥ አገዛዝ አበቃ (31-37)

20  ከጊዜ በኋላ ሞዓባውያንና+ አሞናውያን+ ከተወሰኑ የአሞኒም ሰዎች* ጋር ሆነው ከኢዮሳፍጥ ጋር ለመዋጋት መጡ።  በመሆኑም ኢዮሳፍጥ እንዲህ የሚል ወሬ ሰማ፦ “በባሕሩ* አካባቢ ካለው ክልል፣ ከኤዶም+ ታላቅ ሠራዊት አንተን ሊወጋ መጥቷል፤ ሠራዊቱም በሃጻጾንታማር ማለትም በኤንገዲ+ ይገኛል።”  ኢዮሳፍጥ ይህን ሲሰማ ፈራ፤ ይሖዋንም ለመፈለግ ቆርጦ ተነሳ።*+ በመሆኑም በመላው ይሁዳ ጾም አወጀ።  ከዚያም የይሁዳ ሰዎች ይሖዋን ለመጠየቅ ተሰበሰቡ፤+ የይሖዋን መመሪያ ለማግኘት ከይሁዳ ከተሞች ሁሉ መጡ።  ከዚያም ኢዮሳፍጥ በይሖዋ ቤት ከአዲሱ ግቢ ፊት ለፊት በይሁዳና በኢየሩሳሌም ጉባኤ መካከል ቆመ፤  እንዲህም አለ፦ “የአባቶቻችን አምላክ ይሖዋ ሆይ፣ አንተ በሰማያት ያለህ አምላክ አይደለህም?+ የብሔራትን መንግሥታት ሁሉ የምትገዛ አንተ አይደለህም?+ ኃይልና ብርታት በእጅህ ነው፤ አንተን ሊቋቋም የሚችል ማንም የለም።+  አምላካችን ሆይ፣ የዚህችን ምድር ነዋሪዎች ከሕዝብህ ከእስራኤል ፊት አሳደህ ምድሪቱን ለወዳጅህ ለአብርሃም ዘሮች ለዘለቄታው ርስት አድርገህ የሰጠኸው አንተ አይደለህም?+  እነሱም በምድሪቱ መኖር ጀመሩ፤ በዚያም ለስምህ መቅደስ ሠሩ፤+ እንዲህም አሉ፦  ‘ሰይፍ፣ የቅጣት ፍርድ፣ ቸነፈር ወይም ረሃብ በእኛ ላይ ጥፋት ቢያደርስብን በዚህ ቤትና በአንተ ፊት እንቆማለን (ይህን ቤት ለስምህ መርጠኸዋልና)፤+ ከጭንቀታችንም እንድትገላግለን ወደ አንተ እንጮኻለን፤ አንተም ሰምተህ አድነን።’+ 10  አሁንም የአሞንና የሞዓብ ሰዎች እንዲሁም በሴይር ተራራማ ክልል+ የሚኖሩ ሰዎች የሚያደርጉትን ተመልከት። እስራኤላውያን ከግብፅ ምድር በወጡበት ጊዜ እነሱን እንዲወሩ አልፈቀድክም ነበር። እነሱም አልነኳቸውም፤ ደግሞም አላጠፏቸውም።+ 11  እነሱ ግን ርስት አድርገህ ካወረስከን ምድር እኛን በማባረር ብድራት ሊመልሱልን መጥተዋል።+ 12  አምላካችን ሆይ፣ በእነሱ ላይ አትፈርድባቸውም?+ እኛ የመጣብንን ይህን ታላቅ ሠራዊት ለመቋቋም የሚያስችል ኃይል የለንም፤ ምን ማድረግ እንዳለብንም አናውቅም፤+ ነገር ግን ዓይኖቻችን ወደ አንተ ይመለከታሉ።”+ 13  በዚህ ጊዜ የይሁዳ ሰዎች በሙሉ ከሕፃኖቻቸው፣ ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው* ጋር በይሖዋ ፊት ቆመው ነበር። 14  ከዚያም በጉባኤው መካከል የይሖዋ መንፈስ ከአሳፍ ልጆች ወገን በሆነው በሌዋዊው በማታንያህ ልጅ፣ በየኢዔል ልጅ፣ በበናያህ ልጅ፣ በዘካርያስ ልጅ በያሃዚኤል ላይ መጣ። 15  እሱም እንዲህ አለ፦ “የይሁዳ ሰዎች ሁሉ፣ እናንተም የኢየሩሳሌም ነዋሪዎችና ንጉሥ ኢዮሳፍጥ፣ አዳምጡ! ይሖዋ እንዲህ ይላችኋል፦ ‘ከዚህ ታላቅ ሠራዊት የተነሳ አትፍሩ፤ አትሸበሩ፤ ውጊያው የአምላክ እንጂ የእናንተ አይደለምና።+ 16  ነገ በእነሱ ላይ ውረዱ። እነሱ በጺጽ መተላለፊያ ሽቅብ ይወጣሉ፤ እናንተም የሩኤል ምድረ በዳ ከመድረሳችሁ በፊት በሸለቆው መጨረሻ* ላይ ታገኟቸዋላችሁ። 17  እናንተ ይህን ጦርነት መዋጋት አያስፈልጋችሁም። ቦታ ቦታችሁን ይዛችሁ ዝም ብላችሁ ቁሙ፤+ ይሖዋ ለእናንተ ሲል የሚወስደውን የማዳን እርምጃ ተመልከቱ።*+ ይሁዳና ኢየሩሳሌም ሆይ፣ አትፍሩ ወይም አትሸበሩ።+ ነገ በእነሱ ላይ ውጡ፤ ይሖዋም ከእናንተ ጋር ይሆናል።’”+ 18  ኢዮሳፍጥ ወዲያውኑ በግንባሩ ወደ መሬት ተደፋ፤ የይሁዳ ሰዎች ሁሉና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎችም በይሖዋ ፊት ተደፍተው ይሖዋን አመለኩ። 19  ከዚያም የቀአታውያንና+ የቆሬያውያን ዘሮች የሆኑት ሌዋውያን የእስራኤልን አምላክ ይሖዋን እጅግ ከፍ ባለ ድምፅ ለማወደስ ተነሱ።+ 20  በማግስቱም በማለዳ ተነስተው በተቆአ+ ወደሚገኘው ምድረ በዳ ሄዱ። እየሄዱ ሳሉ ኢዮሳፍጥ ቆሞ እንዲህ አለ፦ “ይሁዳና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ሆይ፣ ስሙኝ! ጸንታችሁ መቆም እንድትችሉ በአምላካችሁ በይሖዋ እመኑ። በነቢያቱም እመኑ፤+ እንዲህ ካደረጋችሁ ይሳካላችኋል።” 21  ከሕዝቡ ጋር ከተማከረ በኋላም ከታጠቁት ሰዎች ፊት ፊት እየሄዱ “ለይሖዋ ምስጋና አቅርቡ፤ ታማኝ ፍቅሩ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራልና”+ እያሉ ለይሖዋ የሚዘምሩ እንዲሁም ያጌጠ የቅድስና ልብስ ለብሰው ውዳሴ የሚያቀርቡ ሰዎችን መደበ።+ 22  በደስታ የውዳሴ መዝሙር መዘመር በጀመሩ ጊዜ ይሖዋ ይሁዳን በወረሩት በአሞን፣ በሞዓብና በሴይር ተራራማ ክልል በሚኖሩት ሰዎች ላይ ድንገተኛ ጥቃት ሰነዘረባቸው፤ እነሱም እርስ በርስ ተፋጁ።+ 23  አሞናውያኑና ሞዓባውያኑ በሴይር ተራራማ ክልል+ በሚኖሩት ሰዎች ላይ ተነስተው አጠፏቸው፤ ደመሰሷቸውም፤ የሴይርን ነዋሪዎች ካጠፉም በኋላ እርስ በርስ ተላለቁ።+ 24  የይሁዳ ሰዎች በምድረ በዳ+ ወዳለው መጠበቂያ ግንብ መጥተው ሠራዊቱን ሲመለከቱ መሬቱ ሬሳ በሬሳ ሆኖ አዩ፤+ በሕይወት የተረፈ አንድም ሰው አልነበረም። 25  በመሆኑም ኢዮሳፍጥና ሕዝቡ ከእነሱ ላይ ምርኮ ለመውሰድ መጡ፤ በእነሱም መካከል እጅግ ብዙ ዕቃ፣ ልብስና ውድ ነገሮች አገኙ፤ መሸከም እስኪያቅታቸው ድረስ ብዙ ነገር ገፈፏቸው።+ ከብዛቱ የተነሳ ለሦስት ቀን ያህል ምርኮ ሲሰበስቡ ቆዩ። 26  በአራተኛውም ቀን በቤራካ ሸለቆ* ተሰበሰቡ፤ በዚያም ይሖዋን አወደሱ።* ይህን ስፍራ እስከ ዛሬ ድረስ የቤራካ* ሸለቆ ብለው የሚጠሩት ከዚህ የተነሳ ነው።+ 27  ከዚያም የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሰዎች ሁሉ ይሖዋ በጠላቶቻቸው ላይ ድል ስላቀዳጃቸው በኢዮሳፍጥ እየተመሩ በታላቅ ደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።+ 28  በባለ አውታር መሣሪያዎች፣ በበገናና+ በመለከት+ ድምፅ ታጅበው ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፤ ከዚያም ወደ ይሖዋ ቤት ሄዱ።+ 29  ይሖዋ የእስራኤልን ጠላቶች እንደተዋጋ በሰሙ ጊዜ በምድሪቱ ያሉ መንግሥታት ሁሉ አምላክን ፈሩ።+ 30  በመሆኑም የኢዮሳፍጥ መንግሥት ከሁከት ነፃ ሆነ፤ አምላኩም በዙሪያው ካሉት ጠላቶቹ ሁሉ እረፍት ሰጠው።+ 31  ኢዮሳፍጥም በይሁዳ መግዛቱን ቀጠለ። በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 35 ዓመት የነበረ ሲሆን በኢየሩሳሌም 25 ዓመት ገዛ። እናቱ የሺልሂ ልጅ አዙባ ነበረች።+ 32  እሱም በአባቱ በአሳ መንገድ ሄደ።+ ከዚያ ፈቀቅ አላለም፤ በይሖዋም ፊት ትክክል የሆነውን ነገር አደረገ።+ 33  ይሁን እንጂ ከፍ ያሉት የማምለኪያ ቦታዎች አልተወገዱም ነበር፤+ ሕዝቡም ልቡን ለአባቶቹ አምላክ ገና አላዘጋጀም ነበር።+ 34  ከመጀመሪያ አንስቶ እስከ መጨረሻ ድረስ ያለው የቀረው የኢዮሳፍጥ ታሪክ የሃናኒ+ ልጅ ኢዩ+ በጻፈው ዘገባ ላይ ሰፍሯል፤ ይህም በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ውስጥ ተካቷል። 35  ከዚህ በኋላ የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሳፍጥ፣ ክፉ ድርጊት ከፈጸመው ከእስራኤል ንጉሥ ከአካዝያስ ጋር ግንባር ፈጠረ።+ 36  ወደ ተርሴስ+ የሚሄዱ መርከቦችን ለመሥራትም ተሻረኩ፤ መርከቦቹንም በዔጽዮንጋብር+ ሠሩ። 37  ይሁን እንጂ የማሬሻ ሰው የሆነው የዶዳዋ ልጅ ኤሊዔዘር “ከአካዝያስ ጋር ግንባር በመፍጠርህ ይሖዋ ሥራህን ያፈርሰዋል” ሲል በኢዮሳፍጥ ላይ ትንቢት ተናገረ።+ በመሆኑም መርከቦቹ ተሰባበሩ፤+ ወደ ተርሴስም መሄድ ሳይችሉ ቀሩ።

የግርጌ ማስታወሻ

“መኡኒማውያን” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ሙት ባሕርን ሊያመለክት ይችላል።
ቃል በቃል “ፊቱን አቀና።”
ቃል በቃል “ከወንዶች ልጆቻቸው።”
ወይም “በደረቁ ወንዝ መጨረሻ።”
ወይም “ይሖዋ እንዴት እንደሚታደጋችሁ ተመልከቱ።”
ወይም “ረባዳማ ሜዳ።”
ቃል በቃል “ባረኩ።”
“በረከት” የሚል ትርጉም አለው።