ሁለተኛ ዜና መዋዕል 21:1-20

  • ኢዮራም በይሁዳ ላይ ነገሠ (1-11)

  • ኤልያስ የላከው የጽሑፍ መልእክት (12-15)

  • የኢዮራም መጥፎ አወዳደቅ (16-20)

21  በመጨረሻም ኢዮሳፍጥ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊት ከተማም ከአባቶቹ ጋር ተቀበረ፤ በእሱም ምትክ ልጁ ኢዮራም ነገሠ።+  የኢዮሳፍጥ ልጆች የሆኑት ወንድሞቹ አዛርያስ፣ የሂኤል፣ ዘካርያስ፣ አዛርያስ፣ ሚካኤል እና ሰፋጥያህ ነበሩ፤ እነዚህ ሁሉ የእስራኤል ንጉሥ የኢዮሳፍጥ ወንዶች ልጆች ናቸው።  አባታቸውም ብዙ ብር፣ ወርቅና ውድ የሆኑ ነገሮች ስጦታ አድርጎ የሰጣቸው ከመሆኑም በላይ በይሁዳ የተመሸጉ ከተሞችን ሰጣቸው፤+ መንግሥቱን ግን የበኩር ልጁ ለነበረው ለኢዮራም+ ሰጠው።  ኢዮራም በአባቱ መንግሥት ላይ ተደላድሎ በተቀመጠ ጊዜ ወንድሞቹን በሙሉ እንዲሁም ከእስራኤል መኳንንት መካከል የተወሰኑትን በሰይፍ በመግደል ሥልጣኑን አጠናከረ።+  ኢዮራም በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 32 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ስምንት ዓመት ገዛ።+  የአክዓብን ልጅ አግብቶ+ ስለነበር ከአክዓብ ቤት የሆኑት እንዳደረጉት ሁሉ እሱም በእስራኤል ነገሥታት መንገድ ሄደ፤+ በይሖዋም ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ።  ሆኖም ይሖዋ ከዳዊት ጋር ለገባው ቃል ኪዳን ሲል የዳዊትን ቤት ማጥፋት አልፈለገም፤+ ምክንያቱም ለእሱና ለልጆቹ ለሁልጊዜ የሚኖር መብራት* እንደሚሰጥ ቃል ገብቶ ነበር።+  በእሱ ዘመን ኤዶም በይሁዳ ላይ ዓምፆ+ የራሱን ንጉሥ አነገሠ።+  በመሆኑም ኢዮራም ከአዛዦቹ ጋር ሠረገሎቹን ሁሉ ይዞ ተሻገረ፤ በሌሊትም ተነስቶ እሱንና የሠረገሎቹን አዛዦች ከበው የነበሩትን ኤዶማውያን ድል አደረገ። 10  ሆኖም ኤዶም እስከ ዛሬ ድረስ በይሁዳ ላይ እንዳመፀ ነው። ሊብናም+ በዚሁ ጊዜ በእሱ ላይ ዓመፀ፤ ምክንያቱም ኢዮራም የአባቶቹን አምላክ ይሖዋን ትቶ ነበር።+ 11  ደግሞም በይሁዳ ተራሮች ላይ ከፍ ያሉ የማምለኪያ ቦታዎችን ሠርቶ+ የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች መንፈሳዊ ምንዝር እንዲፈጽሙ አደረገ፤ ይሁዳንም አሳተ። 12  በመጨረሻም ነቢዩ ኤልያስ እንዲህ የሚል መልእክት በጽሑፍ ላከለት፦+ “የአባትህ የዳዊት አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘በአባትህ በኢዮሳፍጥ+ ወይም በይሁዳ ንጉሥ በአሳ+ መንገድ አልሄድክም። 13  ይልቁንም በእስራኤል ነገሥታት መንገድ በመሄድ፣+ ይሁዳና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች የአክዓብ ቤት የፈጸመውን ምንዝር+ የሚመስል መንፈሳዊ ምንዝር እንዲፈጽሙ አድርገሃል፤+ ከዚህም በላይ ከአንተ ይሻሉ የነበሩትን የአባትህ ቤት ልጆች የሆኑትን የገዛ ወንድሞችህን ገድለሃል።+ 14  ስለዚህ ይሖዋ ሕዝብህን፣ ልጆችህን፣ ሚስቶችህንና ንብረትህን ሁሉ በታላቅ መቅሰፍት ይመታል። 15  አንተም የአንጀት በሽታን ጨምሮ በብዙ ሕመም ትሠቃያለህ፤ ከበሽታው የተነሳ አንጀትህ እስኪወጣ ድረስ ሕመሙ ዕለት ተዕለት እየጠናብህ ይሄዳል።’” 16  ከዚያም ይሖዋ ፍልስጤማውያንና+ በኢትዮጵያውያን አቅራቢያ የሚኖሩት ዓረቦች+ በኢዮራም ላይ እንዲነሱ አደረገ።*+ 17  እነሱም ይሁዳን ወረሩ፤ በኃይል ጥሰው በመግባትም በንጉሡ ቤት* ያገኙትን ንብረት ሁሉ+ እንዲሁም ልጆቹንና ሚስቶቹን ማርከው ወሰዱ፤ ከመጨረሻው ልጁ ከኢዮዓካዝ*+ በቀር አንድም ልጅ አልቀረለትም። 18  ከዚህ ሁሉ በኋላ ይሖዋ በማይድን የአንጀት በሽታ ቀሰፈው።+ 19  ድፍን ሁለት ዓመት ከታመመ በኋላም ሕመሙ ጠንቶበት አንጀቱ ወጣ፤ በበሽታውም እጅግ ሲሠቃይ ቆይቶ በመጨረሻ ሞተ፤ ሕዝቡም ለአባቶቹ ያደርጉት እንደነበረው ለእሱ ክብር እሳት አላነደዱም።+ 20  በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 32 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ለስምንት ዓመት ገዛ። ሲሞት ማንም አላዘነለትም። በመሆኑም በነገሥታቱ የመቃብር ስፍራ ሳይሆን+ በዳዊት ከተማ+ ቀበሩት።

የግርጌ ማስታወሻ

“መብራት” የሚለው ቃል ከዳዊት ቤት የሆነን ንጉሥ ወይም የእሱን ሥርወ መንግሥት ያመለክታል።
ቃል በቃል “የፍልስጤማውያንንና በኢትዮጵያውያን አቅራቢያ የሚኖሩትን ዓረቦች መንፈስ በኢዮራም ላይ አነሳሳ።”
ወይም “ቤተ መንግሥት።”
አካዝያስ ተብሎም ይጠራል።