ሁለተኛ ዜና መዋዕል 23:1-21

  • ካህኑ ዮዳሄ ድፍረት የተሞላበት እርምጃ ወሰደ፤ ኢዮዓስ ነገሠ (1-11)

  • ጎቶልያ ተገደለች (12-15)

  • ዮዳሄ ያካሄደው ተሃድሶ (16-21)

23  በሰባተኛው ዓመት ካህኑ ዮዳሄ ድፍረት የተሞላበት እርምጃ በመውሰድ ከመቶ አለቆቹ+ ይኸውም ከየሮሃም ልጅ ከአዛርያስ፣ ከየሆሃናን ልጅ ከእስማኤል፣ ከኢዮቤድ ልጅ ከአዛርያስ፣ ከአዳያህ ልጅ ከማአሴያህ እና ከዚክሪ ልጅ ከኤሊሻፋጥ ጋር ስምምነት* አደረገ።  ከዚያም በይሁዳ ሁሉ በመዘዋወር ከመላው የይሁዳ ከተሞች ሌዋውያንንና+ የእስራኤልን የአባቶች ቤት መሪዎች ሰበሰቡ። ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጡ  መላው ጉባኤ በእውነተኛው አምላክ ቤት ከንጉሡ ጋር ቃል ኪዳን ገባ፤+ ከዚያም ዮዳሄ እንዲህ አላቸው፦ “እነሆ፣ ይሖዋ የዳዊትን ወንዶች ልጆች አስመልክቶ ቃል በገባው መሠረት የንጉሡ ልጅ ይገዛል።+  እናንተም እንዲህ ታደርጋላችሁ፦ በሰንበት ቀን ተረኛ ከሚሆኑት ካህናትና ሌዋውያን+ መካከል አንድ ሦስተኛዎቹ በር ጠባቂዎች ይሆናሉ፤+  አንድ ሦስተኛዎቹ ደግሞ በንጉሡ ቤት*+ ይሆናሉ፤ ሌላው አንድ ሦስተኛ በመሠረት በር ላይ ይሆናል፤ ሕዝቡ ሁሉ ደግሞ በይሖዋ ቤት ግቢዎች+ ውስጥ ይሆናል።  ከሚያገለግሉት ካህናትና ሌዋውያን በስተቀር ማንንም ወደ ይሖዋ ቤት እንዳታስገቡ።+ እነሱ የተቀደሱ ስለሆኑ ይግቡ፤ የቀረውም ሕዝብ ሁሉ ለይሖዋ ያለበትን ግዴታ ይፈጽማል።  ሌዋውያኑም እያንዳንዳቸው የጦር መሣሪያቸውን በእጃቸው ይዘው ንጉሡን ዙሪያውን ይክበቡት። ወደ ቤቱም ውስጥ የሚገባ ማንኛውም ሰው ይገደላል። ንጉሡ በሚሄድበት ሁሉ* አብራችሁት ሁኑ።”  ሌዋውያኑና የይሁዳ ሰዎች በሙሉ ልክ ካህኑ ዮዳሄ እንዳዘዛቸው አደረጉ። እያንዳንዳቸውም በሰንበት ቀን ተረኛ የሚሆኑትንና በሰንበት ቀን ከሥራ ነፃ የሚሆኑትን የራሳቸውን ሰዎች ወሰዱ፤+ ካህኑ ዮዳሄ ተራቸው ባይሆንም እንኳ በየምድቡ+ ያሉትን ከሥራ አላሰናበተም ነበርና።  ካህኑ ዮዳሄም በእውነተኛው አምላክ ቤት+ የነበሩትን የንጉሥ ዳዊት ጦሮች፣ ትናንሽ ጋሻዎችና* ክብ ጋሻዎች+ ለመቶ አለቆቹ+ ሰጣቸው። 10  ከዚያም ሕዝቡ ሁሉ እያንዳንዳቸው የጦር መሣሪያቸውን* ይዘው በስተ ቀኝ በኩል ካለው የቤቱ ጎን አንስቶ በስተ ግራ በኩል እስካለው የቤቱ ጎን ድረስ በመሠዊያውና በቤቱ አጠገብ በንጉሡ ዙሪያ እንዲቆሙ አደረገ። 11  የንጉሡንም ልጅ+ አውጥተው አክሊሉን* ጫኑበት፤ ምሥክሩንም*+ ሰጡት፤ በዚህም መንገድ አነገሡት፤ ዮዳሄና ወንዶች ልጆቹም ቀቡት። ከዚያም “ንጉሡ ለዘላለም ይኑር!” አሉ።+ 12  ጎቶልያ ሕዝቡ ሲሯሯጥና ንጉሡን ሲያወድስ ስትሰማ ወዲያውኑ በይሖዋ ቤት ወዳለው ሕዝብ መጣች።+ 13  ከዚያም ንጉሡ በመግቢያው ላይ ባለው በዓምዱ አጠገብ ቆሞ አየች። መኳንንቱና+ መለከት ነፊዎቹ ከንጉሡ ጋር ነበሩ፤ የምድሪቱም ሕዝብ ሁሉ እጅግ እየተደሰተና+ መለከት እየነፋ ነበር፤ የሙዚቃ መሣሪያ የያዙት ዘማሪዎችም ውዳሴውን ይመሩ* ነበር። በዚህ ጊዜ ጎቶልያ ልብሷን ቀዳ “ይህ ሴራ ነው! ሴራ ነው!” በማለት ጮኸች። 14  ካህኑ ዮዳሄ ግን በሠራዊቱ ላይ የተሾሙትን መቶ አለቆች ይዟቸው በመውጣት “ከረድፉ መካከል አውጧት፤ እሷን ተከትሎ የሚመጣ ሰው ካለ በሰይፍ ግደሉት!” አላቸው። ካህኑ “በይሖዋ ቤት ውስጥ እንዳትገድሏት” ብሎ ነበር። 15  በመሆኑም ያዟት፤ በንጉሡም ቤት* ወዳለው የፈረስ በር መግቢያ እንደደረሰች ገደሏት። 16  ከዚያም ዮዳሄ የይሖዋ ሕዝብ ሆነው እንዲቀጥሉ እሱ፣ ሕዝቡ ሁሉና ንጉሡ ቃል ኪዳን እንዲጋቡ አደረገ።+ 17  የምድሪቱም ሕዝብ ሁሉ ወደ ባአል ቤት* መጥቶ አፈራረሰው፤+ መሠዊያዎቹንና ምስሎቹንም ሰባበረ፤+ የባአል ካህን የነበረውን ማታንንም በመሠዊያዎቹ ፊት ገደሉት።+ 18  ከዚያም ዮዳሄ በይሖዋ ቤት የሚከናወኑትን ሥራዎች እንዲቆጣጠሩ ካህናቱንና ሌዋውያኑን ሾመ፤ እነሱም በሙሴ ሕግ ላይ በተጻፈው+ እንዲሁም ዳዊት ባዘዘው መሠረት* በደስታና በመዝሙር ለይሖዋ የሚቃጠል መሥዋዕት እንዲያቀርቡ ዳዊት በይሖዋ ቤት በየምድቡ የመደባቸው ናቸው።+ 19  በተጨማሪም በማንኛውም ነገር የረከሰ ሰው እንዳይገባ በር ጠባቂዎቹን+ በይሖዋ ቤት በሮች ላይ አቆመ። 20  ከዚያም መቶ አለቆቹን፣+ መኳንንቱን፣ የሕዝቡን ገዢዎችና የምድሪቱን ሕዝብ ሁሉ ሰበሰበ፤ ንጉሡንም አጅበው ከይሖዋ ቤት ወደ ታች አመጡት። በላይኛውም በር በኩል ወደ ንጉሡ ቤት* ገቡ፤ ንጉሡንም በመንግሥቱ+ ዙፋን+ ላይ አስቀመጡት። 21  በመሆኑም የምድሪቱ ሕዝብ ሁሉ እጅግ ተደሰተ፤ ጎቶልያንም በሰይፍ ስለገደሏት ከተማዋ ጸጥታ ሰፈነባት።

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ቃል ኪዳን።”
ወይም “ቤተ መንግሥት።”
ቃል በቃል “በሚወጣበትም ሆነ በሚገባበት ጊዜ።”
አብዛኛውን ጊዜ ቀስተኞች የሚይዙት ትንሽ ጋሻ።
ወይም “ተወንጫፊ መሣሪያቸውን።”
የአምላክ ሕግ የሰፈረበት ጥቅልል ሊሆን ይችላል።
ወይም “ዘውዱን።”
ወይም “ውዳሴ እንዲቀርብ ምልክት ይሰጡ።”
ወይም “ቤተ መንግሥት።”
ወይም “ቤተ መቅደስ።”
ቃል በቃል “በዳዊት እጅ።”
ወይም “ቤተ መንግሥት።”