ሁለተኛ ዜና መዋዕል 25:1-28

  • አሜስያስ በይሁዳ ላይ ነገሠ (1-4)

  • ከኤዶማውያን ጋር የተደረገ ጦርነት (5-13)

  • አሜስያስ ጣዖት አመለከ (14-16)

  • አሜስያስ ከእስራኤል ንጉሥ ከኢዮዓስ ጋር ተዋጋ (17-24)

  • አሜስያስ ሞተ (25-28)

25  አሜስያስ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 25 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለ29 ዓመት ገዛ። እናቱ ዮዓዳን የተባለች የኢየሩሳሌም ተወላጅ ነበረች።+  እሱም በይሖዋ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር አደረገ፤ ሆኖም በሙሉ ልቡ አልነበረም።  መንግሥቱ በእጁ እንደጸናለትም ንጉሥ የነበረውን አባቱን የገደሉትን አገልጋዮቹን ገደላቸው።+  ይሁንና “አባቶች በልጆቻቸው ኃጢአት መገደል የለባቸውም፤ ልጆችም በአባቶቻቸው ኃጢአት መገደል የለባቸውም፤ ይልቁንም እያንዳንዱ ሰው በገዛ ኃጢአቱ ይገደል” በሚለው በሙሴ የሕግ መጽሐፍ ላይ በተጻፈው የይሖዋ ትእዛዝ መሠረት የገዳዮቹን ልጆች አልገደላቸውም።+  አሜስያስም የይሁዳን ሰዎች ሰብስቦ በየአባቶቻቸው ቤት፣ በሺህ አለቆችና በመቶ አለቆች በመደልደል መላውን ይሁዳና ቢንያም ወክለው እንዲቆሙ አደረገ።+ ዕድሜያቸው 20 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆናቸውን መዘገበ፤+ በጦርና በትልቅ ጋሻ መጠቀምና በሠራዊቱ ውስጥ ማገልገል የሚችሉ 300,000 የሠለጠኑ* ተዋጊዎችን አገኘ።  በተጨማሪም በ100 የብር ታላንት፣* 100,000 ኃያላን ተዋጊዎችን ከእስራኤል ቀጠረ።  ይሁንና አንድ የእውነተኛው አምላክ ሰው ወደ እሱ መጥቶ እንዲህ አለው፦ “ንጉሥ ሆይ፣ ይሖዋ ከእስራኤል፣ ከኤፍሬማውያን ሁሉ ጋር ስላልሆነ+ የእስራኤል ሠራዊት ከአንተ ጋር እንዲዘምት አታድርግ።  ይልቁንም ብቻህን ዝመት፤ ወደኋላ አትበል፤ በቆራጥነትም ተዋጋ። እንዲህ ባታደርግ ግን እውነተኛው አምላክ በጠላቶችህ ፊት ሊጥልህ ይችላል፤ አምላክ ለመርዳትም ሆነ ለመጣል ኃይል አለውና።”+  በዚህ ጊዜ አሜስያስ የእውነተኛውን አምላክ ሰው “ታዲያ ለእስራኤል ወታደሮች የሰጠሁት 100 ታላንት ምን ይሁን?” አለው። የእውነተኛውም አምላክ ሰው “ይሖዋ ከዚህ እጅግ የሚበልጥ ሊሰጥህ ይችላል” ሲል መለሰለት።+ 10  በመሆኑም አሜስያስ ከኤፍሬም ወደ እሱ የመጡትን ወታደሮች ወደ ስፍራቸው እንዲመለሱ አሰናበታቸው። እነሱ ግን በይሁዳ እጅግ ተበሳጭተው በታላቅ ቁጣ ወደ ገዛ አገራቸው ተመለሱ። 11  ከዚያም አሜስያስ ተበረታታ፤ የራሱንም ወታደሮች እየመራ ወደ ጨው ሸለቆ+ ሄደ፤ ደግሞም 10,000 የሚሆኑ የሴይር ሰዎችን ገደለ።+ 12  የይሁዳም ሰዎች 10,000 የሚሆኑ ሰዎችን ማረኩ። ከዚያም ወደ ገደል አፋፍ ወስደው፣ ከአፋፉ ላይ ቁልቁል ወረወሯቸው፤ ሁሉም ተፈጥፍጠው ብትንትናቸው ወጣ። 13  ይሁንና አሜስያስ ከእሱ ጋር ወደ ጦርነት እንዳይሄዱ ያሰናበታቸው ወታደሮች+ ከሰማርያ+ አንስቶ እስከ ቤትሆሮን+ ድረስ ያሉትን የይሁዳ ከተሞች ወረሩ፤ 3,000 ሰዎችም ገደሉ፤ ብዙ ምርኮም ወሰዱ። 14  አሜስያስ ኤዶማውያንን መትቶ ከተመለሰ በኋላ የሴይርን ሰዎች አማልክት ይዞ በመምጣት ለራሱ አማልክት አድርጎ አቆማቸው፤+ በእነሱም ፊት ይሰግድ እንዲሁም የሚጨስ መሥዋዕት ያቀርብላቸው ጀመር። 15  ስለሆነም የይሖዋ ቁጣ በአሜስያስ ላይ ነደደ፤ ነቢይም ልኮ “የገዛ ሕዝባቸውን ከእጅህ መታደግ ያልቻሉትን የሕዝቡን አማልክት የምትከተለው ለምንድን ነው?” አለው።+ 16  በዚህ ጊዜ ንጉሡ ነቢዩን “የንጉሡ አማካሪ አድርገን ሾመንሃል?+ ዝም በል!+ መሞት ትፈልጋለህ?” አለው። ነቢዩም ዝም አለ፤ ሆኖም “ይህን በማድረግህና ምክሬን ባለመስማትህ አምላክ ሊያጠፋህ እንደወሰነ ተረዳሁ” አለ።+ 17  የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስ ከአማካሪዎቹ ጋር ከተማከረ በኋላ የእስራኤል ንጉሥ ወደሆነው ወደ ኢዩ ልጅ ወደ ኢዮዓካዝ ልጅ ወደ ኢዮዓስ “ና፣ ውጊያ እንግጠም”* የሚል መልእክት ላከበት።+ 18  የእስራኤል ንጉሥ ኢዮዓስ ደግሞ ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ አሜስያስ ይህን መልእክት ላከ፦ “በሊባኖስ የሚገኘው ኩርንችት በሊባኖስ ወደሚገኘው አርዘ ሊባኖስ ‘ሴት ልጅህን ለወንድ ልጄ ዳርለት’ የሚል መልእክት ላከ። ይሁን እንጂ በሊባኖስ የነበረ አንድ የዱር አውሬ በዚያ ሲያልፍ ያን ኩርንችት ረገጠው። 19  አንተ ‘እኔ ኤዶምን መትቻለሁ’ ብለሃል።+ በመሆኑም ልብህ ክብር በመሻት ታብዮአል። አሁን ግን አርፈህ ቤትህ* ተቀመጥ። በራስህ ላይ ለምን ጥፋት ትጋብዛለህ? ደግሞስ ራስህንም ሆነ ይሁዳን ለምን ለውድቀት ትዳርጋለህ?” 20  አሜስያስ ግን አልሰማም፤+ የኤዶምን አማልክት በመከተላቸው+ እውነተኛው አምላክ በጠላቶቻቸው እጅ አሳልፎ ሊሰጣቸው ወስኗልና።+ 21  በመሆኑም የእስራኤል ንጉሥ ኢዮዓስ ወጣ፤ እሱና የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስም በይሁዳ በምትገኘው በቤትሼሜሽ+ ተጋጠሙ። 22  ይሁዳ በእስራኤል ድል ተመታ፤ እያንዳንዳቸውም ወደየቤታቸው* ሸሹ። 23  የእስራኤል ንጉሥ ኢዮዓስ የኢዮአካዝ* ልጅ፣ የኢዮዓስ ልጅ የሆነውን የይሁዳን ንጉሥ አሜስያስን ቤትሼሜሽ ላይ ያዘው። ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም አመጣው፤ የኢየሩሳሌምን ቅጥር፣ ከኤፍሬም በር+ አንስቶ እስከ ማዕዘን በር+ ድረስ አፈረሰ፤ ርዝመቱም 400 ክንድ* ያህል ነበር። 24  በእውነተኛው አምላክ ቤት በኦቤድዔዶም እጅና* በንጉሡ ቤት* ግምጃ ቤቶች+ የተገኘውን ወርቅ፣ ብርና ዕቃ ሁሉ እንዲሁም የታገቱትን ሰዎች ወሰደ። ከዚያም ወደ ሰማርያ ተመለሰ። 25  የእስራኤል ንጉሥ የኢዮዓካዝ ልጅ ኢዮዓስ+ ከሞተ በኋላ፣ የይሁዳ ንጉሥ የኢዮዓስ ልጅ አሜስያስ+ 15 ዓመት ኖረ።+ 26  ከመጀመሪያ አንስቶ እስከ መጨረሻ ድረስ ያለው የቀረው የአሜስያስ ታሪክ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ውስጥ ተጽፎ የለም? 27  አሜስያስ ይሖዋን መከተል ከተወበት ጊዜ ጀምሮ በኢየሩሳሌም በእሱ ላይ ሲያሴሩ ቆዩ፤+ እሱም ወደ ለኪሶ ሸሸ፤ እነሱ ግን ተከታትለው እንዲይዙት ሰዎችን ወደ ለኪሶ ላኩ፤ በዚያም ገደሉት። 28  ከዚያም በፈረሶች ላይ ጭነው አመጡት፤ ከአባቶቹም ጋር በይሁዳ ከተማ ቀበሩት።

የግርጌ ማስታወሻ

ቃል በቃል “የተመረጡ።”
አንድ ታላንት 34.2 ኪሎ ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “ፊት ለፊት እንገናኝ።”
ወይም “በቤተ መንግሥትህ።”
ቃል በቃል “ወደየድንኳናቸው።”
ርዝመቱም ወደ 178 ሜትር ገደማ ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
አካዝያስ ተብሎም ይጠራል።
ወይም “በኦቤድዔዶም ኃላፊነት ሥርና።”
ወይም “ቤተ መንግሥት።”