ሁለተኛ ዜና መዋዕል 27:1-9

  • ኢዮዓታም በይሁዳ ላይ ነገሠ (1-9)

27  ኢዮዓታም+ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 25 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለ16 ዓመት ገዛ። እናቱም የሩሻህ ትባል ነበር፤ እሷም የሳዶቅ ልጅ ነበረች።+  ኢዮዓታም አባቱ ዖዝያ እንዳደረገው ሁሉ በይሖዋ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር አደረገ፤+ ይሁንና ሥርዓቱን ጥሶ ወደ ይሖዋ ቤተ መቅደስ አልገባም።+ ሕዝቡ ግን ክፉ ድርጊት መፈጸሙን አልተወም ነበር።  እሱም የይሖዋን ቤት+ የላይኛውን በር ሠራ፤ በኦፌልም+ ቅጥር ላይ መጠነ ሰፊ የግንባታ ሥራ አከናወነ።  በተጨማሪም በተራራማው የይሁዳ ክልል+ ከተሞችን ሠራ፤+ በደን በተሸፈኑት ስፍራዎችም ምሽጎችንና+ ማማዎችን+ ገነባ።  ከአሞናውያንም ንጉሥ ጋር ተዋጋ፤+ በመጨረሻም አሸነፋቸው፤ በመሆኑም አሞናውያን በዚያ ዓመት 100 የብር ታላንት፣* 10,000 የቆሮስ መስፈሪያ* ስንዴና 10,000 የቆሮስ መስፈሪያ ገብስ ሰጡት። በተጨማሪም አሞናውያን በሁለተኛውና በሦስተኛው ዓመት ይህንኑ ግብር አመጡለት።+  ኢዮዓታም በአምላኩ በይሖዋ ፊት መንገዱን ስላጸና* ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበረታ ሄደ።  የቀረው የኢዮዓታም ታሪክ፣ ያካሄዳቸው ጦርነቶችና የተከተለው መንገድ ሁሉ በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት መጽሐፍ ውስጥ ተጽፈዋል።+  እሱ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 25 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለ16 ዓመት ገዛ።+  በመጨረሻም ኢዮዓታም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊት ከተማም+ ቀበሩት። በእሱም ምትክ ልጁ አካዝ ነገሠ።+

የግርጌ ማስታወሻ

አንድ ታላንት 34.2 ኪሎ ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
አንድ ቆሮስ 220 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “ስላዘጋጀ።”