ሁለተኛ ዜና መዋዕል 29:1-36

  • ሕዝቅያስ በይሁዳ ላይ ነገሠ (1, 2)

  • ሕዝቅያስ ያካሄደው ተሃድሶ (3-11)

  • ቤተ መቅደሱን አጸዳ (12-19)

  • በቤተ መቅደሱ ውስጥ ንጹሑ አምልኮ ዳግመኛ መከናወን ጀመረ (20-36)

29  ሕዝቅያስ+ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 25 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለ29 ዓመት ገዛ። እናቱ አቢያህ ትባል ነበር፤ እሷም የዘካርያስ ልጅ ነበረች።+  አባቱ ዳዊት እንዳደረገው ሁሉ+ እሱም በይሖዋ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር አደረገ።+  መግዛት በጀመረ በመጀመሪያው ዓመት፣ በመጀመሪያው ወር የይሖዋን ቤት በሮች ከፈተ፤ አደሳቸውም።+  ከዚያም ካህናቱንና ሌዋውያኑን አስጠርቶ በምሥራቅ በኩል በሚገኘው አደባባይ ሰበሰባቸው።  እንዲህም አላቸው፦ “እናንተ ሌዋውያን፣ ስሙኝ። ራሳችሁንም ሆነ የአባቶቻችሁን አምላክ የይሖዋን ቤት ቀድሱ፤+ ርኩስ የሆነውንም ነገር ከቅዱሱ ስፍራ አስወግዱ።+  አባቶቻችን ታማኞች አልነበሩም፤ በአምላካችን በይሖዋም ፊት ክፉ ነገር አድርገዋል።+ እሱን የተዉት ከመሆኑም ሌላ ከይሖዋ የማደሪያ ድንኳን ፊታቸውን መልሰዋል፤ ጀርባቸውንም ሰጥተውታል።+  በተጨማሪም የበረንዳውን በሮች ዘጉ፤+ መብራቶቹንም አጠፉ።+ ዕጣን ማጠንና+ በተቀደሰው ስፍራ ለእስራኤል አምላክ የሚቃጠል መሥዋዕት ማቅረብ+ አቆሙ።  ስለዚህ የይሖዋ ቁጣ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ ነደደ፤+ በመሆኑም በገዛ ዓይናችሁ እንደምታዩት መቀጣጫ፣ የሰዎች መደነቂያና ማፏጫ* አደረጋቸው።+  በዚህም የተነሳ አባቶቻችን በሰይፍ ወደቁ፤+ እንዲሁም ወንዶች ልጆቻችን፣ ሴቶች ልጆቻችንና ሚስቶቻችን ተማርከው ተወሰዱ።+ 10  አሁንም የሚነድ ቁጣው ከእኛ እንዲመለስ ከእስራኤል አምላክ ከይሖዋ ጋር ቃል ኪዳን ለመግባት ከልቤ ተመኝቻለሁ።+ 11  እንግዲህ ልጆቼ በፊቱ እንድትቆሙ፣ እንድታገለግሉትና+ የሚጨስ መሥዋዕቱን እንድታቀርቡ+ ይሖዋ የመረጠው እናንተን ስለሆነ አሁን ቸልተኛ የምትሆኑበት* ጊዜ አይደለም።” 12  በዚህ ጊዜ ሌዋውያኑ ለሥራ ተነሱ፤ እነሱም የሚከተሉት ናቸው፦ ከቀአታውያን+ መካከል የአማሳይ ልጅ ማሃት እና የአዛርያስ ልጅ ኢዩኤል፤ ከሜራራውያን+ መካከል የአብዲ ልጅ ቂስ እና የይሃሌልዔል ልጅ አዛርያስ፤ ከጌድሶናውያን+ መካከል የዚማ ልጅ ዮአህ እና የዮአህ ልጅ ኤደን፤ 13  ከኤሊጻፋን ልጆች መካከል ሺምሪ እና የኡዔል፤ ከአሳፍ+ ልጆች መካከል ዘካርያስ እና ማታንያህ፤ 14  ከሄማን+ ልጆች መካከል የሂኤል እና ሺምአይ እንዲሁም ከየዱቱን+ ልጆች መካከል ሸማያህ እና ዑዚኤል። 15  እነሱም ወንድሞቻቸውን ከሰበሰቡና ራሳቸውን ከቀደሱ በኋላ ንጉሡ በይሖዋ ቃል ባዘዛቸው መሠረት የይሖዋን ቤት ለማንጻት መጡ።+ 16  ከዚያም ካህናቱ የይሖዋን ቤት ለማንጻት ወደ ውስጥ ገቡ፤ በይሖዋ ቤተ መቅደስ ውስጥ ያገኙትን ርኩስ የሆነ ነገር ሁሉ አውጥተው ወደ ይሖዋ ቤት ግቢ+ ወሰዱት። ሌዋውያኑ ደግሞ ከዚያ አውጥተው በቄድሮን ሸለቆ+ ውስጥ ጣሉት። 17  እነሱም በዚህ መንገድ በመጀመሪያው ወር፣ በመጀመሪያው ቀን የማንጻት ሥራውን ጀመሩ፤ በወሩም በስምንተኛ ቀን ወደ ይሖዋ ቤት በረንዳ+ ደረሱ። የይሖዋንም ቤት ለስምንት ቀን ቀደሱ፤ በመጀመሪያውም ወር በ16ኛው ቀን ሥራውን አጠናቀቁ። 18  ከዚያም ወደ ንጉሥ ሕዝቅያስ ገብተው እንዲህ አሉት፦ “የይሖዋን ቤት በሙሉ፣ የሚቃጠለው መባ የሚቀርብበትን መሠዊያና+ ዕቃዎቹን በሙሉ+ እንዲሁም የሚነባበረው ዳቦ*+ የሚቀመጥበትን ጠረጴዛና ዕቃዎቹን በሙሉ አንጽተናል። 19  ንጉሥ አካዝ በንግሥና ዘመኑ ታማኝነቱን ባጎደለ ጊዜ+ ከቦታቸው ያስወገዳቸውን ዕቃዎች ሁሉ አዘጋጅተን ቀድሰናቸዋል፤+ ዕቃዎቹም በይሖዋ መሠዊያ ፊት ይገኛሉ።” 20  ንጉሥ ሕዝቅያስም በማለዳ ተነስቶ የከተማዋን መኳንንት ሰበሰበ፤ ከዚያም ወደ ይሖዋ ቤት ወጡ። 21  እነሱም ለመንግሥቱ፣ ለመቅደሱና ለይሁዳ የኃጢአት መባ ሆነው የሚቀርቡ ሰባት በሬዎች፣ ሰባት አውራ በጎች፣ ሰባት ተባዕት የበግ ጠቦቶችና ሰባት ተባዕት ፍየሎች አመጡ።+ እሱም በይሖዋ መሠዊያ ላይ እንዲያቀርቧቸው የአሮን ዘሮች ለሆኑት ካህናት ነገራቸው። 22  ከዚያም ከብቶቹን አረዱ፤+ ካህናቱም ደሙን ወስደው በመሠዊያው ላይ ረጩት፤+ ቀጥሎም አውራ በጎቹን አርደው ደሙን መሠዊያው ላይ ረጩ፤ ተባዕት የበግ ጠቦቶቹንም አርደው ደሙን በመሠዊያው ላይ ረጩ። 23  ከዚያ በኋላ ለኃጢአት መባ የሚሆኑትን ተባዕት ፍየሎች በንጉሡና በጉባኤው ፊት አቀረቧቸው፤ እጆቻቸውንም ጫኑባቸው። 24  ካህናቱም ፍየሎቹን አርደው ለእስራኤል ሁሉ ማስተሰረያ እንዲሆን ደማቸውን በመሠዊያው ላይ የኃጢአት መባ አድርገው አቀረቡ፤ ምክንያቱም ንጉሡ የሚቃጠለው መባና ለኃጢአት የሚሆነው መባ ለመላው እስራኤል እንዲቀርብ አዝዞ ነበር። 25  እሱም በዳዊት፣+ የንጉሡ ባለ ራእይ በሆነው በጋድና+ በነቢዩ ናታን+ በተሰጠው ትእዛዝ መሠረት ሌዋውያኑን ሲምባል፣ ባለ አውታር መሣሪያዎችና በገና+ አስይዞ በይሖዋ ቤት እንዲቆሙ አደረገ፤ ይህም ይሖዋ በነቢያቱ አማካኝነት የሰጠው ትእዛዝ ነበር። 26  በመሆኑም ሌዋውያኑ የዳዊትን የሙዚቃ መሣሪያዎች፣ ካህናቱ ደግሞ መለከቶችን+ ይዘው ቆሙ። 27  ከዚያም ሕዝቅያስ የሚቃጠለው መሥዋዕት በመሠዊያው ላይ እንዲቀርብ አዘዘ።+ የሚቃጠለው መባ መቅረብ በጀመረበት ጊዜ የይሖዋ መዝሙር ተሰማ፤ ደግሞም የእስራኤልን ንጉሥ የዳዊትን የሙዚቃ መሣሪያዎች ተከትለው መለከቶቹ ተነፉ። 28  መዝሙሩ በሚዘመርበትና መለከቶቹ በሚነፉበት ጊዜም መላው ጉባኤ ተደፍቶ ሰገደ፤ የሚቃጠለው መባ እስኪጠናቀቅ ድረስ ይህ ሁሉ መከናወኑን ቀጠለ። 29  መባውን አቅርበው እንደጨረሱም ንጉሡና አብረውት ያሉት ሁሉ በግንባራቸው ተደፍተው ሰገዱ። 30  ንጉሥ ሕዝቅያስና መኳንንቱ በዳዊትና+ በባለ ራእዩ በአሳፍ+ መዝሙራት ይሖዋን እንዲያወድሱ ሌዋውያኑን አዘዙ። እነሱም በታላቅ ደስታ ውዳሴ አቀረቡ፤ ተደፍተውም ሰገዱ። 31  ከዚያም ሕዝቅያስ እንዲህ አለ፦ “አሁን እናንተ ለይሖዋ ስለተለያችሁ* ቅረቡ፤ ለይሖዋም ቤት መሥዋዕቶችና የምስጋና መባዎች አምጡ።” በመሆኑም ጉባኤው መሥዋዕቶችንና የምስጋና መባዎችን ማምጣት ጀመረ፤ ልቡ ያነሳሳውም ሁሉ የሚቃጠል መባ አመጣ።+ 32  ጉባኤው ያመጣቸው የሚቃጠሉ መባዎች ብዛት 70 ከብቶች፣ 100 አውራ በጎችና 200 ተባዕት የበግ ጠቦቶች ነበሩ፤ እነዚህ ሁሉ ለይሖዋ የሚቃጠል መባ+ ሆነው የሚቀርቡ ነበሩ፤ 33  ሌሎቹ ቅዱስ መባዎች ደግሞ 600 ከብቶችና 3,000 በጎች ነበሩ። 34  ይሁንና የሚቃጠል መባ ሆነው የሚቀርቡትን እንስሳት ሁሉ ለመግፈፍ በቂ ካህናት ስላልነበሩ ሥራው እስኪጠናቀቅና ካህናቱ ራሳቸውን እስኪቀድሱ+ ድረስ ወንድሞቻቸው የሆኑት ሌዋውያን ረዷቸው፤+ ሌዋውያኑ ራሳቸውን በመቀደስ ረገድ ከካህናቱ ይበልጥ ጠንቃቆች* ነበሩና። 35  በተጨማሪም የሚቃጠሉት መባዎችና+ የኅብረት መሥዋዕቶቹ+ ስብ እንዲሁም ከሚቃጠሉት መባዎች ጋር የሚቀርቡት የመጠጥ መባዎች+ ብዙ ነበሩ። በዚህ መንገድ የይሖዋ ቤት አገልግሎት እንደገና ተደራጀ።* 36  ሕዝቅያስና ሕዝቡ ሁሉ እውነተኛው አምላክ ለሕዝቡ ይህን በማቋቋሙና ይህ ሁሉ ነገር በአጭር ጊዜ ውስጥ በመከናወኑ እጅግ ተደሰቱ።+

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ማላገጫ።”
ወይም “የምታርፉበት።”
ገጸ ኅብስቱን ያመለክታል።
ቃል በቃል “እጃችሁን ስለሞላችሁ።”
ቃል በቃል “ይበልጥ ልበ ቀና።”
ወይም “ተዘጋጀ።”