ሁለተኛ ዜና መዋዕል 3:1-17

  • ሰለሞን ቤተ መቅደሱን መገንባት ጀመረ (1-7)

  • ቅድስተ ቅዱሳኑ (8-14)

  • ሁለቱ የመዳብ ዓምዶች (15-17)

3  ከዚያም ሰለሞን በኢየሩሳሌም፣ ይሖዋ ለአባቱ ለዳዊት በተገለጠበት+ በሞሪያ ተራራ+ ይኸውም ዳዊት በኢያቡሳዊው በኦርናን+ አውድማ ላይ ባዘጋጀው ቦታ የይሖዋን ቤት መሥራት ጀመረ።+  በነገሠ በአራተኛው ዓመት፣ በሁለተኛው ወር፣ በሁለተኛው ቀን የግንባታውን ሥራ ጀመረ።  ሰለሞን የእውነተኛውን አምላክ ቤት ለመሥራት የጣለው መሠረት በቀድሞው መለኪያ* ርዝመቱ 60 ክንድ፣ ወርዱም 20 ክንድ ነበር።+  ከቤቱ ፊት ያለው በረንዳ ርዝመቱ 20 ክንድ ሲሆን ይህም ከቤቱ ወርድ ጋር እኩል ነው፤ ከፍታው ደግሞ 120* ነው፤ ውስጡንም በንጹሕ ወርቅ ለበጠው።+  ዋናውን ክፍል* በጥድ እንጨት አልብሶ በጥሩ ወርቅ ለበጠው፤+ ከዚያም በዘንባባ ዛፍ ምስሎችና+ በሰንሰለቶች+ አስጌጠው።  በተጨማሪም ቤቱን ባማሩና በከበሩ ድንጋዮች ለበጠው፤+ የተጠቀመበትም ወርቅ+ ከፓርዋይም የመጣ ነበር።  እሱም ቤቱን፣ ወራጆቹን፣ ደፎቹን፣ ግድግዳዎቹንና በሮቹን በወርቅ ለበጣቸው፤+ በግድግዳዎቹም ላይ የኪሩቦችን ምስል ቀረጸ።+  ከዚያም የቅድስተ ቅዱሳኑን ክፍል* ሠራ፤+ ርዝመቱ ከቤቱ ወርድ ጋር እኩል የነበረ ሲሆን 20 ክንድ ነበር፤ ወርዱም 20 ክንድ ነበር። ከዚያም 600 ታላንት* በሚሆን ጥሩ ወርቅ ለበጠው።+  ለምስማሮቹ የዋለው ወርቅ 50 ሰቅል* ይመዝን ነበር፤ ሰገነት ላይ ያሉትንም ክፍሎች በወርቅ ለበጣቸው። 10  ከዚያም በቅድስተ ቅዱሳኑ ክፍል* ውስጥ ሁለት የኪሩቦች ቅርጽ ሠርቶ በወርቅ ለበጣቸው።+ 11  የኪሩቦቹ ክንፎች+ አጠቃላይ ርዝመት 20 ክንድ ነበር፤ የመጀመሪያው ኪሩብ አንደኛው ክንፍ አምስት ክንድ ርዝመት ያለው ሲሆን የቤቱን ግድግዳ ይነካ ነበር፤ ሌላኛው ክንፉም አምስት ክንድ ርዝመት ያለው ሲሆን የሁለተኛውን ኪሩብ ክንፍ ይነካ ነበር። 12  የሁለተኛውም ኪሩብ አንደኛው ክንፍ አምስት ክንድ ርዝመት ያለው ሲሆን በአንጻሩ ያለውን የቤቱን ግድግዳ ይነካ ነበር፤ ሌላኛው ክንፉም አምስት ክንድ ርዝመት ያለው ሲሆን የመጀመሪያውን ኪሩብ ክንፍ ይነካ ነበር። 13  የተዘረጉት የእነዚህ ኪሩቦች ክንፎች 20 ክንድ ነበሩ፤ ኪሩቦቹም ፊታቸውን ወደ ውስጥ* አዙረው በእግራቸው ቆመው ነበር። 14  በተጨማሪም ከሰማያዊ ክር፣ ከሐምራዊ ሱፍ፣ ከደማቅ ቀይ ክርና ጥራት ካለው ጨርቅ መጋረጃ+ ሠርቶ የኪሩቦችን ምስል ጠለፈበት።+ 15  ከቤቱ ፊት ለፊትም 35 ክንድ ርዝመት ያላቸው ሁለት ዓምዶችን+ ሠራ፤ በእያንዳንዱ ዓምድ ላይ ያለው የዓምድ ራስ አምስት ክንድ ነበር።+ 16  እንደ ሐብል ያሉ ሰንሰለቶች ሠርቶም በዓምዶቹ አናት ላይ አደረጋቸው፤ እንዲሁም 100 የሮማን ፍሬዎችን ሠርቶ ከሰንሰለቶቹ ጋር አያያዛቸው። 17  ዓምዶቹንም አንዱን በቀኝ* ሌላውን በግራ* አድርጎ በቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት አቆማቸው፤ በስተ ቀኝ ያለውን ያኪን፣* በስተ ግራ ያለውን ደግሞ ቦዔዝ* ብሎ ሰየማቸው።

የግርጌ ማስታወሻ

በመደበኛው መለኪያ መሠረት አንድ ክንድ 44.5 ሴንቲ ሜትር ነው፤ አንዳንዶች ግን “የቀድሞው መለኪያ” 51.8 ሴንቲ ሜትር የሚሆነውን ረጅሙን ክንድ እንደሚያመለክት ይሰማቸዋል። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
የመለኪያው ምንነት በእርግጠኝነት አይታወቅም።
ቃል በቃል “ታላቁን ቤት።” ቅድስቱን የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም።
አንድ ታላንት 34.2 ኪሎ ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ቃል በቃል “ቤት።”
አንድ ሰቅል 11.4 ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ቃል በቃል “ቤት።”
ወደ ቅድስቱ ማለት ነው።
ወይም “በደቡብ።”
ወይም “በሰሜን።”
“እሱ [ማለትም ይሖዋ] አጽንቶ ይመሥርት” የሚል ትርጉም አለው።
“በብርታት” ማለት ሳይሆን አይቀርም።