ሁለተኛ ዜና መዋዕል 30:1-27

  • ሕዝቅያስ የፋሲካን በዓል አከበረ (1-27)

30  ሕዝቅያስ ለእስራኤል አምላክ ለይሖዋ ፋሲካን*+ ለማክበር በኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ወደ ይሖዋ ቤት እንዲመጡ ለእስራኤልና ለይሁዳ ሁሉ መልእክት ላከ፤+ ለኤፍሬምና ለምናሴም እንኳ ሳይቀር ደብዳቤ ጻፈ።+  ይሁን እንጂ ንጉሡና መኳንንቱ እንዲሁም በኢየሩሳሌም ያለው መላው ጉባኤ ፋሲካን በሁለተኛው ወር ለማክበር ወሰኑ፤+  በቂ ካህናት ራሳቸውን ስላልቀደሱና+ ሕዝቡ ገና በኢየሩሳሌም ስላልተሰበሰበ ፋሲካውን በመደበኛው ጊዜ ማክበር አልቻሉም ነበር።+  ይህ ዝግጅት በንጉሡና በመላው ጉባኤ ፊት ተቀባይነት አገኘ።  ስለዚህ ሕዝቡ ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ለእስራኤል አምላክ ለይሖዋ ፋሲካን እንዲያከብር በመላው እስራኤል፣ ከቤርሳቤህ አንስቶ እስከ ዳን+ ድረስ አዋጅ እንዲነገር ወሰኑ፤ በተጻፈው መሠረት በዓሉን በጋራ አክብረው አያውቁም ነበር።+  ከዚያም መልእክተኞቹ* የንጉሡንና የመኳንንቱን ደብዳቤዎች ይዘው ወደ እስራኤልና ወደ ይሁዳ ሁሉ ሄዱ፤ ንጉሡም እንዲህ የሚል ትእዛዝ አስተላልፎ ነበር፦ “የእስራኤል ሕዝብ ሆይ፣ የአብርሃም፣ የይስሐቅና የእስራኤል አምላክ ወደሆነው ወደ ይሖዋ ተመለሱ፤ እሱም ከአሦር ነገሥታት እጅ ወዳመለጡት ቀሪዎች ይመለሳል።+  አሁን እንደምታዩት፣ መቀጣጫ እስኪያደርጋቸው ድረስ በአባቶቻቸው አምላክ በይሖዋ ላይ ታማኝነት የጎደለው ድርጊት እንደፈጸሙት እንደ አባቶቻችሁና እንደ ወንድሞቻችሁ አትሁኑ።+  አሁንም እንደ አባቶቻችሁ አንገታችሁን አታደንድኑ።+ የሚነድ ቁጣው ከእናንተ እንዲመለስ ለይሖዋ ተገዙ፤+ ለዘላለም ወደቀደሰው መቅደሱ ኑ፤+ አምላካችሁን ይሖዋን አገልግሉ።  ወደ ይሖዋ ስትመለሱ ወንድሞቻችሁና ልጆቻችሁ በማረኳቸው ዘንድ ምሕረት ያገኛሉ፤+ ወደዚህች ምድር እንዲመለሱም ይለቋቸዋል፤+ አምላካችሁ ይሖዋ ሩኅሩኅና* መሐሪ ነውና፤+ ወደ እሱም ከተመለሳችሁ ፊቱን አያዞርባችሁም።”+ 10  ስለዚህ መልእክተኞቹ* ከከተማ ወደ ከተማ እየተዘዋወሩ የኤፍሬምንና የምናሴን+ እንዲሁም የዛብሎንን አገር ሁሉ አዳረሱ፤ ሕዝቡ ግን ያፌዝባቸውና ይሳለቅባቸው ነበር።+ 11  ይሁን እንጂ ከአሴር፣ ከምናሴና ከዛብሎን ምድር የተወሰኑ ሰዎች ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ወደ ኢየሩሳሌም መጡ።+ 12  በተጨማሪም የእውነተኛው አምላክ እጅ ከይሁዳ ሰዎች ጋር ስለነበር ንጉሡና መኳንንቱ በይሖዋ ቃል መሠረት ያስተላለፉትን ትእዛዝ እንዲፈጽሙ አንድ ልብ ሰጣቸው። 13  በሁለተኛው ወር+ የቂጣን በዓል+ ለማክበር እጅግ ብዙ ሕዝብ በኢየሩሳሌም ተሰበሰበ፤ ጉባኤው እጅግ ታላቅ ነበር። 14  እነሱም ተነስተው በኢየሩሳሌም የነበሩትን መሠዊያዎችና የዕጣን መሠዊያዎች ከነቃቀሉ+ በኋላ በቄድሮን ሸለቆ ውስጥ ጣሏቸው። 15  ከዚያም በሁለተኛው ወር በ14ኛው ቀን የፋሲካን መሥዋዕት አረዱ። ካህናቱና ሌዋውያኑ አፍረው ስለነበር ራሳቸውን ቀደሱ፤ ወደ ይሖዋም ቤት የሚቃጠል መባ አመጡ። 16  በእውነተኛው አምላክ ሰው በሙሴ ሕግ መሠረት የተሰጣቸውን መመሪያ ተከትለው መደበኛ ቦታቸውን ያዙ፤ ከዚያም ካህናቱ ከሌዋውያኑ እጅ የተቀበሉትን ደም ረጩ።+ 17  በጉባኤው መካከል ራሳቸውን ያልቀደሱ ብዙ ሰዎች ስለነበሩ ሌዋውያኑ ያልነጹትን ሰዎች+ ለይሖዋ ለመቀደስ የፋሲካን መሥዋዕት የማረድ ኃላፊነት ተጥሎባቸው ነበር። 18  እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ በተለይም ከኤፍሬም፣ ከምናሴ፣+ ከይሳኮርና ከዛብሎን የመጡ ሰዎች ራሳቸውን ያላነጹ ቢሆንም የተጻፈውን መመሪያ ተላልፈው ፋሲካውን በሉ። ይሁንና ሕዝቅያስ እንዲህ ሲል ጸለየላቸው፦ “ጥሩ የሆነው+ ይሖዋ ይቅር ይበል፤ 19  የቅድስናውን መሥፈርት አሟልተው ራሳቸውን ባያነጹም+ እንኳ እውነተኛ አምላክ የሆነውን የአባቶቻቸውን አምላክ ይሖዋን ለመፈለግ ልባቸውን ያዘጋጁትን+ ሁሉ ይቅር ይበላቸው።” 20  ይሖዋም ሕዝቅያስን ሰምቶ ሕዝቡን ይቅር አለ።* 21  በመሆኑም በኢየሩሳሌም የተገኙት እስራኤላውያን የቂጣን በዓል+ ለሰባት ቀናት በታላቅ ደስታ አከበሩ፤+ ሌዋውያኑና ካህናቱም ከፍ ባለ ድምፅ ለይሖዋ የሙዚቃ መሣሪያዎቻቸውን በመጫወት በየዕለቱ ይሖዋን ያወድሱ ነበር።+ 22  በተጨማሪም ሕዝቅያስ ይሖዋን በማስተዋል ያገለግሉ የነበሩትን ሌዋውያን ሁሉ በማነጋገር አበረታታቸው።* እነሱም የኅብረት መሥዋዕቶች+ በማቅረብና ለአባቶቻቸው አምላክ ለይሖዋ ምስጋና በማቅረብ በዓሉ ተጀምሮ እስኪያበቃ ድረስ ለሰባት ቀናት በሉ።+ 23  ከዚያም መላው ጉባኤ ለተጨማሪ ሰባት ቀናት በዓሉን ለማክበር ወሰነ፤ በመሆኑም እንደገና ለሰባት ቀናት በዓሉን በታላቅ ደስታ አከበሩ።+ 24  የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስም 1,000 በሬዎችና 7,000 በጎች ለጉባኤው ሰጥቶ ነበር፤ መኳንንቱ ደግሞ 1,000 በሬዎችና 10,000 በጎች ለጉባኤው አበረከቱ፤+ እጅግ ብዙ ካህናትም ራሳቸውን ቀደሱ።+ 25  መላው የይሁዳ ጉባኤ፣ ካህናቱ፣ ሌዋውያኑ፣ ከእስራኤል የመጣው መላው ጉባኤ+ እንዲሁም ከእስራኤል ምድር የመጡትና በይሁዳ የሚኖሩት የባዕድ አገር ሰዎች+ እጅግ ተደሰቱ። 26  ከእስራኤል ንጉሥ ከዳዊት ልጅ ከሰለሞን ዘመን አንስቶ በኢየሩሳሌም እንዲህ ያለ ነገር ሆኖ ስለማያውቅ በኢየሩሳሌም ታላቅ ደስታ ሆነ።+ 27  በመጨረሻም ሌዋውያኑ ካህናት ተነስተው ሕዝቡን ባረኩ፤+ አምላክም ድምፃቸውን ሰማ፤ ጸሎታቸውም ወደ ቅዱሱ መኖሪያው ወደ ሰማያት ደረሰ።

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “የማለፍን በዓል።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ቃል በቃል “ሯጮቹ።”
ወይም “ቸርና።”
ቃል በቃል “ሯጮቹ።”
ቃል በቃል “ፈወሰ።”
ቃል በቃል “ለልባቸው ተናገረ።”