ሁለተኛ ዜና መዋዕል 33:1-25

  • ምናሴ በይሁዳ ላይ ነገሠ (1-9)

  • ምናሴ ንስሐ ገባ (10-17)

  • ምናሴ ሞተ (18-20)

  • አምዖን በይሁዳ ላይ ነገሠ (21-25)

33  ምናሴ+ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 12 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ 55 ዓመት ገዛ።+  እሱም ይሖዋ ከእስራኤል ሕዝብ ፊት ያባረራቸው ብሔራት ይፈጽሟቸው የነበሩትን አስጸያፊ ልማዶች በመከተል በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ።+  አባቱ ሕዝቅያስ አፍርሷቸው የነበሩትን ከፍ ያሉ የማምለኪያ ቦታዎች መልሶ ገነባ፣+ ለባአል አማልክት መሠዊያዎችን አቆመ፣ የማምለኪያ ግንዶች* ሠራ እንዲሁም ለሰማይ ሠራዊት ሁሉ ሰገደ፤ እነሱንም አገለገለ።+  በተጨማሪም ይሖዋ “ኢየሩሳሌም ለዘላለም በስሜ ትጠራለች”+ ብሎ በተናገረለት በይሖዋ ቤት ውስጥ መሠዊያዎችን ሠራ።+  ደግሞም በይሖዋ ቤት በሚገኙት በሁለቱ ግቢዎች ውስጥ ለሰማይ ሠራዊት ሁሉ መሠዊያዎችን ሠራ።+  በሂኖም ልጅ ሸለቆም+ የገዛ ልጆቹን ለእሳት አሳልፎ ሰጠ፤+ አስማተኛ፣+ ሟርተኛና መተተኛ ሆነ፤ መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችን ቀጠረ።+ ይሖዋን ያስቆጣው ዘንድ በእሱ ፊት በጣም ብዙ መጥፎ ነገሮችን ሠራ።  ምናሴም የሠራውን የተቀረጸ ምስል አምላክ ለዳዊትና ለልጁ ለሰለሞን እንዲህ ብሎ በተናገረለት በእውነተኛው አምላክ ቤት ውስጥ አስቀመጠው፦+ “በዚህ ቤትና ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ በመረጥኳት በኢየሩሳሌም ስሜን ለዘለቄታው አኖራለሁ።+  እነሱ በሙሴ በኩል የሰጠኋቸውን ሕግ ሁሉ እንዲሁም ሥርዓቶቹንና ድንጋጌዎቹን በጥንቃቄ ይጠብቁ እንጂ የእስራኤላውያን እግር ለአባቶቻቸው ከሰጠሁት ምድር ዳግመኛ እንዲወጣ አላደርግም።”  ምናሴም ይሖዋ ከእስራኤላውያን ፊት ካጠፋቸው ብሔራት የባሰ ክፉ ነገር እንዲሠሩ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ነዋሪዎች አሳተ።+ 10  ይሖዋ ለምናሴና ለሕዝቡ በተደጋጋሚ ቢናገርም እነሱ ለመስማት ፈቃደኛ አልሆኑም።+ 11  ስለዚህ ይሖዋ የአሦርን ንጉሥ ሠራዊት አለቆች አመጣባቸው፤ እነሱም ምናሴን በመንጠቆ ያዙት፤* ከመዳብ በተሠሩ ሁለት የእግር ብረቶች አስረው ወደ ባቢሎን ወሰዱት። 12  በተጨነቀም ጊዜ ሞገስ እንዲያሳየው አምላኩን ይሖዋን ለመነ፤ በአባቶቹም አምላክ ፊት ራሱን እጅግ አዋረደ። 13  ወደ እሱ አጥብቆ ጸለየ፤ እሱም ተለመነው፤ በእሱ ዘንድ ሞገስ ለማግኘት ያቀረበውንም ልመና ሰማው፤ ወደ ኢየሩሳሌም፣ ወደ ንግሥናው መለሰው።+ ከዚያም ምናሴ፣ ይሖዋ እውነተኛ አምላክ እንደሆነ አወቀ።+ 14  ከዚህ በኋላ በሸለቆው ውስጥ ከሚገኘው* ከግዮን+ በስተ ምዕራብ አንስቶ እስከ ዓሣ በር+ ድረስ ለዳዊት ከተማ+ በውጭ በኩል ቅጥር ሠራ። ቅጥሩ ከዚያ ተነስቶ ከተማዋን በመዞር እስከ ኦፌል+ የሚደርስ ሲሆን እጅግ ከፍ አድርጎ ሠራው። በተጨማሪም በተመሸጉ የይሁዳ ከተሞች ሁሉ ላይ የጦር አለቆች ሾመ። 15  ከዚያም ባዕዳን አማልክቱንና የጣዖቱን ምስል ከይሖዋ ቤት አስወገደ፤+ ደግሞም በይሖዋ ቤት ተራራ ላይና በኢየሩሳሌም የሠራቸውን መሠዊያዎች ሁሉ አፍርሶ ከከተማዋ ውጭ እንዲጣሉ አደረገ።+ 16  በተጨማሪም የይሖዋን መሠዊያ አድሶ+ በላዩ ላይ የኅብረት መሥዋዕቶችና+ የምስጋና መሥዋዕቶች+ ያቀርብ ጀመር፤ የይሁዳም ሰዎች የእስራኤልን አምላክ ይሖዋን እንዲያገለግሉ አዘዘ። 17  ያም ሆኖ ሕዝቡ ከፍ ባሉት የማምለኪያ ቦታዎቹ ላይ መሠዋታቸውን አልተዉም፤ የሚሠዉት ግን ለአምላካቸው ለይሖዋ ነበር። 18  የቀረው የምናሴ ታሪክ፣ ለአምላኩ ያቀረበው ጸሎትና በእስራኤል አምላክ በይሖዋ ስም ያናገሩት ባለ ራእዮች ቃል ስለ እስራኤል ነገሥታት በተጻፈው ታሪክ ውስጥ ተመዝግበዋል። 19  በተጨማሪም ያቀረበው ጸሎት፣+ ልመናው እንዴት እንደተሰማለት፣ የሠራው ኃጢአት ሁሉና ታማኝነት በማጉደል የፈጸመው ድርጊት+ በባለ ራእዮቹ ዘገባዎች ውስጥ ተካተዋል፤ ደግሞም ራሱን ከማዋረዱ በፊት ከፍ ያሉ የማምለኪያ ቦታዎች የሠራባቸው እንዲሁም የማምለኪያ ግንዶችና*+ የተቀረጹ ምስሎች ያቆመባቸው ስፍራዎች በእነዚህ ዘገባዎች ላይ ተጽፈዋል። 20  በመጨረሻም ምናሴ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ እነሱም በቤቱ ቀበሩት፤ ልጁም አምዖን በእሱ ምትክ ነገሠ።+ 21  አምዖን+ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 22 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለሁለት ዓመት ገዛ።+ 22  እሱም አባቱ ምናሴ እንዳደረገው በይሖዋ ፊት መጥፎ ነገር አደረገ፤+ አምዖን አባቱ ምናሴ ለሠራቸው የተቀረጹ ምስሎች ሁሉ ሠዋ፤+ ያገለግላቸውም ነበር። 23  ይሁንና አባቱ ምናሴ ራሱን እንዳዋረደ፣+ በይሖዋ ፊት ራሱን አላዋረደም፤+ ይልቁንም በበደል ላይ በደል እየጨመረ ሄደ። 24  ከጊዜ በኋላም አገልጋዮቹ በእሱ ላይ አሲረው+ በገዛ ቤቱ ውስጥ ገደሉት። 25  ሆኖም የምድሪቱ ሕዝብ በንጉሥ አምዖን ላይ ያሴሩትን ሁሉ ገደላቸው፤+ በእሱም ምትክ ልጁን ኢዮስያስን አነገሠው።+

የግርጌ ማስታወሻ

“ጉድጓድ ውስጥ አግኝተው ያዙት” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “በደረቁ ወንዝ አካባቢ ከሚገኘው።”