ሁለተኛ ዜና መዋዕል 36:1-23

  • ኢዮዓካዝ በይሁዳ ላይ ነገሠ (1-3)

  • ኢዮዓቄም በይሁዳ ላይ ነገሠ (4-8)

  • ዮአኪን በይሁዳ ላይ ነገሠ (9, 10)

  • ሴዴቅያስ በይሁዳ ላይ ነገሠ (11-14)

  • ኢየሩሳሌም ጠፋች (15-21)

  • ቂሮስ ቤተ መቅደሱ እንደገና እንዲገነባ አዋጅ አወጣ (22, 23)

36  ከዚያም የምድሪቱ ሕዝብ የኢዮስያስን ልጅ ኢዮዓካዝን+ በአባቱ ምትክ በኢየሩሳሌም አነገሡት።+  ኢዮዓካዝ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 23 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለሦስት ወር ገዛ።  ይሁን እንጂ የግብፅ ንጉሥ በኢየሩሳሌም ካለው ዙፋኑ አወረደው፤ በምድሪቱም ላይ 100 የብር ታላንትና* አንድ የወርቅ ታላንት ቅጣት ጣለ።+  በተጨማሪም የግብፁ ንጉሥ ኒካዑ+ የኢዮዓካዝን ወንድም ኤልያቄምን በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ አነገሠው፤ ስሙንም ቀይሮ ኢዮዓቄም አለው፤ ወንድሙን ኢዮዓካዝን ግን ወደ ግብፅ ወሰደው።+  ኢዮዓቄም+ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 25 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለ11 ዓመት ገዛ። እሱም በአምላኩ በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ።+  የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነጾር+ ከመዳብ በተሠሩ ሁለት የእግር ብረቶች አስሮ ወደ ባቢሎን ለመውሰድ በእሱ ላይ ዘመተ።+  ናቡከደነጾርም በይሖዋ ቤት ያሉ የተወሰኑ ዕቃዎችን ወደ ባቢሎን ወስዶ በባቢሎን በሚገኘው ቤተ መንግሥቱ አስቀመጣቸው።+  የቀረው የኢዮአቄም ታሪክ፣ የፈጸማቸው አስጸያፊ ነገሮችና በእሱ ላይ የተገኘበት መጥፎ ነገር በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፈዋል፤ በእሱም ምትክ ልጁ ዮአኪን ነገሠ።+  ዮአኪን+ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 18 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለሦስት ወር ከአሥር ቀን ገዛ፤ እሱም በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ።+ 10  በዓመቱ መጀመሪያ* ላይ ንጉሥ ናቡከደነጾር አገልጋዮቹን ልኮ በይሖዋ ቤት ካሉት ውድ ዕቃዎች+ ጋር ወደ ባቢሎን አመጣው።+ የአባቱን ወንድም ሴዴቅያስንም በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ አነገሠው።+ 11  ሴዴቅያስ+ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 21 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለ11 ዓመት ገዛ።+ 12  በአምላኩ በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ። በይሖዋ ትእዛዝ በተናገረው በነቢዩ ኤርምያስ ፊት ራሱን ዝቅ አላደረገም።+ 13  ደግሞም በአምላክ ስም ባስማለው በንጉሥ ናቡከደነጾር ላይ ዓመፀ፤+ ግትር ሆነ፤* ልቡንም አጠነከረ፤ ወደ እስራኤል አምላክ ወደ ይሖዋ ለመመለስ አሻፈረኝ አለ። 14  ዋነኞቹ ካህናት ሁሉና ሕዝቡ፣ ብሔራት የሚፈጽሟቸውን አስጸያፊ ነገሮች በማድረግ እጅግ ከፍተኛ ክህደት ፈጸሙ፤ ይሖዋ በኢየሩሳሌም የቀደሰውንም ቤት አረከሱ።+ 15  የአባቶቻቸው አምላክ ይሖዋ ለሕዝቡና ለማደሪያው ስፍራ ስለራራ መልእክተኞቹን እየላከ በተደጋጋሚ ያስጠነቅቃቸው ነበር። 16  እነሱ ግን የይሖዋ ቁጣ በሕዝቡ ላይ እስኪነድና+ ፈውስ እስከማይገኝላቸው ድረስ በእውነተኛው አምላክ መልእክተኞች ላይ ያላግጡ፣+ ቃሉን ይንቁና+ በነቢያቱ ላይ ያፌዙ+ ነበር። 17  ስለዚህ የከለዳውያንን+ ንጉሥ አመጣባቸው፤ እሱም ወጣቶቻቸውን በቤተ መቅደሳቸው+ ውስጥ በሰይፍ ገደለ፤+ ለወጣቱም ሆነ ለድንግሊቱ፣ ለሽማግሌውም ሆነ ለአቅመ ደካማው አልራራም።+ አምላክ ሁሉንም በእጁ አሳልፎ ሰጠው።+ 18  በእውነተኛው አምላክ ቤት የነበሩትን ትላልቅም ሆኑ ትናንሽ ዕቃዎች በሙሉ፣ የይሖዋን ቤት ውድ ሀብት እንዲሁም የንጉሡንና የመኳንንቱን ውድ ሀብት ሁሉ ወደ ባቢሎን አጋዘ።+ 19  የእውነተኛውን አምላክ ቤት አቃጠለ፤+ የኢየሩሳሌምን ቅጥር አፈረሰ፤+ የማይደፈሩ ማማዎቿን ሁሉ በእሳት አቃጠለ፤ እንዲሁም ውድ የሆኑትን ዕቃዎች በሙሉ አወደመ።+ 20  ከሰይፍ የተረፉትንም ሁሉ ማርኮ ወደ ባቢሎን ወሰዳቸው፤+ እነሱም የፋርስ መንግሥት* መግዛት እስከጀመረበት ጊዜ ድረስ+ የእሱና የወንዶች ልጆቹ አገልጋዮች ሆኑ፤+ 21  ይህም የሆነው ይሖዋ በኤርምያስ በኩል የተናገረው ቃል ይፈጸም ዘንድ፣+ ምድሪቱ የሰንበት ዕዳዋን እስክትከፍል ድረስ ነው።+ ፈራርሳ በቆየችባቸው ጊዜያት ሁሉ፣ 70 ዓመት እስኪፈጸም ድረስ ሰንበትን አከበረች።+ 22  በኤርምያስ በኩል የተነገረው የይሖዋ ቃል ይፈጸም ዘንድ+ የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ+ በነገሠ በመጀመሪያው ዓመት የሚከተለውን አዋጅ በመላ ግዛቱ እንዲያውጅ ይሖዋ የፋርሱን ንጉሥ የቂሮስን መንፈስ አነሳሳ፤ እሱም ይህ በጽሑፍ እንዲሰፍር አደረገ፦+ 23  “የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ እንዲህ ይላል፦ ‘የሰማይ አምላክ ይሖዋ የምድርን መንግሥታት ሁሉ ሰጥቶኛል፤+ በይሁዳ በምትገኘው በኢየሩሳሌምም ቤት እንድሠራለት አዞኛል።+ ከእሱ ሕዝብ መካከል የሆነ አብሯችሁ የሚኖር ማንኛውም ሰው አምላኩ ይሖዋ ከእሱ ጋር ይሁን፤ እሱም ወደዚያ ይውጣ።’”+

የግርጌ ማስታወሻ

አንድ ታላንት 34.2 ኪሎ ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
በበልግ ወቅት ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “አንገቱን አደነደነ።”
ወይም “ንጉሣዊ አገዛዝ።”