ሁለተኛ ዜና መዋዕል 6:1-42

  • ሰለሞን ለሕዝቡ ንግግር አቀረበ (1-11)

  • ሰለሞን በምርቃቱ ወቅት ያቀረበው ጸሎት (12-42)

6  በዚህ ጊዜ ሰለሞን እንዲህ አለ፦ “ይሖዋ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ እንደሚኖር ተናግሯል።+  አሁን እኔ እጅግ ከፍ ያለ ቤት፣ ለዘላለም የምትኖርበት ጸንቶ የተመሠረተ ቦታ ገንብቼልሃለሁ።”+  ከዚያም መላው የእስራኤል ጉባኤ ቆሞ ሳለ ንጉሡ ዞሮ የእስራኤልን ጉባኤ ሁሉ መባረክ ጀመረ።+  እንዲህም አለ፦ “ለአባቴ ለዳዊት በገዛ አፉ እንዲህ ብሎ ቃል የገባውና ይህን በራሱ እጆች የፈጸመው የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ይወደስ፦  ‘ሕዝቤን እስራኤልን ከግብፅ ምድር ካወጣሁበት ዕለት አንስቶ ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ መካከል ስሜ የሚጠራበት ቤት እንዲሠራበት አንድም ከተማ አልመረጥኩም፤+ ደግሞም የሕዝቤ የእስራኤል መሪ እንዲሆን ማንንም አልመረጥኩም።  ሆኖም ስሜ እንዲጠራባት ኢየሩሳሌምን፣+ በሕዝቤም በእስራኤል ላይ ገዢ እንዲሆን ዳዊትን መርጫለሁ።’+  አባቴ ዳዊት ለእስራኤል አምላክ ለይሖዋ ስም ቤት ለመሥራት ከልቡ ተመኝቶ ነበር።+  ሆኖም ይሖዋ አባቴን ዳዊትን እንዲህ አለው፦ ‘ለስሜ ቤት ለመሥራት ከልብህ ተመኝተህ ነበር፤ ይህን በልብህ መመኘትህም መልካም ነው።  ይሁንና ቤቱን የምትሠራው አንተ አይደለህም፤ ሆኖም ለስሜ ቤት የሚሠራልኝ የሚወለድልህ የገዛ ልጅህ* ይሆናል።’+ 10  ይሖዋ የገባውን ቃል ፈጽሟል፤ ልክ ይሖዋ ቃል በገባው መሠረት+ አባቴን ዳዊትን ተክቼ በእስራኤል ዙፋን ላይ ተቀምጫለሁና።+ በተጨማሪም ለእስራኤል አምላክ ለይሖዋ ስም ቤት ሠርቻለሁ፤ 11  በዚያም ይሖዋ ከእስራኤል ሕዝብ ጋር የገባው ቃል ኪዳን ያለበትን ታቦት+ አስቀምጫለሁ።” 12  ከዚያም ሰለሞን በይሖዋ መሠዊያ ፊት፣ በመላው የእስራኤል ጉባኤ ፊት ለፊት ቆመ፤ እጆቹንም ዘረጋ።+ 13  (ሰለሞን የመዳብ መድረክ ሠርቶ በግቢው መካከል አስቀምጦ ነበር።+ የመድረኩ ርዝመት አምስት ክንድ፣* ወርዱ አምስት ክንድ፣ ከፍታውም ሦስት ክንድ ነበር፤ እሱም በመድረኩ ላይ ቆሞ ነበር።) በመላው የእስራኤል ጉባኤ ፊት ተንበርክኮም እጆቹን ወደ ሰማያት ዘረጋ፤+ 14  እንዲህም አለ፦ “የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ሆይ፣ በፊቱ በሙሉ ልባቸው ለሚመላለሱ አገልጋዮቹ ቃል ኪዳኑን የሚጠብቅና ታማኝ ፍቅር የሚያሳይ እንደ አንተ ያለ አምላክ በሰማያትም ሆነ በምድር የለም።+ 15  ለአገልጋይህ ለአባቴ ለዳዊት የገባኸውን ቃል ጠብቀሃል።+ በገዛ አፍህ ቃል ገባህ፤ ዛሬ ደግሞ በራስህ እጅ ፈጸምከው።+ 16  አሁንም የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ሆይ ‘አንተ በፊቴ እንደተመላለስከው ሁሉ+ ልጆችህም በጥንቃቄ ሕጌን ጠብቀው ከተመላለሱ ከዘርህ በእስራኤል ዙፋን ላይ የሚቀመጥ ሰው ከፊቴ አይታጣም’+ በማለት ለአገልጋይህ ለአባቴ ለዳዊት የገባኸውን ቃል ጠብቅ። 17  አሁንም የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ሆይ፣ ለአገልጋይህ ለዳዊት የገባኸው ቃል ይፈጸም። 18  “በእርግጥ አምላክ ከሰው ልጆች ጋር በምድር ላይ ይኖራል?+ እነሆ ሰማያት፣ አዎ ሰማየ ሰማያት እንኳ ሊይዙህ አይችሉም፤+ ታዲያ እኔ የሠራሁት ይህ ቤትማ ምንኛ ያንስ!+ 19  እንግዲህ አምላኬ ይሖዋ ሆይ፣ የአገልጋይህን ጸሎትና ሞገስ ለማግኘት የሚያቀርበውን ልመና በትኩረት ስማ፤ አገልጋይህ እርዳታ ለማግኘት የሚያሰማውን ጩኸትና በፊትህ የሚያቀርበውን ጸሎት አዳምጥ። 20  አገልጋይህ ወደዚህ ስፍራ የሚያቀርበውን ጸሎት ለመስማት ስምህ እንደሚጠራበት+ ወደተናገርከው ወደዚህ ቤት ዓይኖችህ ሌሊትና ቀን ይመልከቱ። 21  አገልጋይህ እርዳታ ለማግኘት የሚያቀርበውን ልመናና ሕዝብህ እስራኤል ወደዚህ ስፍራ በሚጸልይበት ጊዜ+ የሚያቀርበውን ልመና አዳምጥ፤ በማደሪያህም በሰማያት ሆነህ ስማ፤+ ሰምተህም ይቅር በል።+ 22  “አንድ ሰው ባልንጀራውን በድሎ እንዲምል ቢደረግ፣* በመሐላውም* ተጠያቂ ቢሆን፣ በዳዩም በዚህ መሐላ* ሥር ሆኖ እዚህ ቤት ውስጥ ባለው መሠዊያህ ፊት ቢቀርብ፣+ 23  አንተ በሰማያት ሆነህ ስማ፤ ለክፉው እንደ ሥራው በመመለስና+ የእጁን እንዲያገኝ በማድረግ፣ ጻድቁንም ንጹሕ* መሆኑን በማሳወቅና እንደ ጽድቁ ወሮታውን በመክፈል+ እርምጃ ውሰድ፤ አገልጋዮችህንም ዳኝ። 24  “ሕዝብህ እስራኤላውያን አንተን ከመበደላቸው የተነሳ በጠላት ድል ቢነሱና+ ተመልሰው ስምህን ቢያወድሱ+ እንዲሁም በዚህ ቤት በፊትህ ቢጸልዩና+ ሞገስ ለማግኘት ልመና ቢያቀርቡ+ 25  ከሰማያት ሆነህ ስማ፤+ የሕዝብህንም የእስራኤልን ኃጢአት ይቅር በል፤ ለእነሱና ለአባቶቻቸው ወደሰጠኸው ምድርም መልሳቸው።+ 26  “ሕዝቡ አንተን በመበደሉ የተነሳ+ ሰማያት ተዘግተው ዝናብ ቢጠፋ፣+ እነሱም አንተ ስላዋረድካቸው* ወደዚህ ስፍራ ቢጸልዩና ስምህን ቢያወድሱ እንዲሁም ከኃጢአታቸው ቢመለሱ+ 27  ከሰማያት ሆነህ ስማ፤ የአገልጋዮችህን፣ የሕዝብህን የእስራኤላውያንን ኃጢአት ይቅር በል፤ ስለሚሄዱበት ቀና መንገድ ታስተምራቸዋለህና፤+ ለሕዝብህ ርስት አድርገህ ባወረስከው ምድርህም ላይ ዝናብ አዝንብ።+ 28  “በምድሪቱ ላይ ረሃብ+ ወይም ቸነፈር፣+ የሚለበልብና የሚያደርቅ ነፋስ ወይም ዋግ+ ቢከሰት፣ የአንበጣ መንጋ ወይም የማይጠግብ አንበጣ*+ ቢመጣ አሊያም ጠላቶቻቸው በምድሪቱ ላይ ባለ በየትኛውም ከተማ* ውስጥ ሳሉ ቢከቧቸው+ ወይም ደግሞ ማንኛውም ዓይነት መቅሰፍት አሊያም ማንኛውም ዓይነት በሽታ ቢከሰትና+ 29  ማንኛውም ሰው ወይም ሕዝብህ እስራኤል በሙሉ (እያንዳንዱ የገዛ ጭንቀቱንና ሥቃዩን ያውቃልና)+ ወደ አንተ ለመጸለይ+ ወይም ሞገስ እንድታሳየው ልመና ለማቅረብ+ እጁን ወደዚህ ቤት ቢዘረጋ+ 30  አንተ ከመኖሪያ ቦታህ ከሰማያት ሆነህ ስማ፤+ ደግሞም ይቅር በል፤+ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው ብድራቱን ክፈለው፤ ምክንያቱም አንተ ልቡን ታውቃለህ (የሰውን ልብ በሚገባ የምታውቀው አንተ ብቻ ነህ)፤+ 31  ይህም ለአባቶቻችን በሰጠኸው ምድር ላይ በሚኖሩበት ዘመን ሁሉ በመንገዶችህ በመመላለስ አንተን እንዲፈሩ ነው። 32  “በተጨማሪም ከሕዝብህ ከእስራኤል ወገን ያልሆነ የባዕድ አገር ሰው ከታላቁ ስምህ፣* ከኃያሉ እጅህና ከተዘረጋው ክንድህ የተነሳ ከሩቅ አገር ቢመጣ፣+ ወደዚህም ቤት መጥቶ ቢጸልይ፣+ 33  ከመኖሪያ ቦታህ ከሰማያት ሆነህ ስማ፤ የምድር ሕዝቦች ሁሉ እንደ ሕዝብህ እንደ እስራኤል ስምህን እንዲያውቁና+ እንዲፈሩህ እንዲሁም ስምህ እኔ በሠራሁት በዚህ ቤት እንደሚጠራ እንዲያውቁ ያ የባዕድ አገር ሰው የጠየቀህን ሁሉ ፈጽምለት። 34  “ሕዝብህ ጠላቶቻቸውን ለመውጋት አንተ በምትልካቸው መንገድ ለጦርነት ቢወጡና+ አንተ ወደመረጥከው ወደዚህ ከተማ እንዲሁም ለስምህ ወደሠራሁት ቤት አቅጣጫ+ ቢጸልዩ+ 35  ከሰማያት ሆነህ ጸሎታቸውንና ሞገስ ለማግኘት የሚያቀርቡትን ልመና ስማ፤ ፍረድላቸውም።+ 36  “በአንተ ላይ ኃጢአት ቢሠሩ (መቼም ኃጢአት የማይሠራ ሰው የለም)፣+ አንተም በእነሱ እጅግ ተቆጥተህ ለጠላት አሳልፈህ ብትሰጣቸው፣ ጠላቶቻቸውም ራቅ ወዳለ ወይም ቅርብ ወደሆነ ምድር ምርኮኛ አድርገው ቢወስዷቸው፣+ 37  እነሱም በምርኮ በተወሰዱበት ምድር ወደ ልቦናቸው ቢመለሱና ወደ አንተ ዞር በማለት ‘ኃጢአት ሠርተናል፤ አጥፍተናል፤ ክፉ ድርጊትም ፈጽመናል’ በማለት በተማረኩበት ምድር ሆነው ሞገስ ለማግኘት ወደ አንተ ልመና ቢያቀርቡ፣+ 38  ደግሞም ተማርከው በተወሰዱበት፣ ምርኮኛ ሆነው በሚኖሩበት ምድር፣+ በሙሉ ልባቸውና+ በሙሉ ነፍሳቸው* ወደ አንተ ቢመለሱ እንዲሁም ለአባቶቻቸው በሰጠሃቸው ምድር፣ አንተ በመረጥካት ከተማና ለስምህ በሠራሁት ቤት አቅጣጫ ቢጸልዩ፣+ 39  ጸሎታቸውንና ሞገስ ለማግኘት ያቀረቡትን ልመና ከመኖሪያ ቦታህ ከሰማያት ሆነህ ስማ፤ ፍረድላቸውም፤+ በአንተ ላይ ኃጢአት የሠራውን ሕዝብህን ይቅር በል። 40  “አሁንም አምላኬ ሆይ፣ እባክህ በዚህ ቦታ* ወደቀረበው ጸሎት ዓይኖችህ ይመልከቱ፤ ጆሮዎችህም በትኩረት ያዳምጡ።+ 41  አሁንም ይሖዋ አምላክ ሆይ፣ ከብርታትህ ታቦት ጋር ወደ ማረፊያ ቦታህ+ ውጣ። ይሖዋ አምላክ ሆይ፣ ካህናትህ መዳንን ይልበሱ፤ ታማኞችህም በጥሩነትህ ሐሴት ያድርጉ።+ 42  ይሖዋ አምላክ ሆይ፣ የቀባኸውን ሰው ገሸሽ አታድርግ።*+ ለአገልጋይህ ለዳዊት ያሳየኸውን ታማኝ ፍቅር አስብ።”+

የግርጌ ማስታወሻ

ቃል በቃል “ከወገብህ የሚወጣው ወንድ ልጅህ።”
አንድ ክንድ 44.5 ሴንቲ ሜትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “ባልንጀራው በእርግማን ሥር ቢያደርገው።” ግለሰቡ የማለው በውሸት ከሆነ ወይም መሐላውን ከጣሰ እርግማኑ እንደ ቅጣት እንደሚደርስበት ያመለክታል።
ቃል በቃል “በእርግማኑም።”
ቃል በቃል “እርግማን።”
ቃል በቃል “ጻድቅ።”
ወይም “ስላጎሳቆልካቸው።”
ቃል በቃል “በበሮቹ ምድር።”
ወይም “ፌንጣ።”
ወይም “ዝናህ።”
ወይም “ከዚህ ቦታ ጋር በተያያዘ።”
ቃል በቃል “ፊት አትመልስ።”