ሁለተኛ ዜና መዋዕል 7:1-22

  • ቤተ መቅደሱ በይሖዋ ክብር ተሞላ (1-3)

  • የምረቃው ሥርዓት (4-10)

  • ይሖዋ ለሰለሞን ተገለጠለት (11-22)

7  ሰለሞንም ጸሎቱን እንደጨረሰ+ እሳት ከሰማያት ወርዶ+ የሚቃጠለውን መባና መሥዋዕቶቹን በላ፤ የይሖዋም ክብር ቤቱን ሞላው።+  የይሖዋ ክብር የይሖዋን ቤት ሞልቶት ስለነበር ካህናቱ ወደ ይሖዋ ቤት መግባት አልቻሉም።+  የእስራኤልም ሕዝብ ሁሉ እሳቱ ሲወርድና የይሖዋ ክብር ከቤቱ በላይ ሲሆን ይመለከቱ ነበር፤ ወደ መሬት አጎንብሰው ድንጋይ በተነጠፈበት ወለል ላይ በግንባራቸው ተደፍተው ሰገዱ፤ ደግሞም “እሱ ጥሩ ነውና፤ ታማኝ ፍቅሩ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል” እያሉ ይሖዋን አመሰገኑ።  ከዚያም ንጉሡና ሕዝቡ ሁሉ በይሖዋ ፊት መሥዋዕት አቀረቡ።+  ንጉሥ ሰለሞን 22,000 ከብቶችና 120,000 በጎች መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ። በዚህ መንገድ ንጉሡና ሕዝቡ ሁሉ የእውነተኛውን አምላክ ቤት መረቁ።+  ካህናቱም ሆኑ የይሖዋን መዝሙር ለማጀብ የሚያገለግሉ የሙዚቃ መሣሪያዎችን የያዙት ሌዋውያን እንዲያገለግሉ በተመደቡበት ስፍራ ቆመው ነበር።+ (ንጉሥ ዳዊት እነዚህን መሣሪያዎች የሠራው ከእነሱ ጋር* ሆኖ ውዳሴ በሚያቀርብበት ጊዜ “ታማኝ ፍቅሩ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራልና” በማለት ይሖዋን ለማመስገን ነው።) ካህናቱ በእነሱ ትይዩ ሆነው መለከቶቹን በኃይል ይነፉ ነበር፤+ በዚህ ጊዜ እስራኤላውያን ሁሉ በዚያ ቆመው ነበር።  ከዚያም ሰለሞን በይሖዋ ቤት ፊት የሚገኘውን የግቢውን መሃል ቀደሰው፤ ምክንያቱም ሰለሞን የሚቃጠለውን መባና+ የኅብረት መሥዋዕቱን ስብ በዚያ ማቅረብ ነበረበት፤ ይህም የሆነው ሰለሞን የሠራው የመዳብ መሠዊያ+ የሚቃጠለውን መሥዋዕት፣ የእህሉን መባና+ ስቡን+ መያዝ ስላልቻለ ነው።  በዚያን ጊዜ ሰለሞን ከመላው እስራኤል ጋር ይኸውም ከሌቦሃማት* አንስቶ እስከ ግብፅ ደረቅ ወንዝ* ድረስ+ ካለው ምድር ከመጣው ታላቅ ጉባኤ ጋር በመሆን ለሰባት ቀን በዓሉን* አከበረ።+  ይሁንና የመሠዊያውን የምረቃ ሥነ ሥርዓት ለሰባት ቀን ስላከናወኑና በዓሉን ለሰባት ቀን ስላከበሩ በስምንተኛው ቀን* የተቀደሰ ጉባኤ አደረጉ።+ 10  ከዚያም በሰባተኛው ወር፣ በ23ኛው ቀን ሕዝቡን ወደየቤታቸው አሰናበተ፤ እነሱም ይሖዋ ለዳዊት፣ ለሰለሞንና ለሕዝቡ ለእስራኤል ባሳየው ጥሩነት እየተደሰቱና+ ከልባቸው እየፈነደቁ ሄዱ።+ 11  ሰለሞንም የይሖዋን ቤትና የንጉሡን ቤት*+ ሠርቶ ጨረሰ፤ ከይሖዋ ቤትና ከራሱ ቤት ጋር በተያያዘ በልቡ ያሰበውን ሁሉ በተሳካ ሁኔታ አከናወነ።+ 12  ከዚያም ይሖዋ በሌሊት ለሰለሞን ተገልጦለት+ እንዲህ አለው፦ “ጸሎትህን ሰምቻለሁ፤ ይህን ቦታ መሥዋዕት የሚቀርብበት ቤት እንዲሆን ለራሴ መርጬዋለሁ።+ 13  ዝናብ እንዳይዘንብ ሰማያትን ብዘጋ፣ ምድሪቱን እንዲበሉ አንበጦችን ብልክ፣ በሕዝቤ መካከል ቸነፈር ብሰድ፣ 14  በስሜ የተጠሩትም ሕዝቤ+ ራሳቸውን ዝቅ ቢያደርጉ፣+ ቢጸልዩ፣ ፊቴን ቢሹና ከክፉ መንገዳቸው ቢመለሱ፣+ ከሰማያት ሆኜ እሰማለሁ፤ ኃጢአታቸውን ይቅር እላለሁ፤ ምድራቸውንም እፈውሳለሁ።+ 15  በዚህም ስፍራ ለሚቀርበው ጸሎት ዓይኖቼ ይገለጣሉ፤ ጆሮዎቼም ይከፈታሉ።+ 16  አሁንም ስሜ ለዘለቄታው በዚያ እንዲጠራ ይህን ቤት መርጬዋለሁ፤+ ደግሞም ቀድሼዋለሁ፤ ዓይኔም ሆነ ልቤ ሁልጊዜ በዚያ ይሆናል።+ 17  “አንተም አባትህ ዳዊት እንዳደረገው ያዘዝኩህን ሁሉ በመፈጸም በፊቴ ብትሄድ እንዲሁም ሥርዓቶቼንና ድንጋጌዎቼን ብትጠብቅ፣+ 18  ለአባትህ ለዳዊት ‘ከዘር ሐረግህ በእስራኤል ላይ ገዢ የሚሆን አይታጣም’+ በማለት በገባሁለት ቃል ኪዳን መሠረት+ የንግሥና ዙፋንህን አጸናለሁ።+ 19  ሆኖም ጀርባችሁን ብትሰጡ፣ በፊታችሁ ያስቀመጥኳቸውን ደንቦቼንና ትእዛዛቴን ብትተዉ፣ ሄዳችሁም ሌሎች አማልክትን ብታገለግሉና ለእነሱ ብትሰግዱ፣+ 20  እስራኤልን ከሰጠሁት ምድሬ ላይ እነቅለዋለሁ፤+ ለስሜ የቀደስኩትንም ይህን ቤት ከፊቴ አስወግደዋለሁ፤ በሕዝቦች ሁሉ ዘንድ መቀለጃና* መሳለቂያ አደርገዋለሁ።+ 21  ይህም ቤት የፍርስራሽ ክምር ይሆናል። በዚያም የሚያልፉ ሰዎች ሁሉ በመገረም ትኩር ብለው እየተመለከቱ+ ‘ይሖዋ በዚህች ምድርና በዚህ ቤት ላይ እንዲህ ያለ ነገር ያደረገው ለምንድን ነው?’ በማለት ይጠይቃሉ።+ 22  ከዚያም እንዲህ ይላሉ፦ ‘ይህ የደረሰባቸው ከግብፅ ምድር ያወጣቸውን+ የአባቶቻቸውን አምላክ ይሖዋን ትተው+ ሌሎች አማልክትን ስለተከተሉና ለእነሱ ስለሰገዱ እንዲሁም እነሱን ስላገለገሉ ነው።+ ይህን ሁሉ መከራ ያመጣባቸው ለዚህ ነው።’”+

የግርጌ ማስታወሻ

ሌዋውያኑን የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም።
የዳስ በዓልን ያመለክታል።
ወይም “ከሃማት መግቢያ።”
ከበዓሉ በኋላ ያለው ቀን ወይም 15ኛው ቀን።
ወይም “ቤተ መንግሥት።”
ቃል በቃል “መተረቻና።”