የዮሐንስ ሁለተኛው ደብዳቤ 1:1-13

  • ሰላምታ (1-3)

  • በእውነት ተመላለሱ (4-6)

  • ከአሳቾች ተጠበቁ (7-11)

    • “ሰላም አትበሉት” (10, 11)

  • ዮሐንስ የነበረው ዕቅድና የላከው ሰላምታ (12, 13)

 ከሽማግሌው፣ ለተመረጠችው እመቤትና* ለልጆቿ፦ ከልብ እወዳችኋለሁ፤ እኔ ብቻ ሳልሆን እውነትን ያወቁ ሁሉ ይወዷችኋል፤  የምንወዳችሁ በውስጣችን በሚኖረው እውነት የተነሳ ነው፤ ይህም እውነት አብሮን ለዘላለም ይኖራል።  አባት ከሆነው አምላክና የአብ ልጅ ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ እውነትንና ፍቅርን ጨምሮ ጸጋ፣ ምሕረትና ሰላም እናገኛለን።  ከልጆችሽ መካከል አንዳንዶቹ ከአብ በተቀበልነው ትእዛዝ መሠረት በእውነት እየተመላለሱ መሆናቸውን ስላወቅኩ እጅግ ደስ ብሎኛል።+  ስለሆነም እመቤት ሆይ፣ እርስ በርስ እንዋደድ ዘንድ እለምንሻለሁ። (እየጻፍኩልሽ ያለሁት አዲስ ትእዛዝ ሳይሆን ከመጀመሪያ ጀምሮ የተቀበልነው ነው።)+  ፍቅር ሲባል ደግሞ በትእዛዛቱ መሠረት መመላለስ ማለት ነው።+ እናንተ ከመጀመሪያ እንደሰማችሁት ትእዛዙ በፍቅር መመላለሳችሁን እንድትቀጥሉ ነው።  ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ መምጣቱን+ አምነው የማይቀበሉ ብዙ አሳቾች ወደ ዓለም ወጥተዋልና።+ እንዲህ ያለ ሰው አሳችና ፀረ ክርስቶስ ነው።+  ሙሉ ሽልማት እንድታገኙ እንጂ የደከምንባቸውን ነገሮች እንዳታጡ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።+  ከክርስቶስ ትምህርት አልፎ የሚሄድና በትምህርቱ ጸንቶ የማይኖር ሁሉ አምላክ የለውም።+ በዚህ ትምህርት ጸንቶ የሚኖር ሰው ግን አብና ወልድ አሉት።+ 10  ማንም ሰው ወደ እናንተ ቢመጣና ይህን ትምህርት ይዞ ባይመጣ በቤታችሁ አትቀበሉት+ ወይም ሰላም አትበሉት። 11  ሰላም የሚለው ሰው የክፉ ሥራው ተባባሪ ይሆናልና። 12  የምነግራችሁ ብዙ ነገር ቢኖረኝም በወረቀትና በቀለም ልጽፈው አልፈልግም፤ ከዚህ ይልቅ ደስታችሁ የተሟላ እንዲሆን ወደ እናንተ መጥቼ ፊት ለፊት እንደማነጋግራችሁ ተስፋ አደርጋለሁ። 13  የተመረጠችው የእህትሽ ልጆች ሰላምታ ያቀርቡልሻል።

የግርጌ ማስታወሻ

“ለተመረጠችው እመቤት” የሚለው አገላለጽ አንዲትን ሴት ወይም በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረን የክርስቲያን ጉባኤ ሊያመለክት ይችላል።